ወልቂጤ ከተማ ከስድስት ቀናት በኋላ በሽምግልና ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴ መመለሷ ተነገረ

በወልቂጤ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ነዋሪዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች አድርሰዉታል ከተባለዉ ጉዳት በኋላ ለተከታታይ ስድስት ቀናት መደበኛ እንቅስቃሴ ተቋርጦ ቆይቶ ዛሬ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል።

የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ የሆነዉ ሙሃባ ያሲን በተለይ ለአዲስ ዘይቤ እንደተናገረዉ “ከየካቲት 8 ክስተት በኋላ ሙሉ ከተማዋንና ዙሪያዋን ማለት በሚቻል ደረጃ የንግድ እንቅስቃሴ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እና ሌሎች መደበኛ እንቅስቃሴዎች ከተቋረጡ ስድስት ቀናት ያለፈዉ ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ በወቅቱ በተከሰተዉ ድርጊት ነዉ” ብሏል።

ትላንት የካቲት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጉዳት የደረሰባቸዉ ዜጎችን ቤተሰብ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ከመንግሥት አመራሮች የተወጣጡ ኃላፊዎች በአንድ ላይ በተፈጠረዉ ጉዳይ በጥልቅ መወያየታቸዉን ታውቋል።

ተጠያቂዎችን ለህግ ለማቅረብና ለችግሮችም መፍትሔ እየተሰጠ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን ከውይይታቸው በኋላ ዛሬ የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም በወልቂጤ ከተማ መደበኛ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ሁሉም የንግድ ሱቆች ተከፍተዉ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።