የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ መንግሥት ያስታጠቀው “የወለጋ ፋኖ” የተሠኘ ታጣቂ ኃይልን ከሰሰ

አማጺው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ መንግሥት ያስታጠቀው “የወለጋ ፋኖ” የተሠኘ ታጣቂ ኃይል በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት እያደረሰ ይገኛል በማለት አዲስ ባወጣው መግእ ከሷል። ቡድኑ፣ መንግሥት ለዚህ ቡድን ድጋፍ የሚሠጥበት አንዱ ምክንያት፣ በአካባቢው ሕዝብ ላይ የፍርሃት ድባብ በመፍጠር ሕዝቡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለሚመራው ዓላማ የሚሠጠውን ድጋፍ እንዲቀንስ ማድረግ ነው ብሏል። ሁለተኛው የመንግሥት ዓላማ ደሞ በኦሮሞና አማራ ሕዝቦች መካከል መቃቃርና “የእርስ በርስ ግጭት” እንዲፈጠር ማድረግ ነው በማለት ቡድኑ ከሷል። ሕዝቡን ከእነዚህ ታጣቂዎች ጥቃት ለመጠበቅ፣ አስፈላጊውን ርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ቡድኑ አስጠንቅቋል። ራሳቸውን “ፋኖ” በማለት የሚጠሩ ታጣቂዎች በዞኑ አንዳንድ ወረዳዎች በሲቪሎች ላይ ጥቃት እንደሚፈጽሙ፣ ዋዜማ የአካባቢውን ነዋሪዎች በመጥቀስ ካሁን ቀደም በተደጋጋሚ መዘገቧ አይዘነጋም።