የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ለኢንቨስትመንት እንዲሁም ለመኖሪያ ቤትና ለመኪና መግዣ የሚያውሉት 50 ቢሊዮን ብር ለማበደር መዘጋጀቱን ይፋ አድርገዋል። አቤ፣ ወደ አገሪቱ የሚገባው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ ቢሄድም፣ በሕጋዊ መንገድ የሚገባው ግን አነስተኛ መኾኑን ገልጸዋል። በኤምሬቶች የሚገኙ ሕገወጥ የገንዘብ አስተላላፊዎች ለዚህ ችግር ተዋናይ ተጠያቂ እንደኾኑም አቤ በኢምሬቶች ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በተወያዩበት ወቅት ተናግረዋል። ፕሬዝዳንቱ፣ ኢትዮጵያዊያን በባንኩ አመቺ የውጭ ምንዛሬ መላኪያ አማራጮች እንዲጠቀሙም ጥሪ አድርገዋል። ባንኩ ኢምሬቶች ውስጥ ወኪል ቅርንጫፍ ለመክፈት ማቀዱም ተገልጧል።