ኢትዮጵያ ውስጥ የሐይማኖት አባቶችን መግደል ያልተጻፈ ሕግ ኾኗል

እናት ፓርቲ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሐይማኖት አባቶችን መግደል ያልተጻፈ ሕግ ኾኗል ሲል አዲስ ባወጣው መግለጫ ከሷል። ፓርቲው፣ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ አርሲ ዞን፣ ሮቤ ወረዳ፣ የመሰራንጄ ኦዳ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የ78 ዓመቱ መምሬ ንጉሤ ወልደ መድኅን በታጣቂዎች መገደላቸውን ሰሞኑን በግፍ ገልጿል። በተለይ የአርሲ ዞን የደም መሬት ኾኗል ያለው ፓርቲው፣ የሐይማኖት አባቶች ግድያ ወደመለመድ ደረጃ ደርሷል ብሏል። ዕሁድ’ለትም በቦሌ ክፍለ ከተማ የጎጆ ቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን የድጓ መምህር አፈወርቅ አበባው በጥይት መገደላቸውን ፓርቲው ጠቅሷል። የማኅበረ ቅዱሳን ብሮድካስት አገልግሎትም ይህንኑ ግድያ አረጋግጧል።