የአብይ አሕመድ በግድቡ ሰው ሰራሽ ሃይቅ ላይ የተናገረው ውሸት ሲጋለጥ

የህዳሴ ግድብ የፈጠረው ሀይቅ የሚይዘው የውሀ መጠን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ያሏት ሀይቆች ከሚይዙት ውሀ መጠን ይበልጣል በሚል የቀረበው መረጃ የተሳሳተ ነው
/ኢትዮጵያ ቼክ/- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በተሰራጨ ንግግራቸው ላይ የህዳሴ ግድብ የፈጠረው ሀይቅ የሚይዘው የውሀ መጠን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ያሏት ሀይቆች ከሚይዙት ውሀ መጠን ይበልጣል የሚል መረጃ ተናግረዋል (ሊንክ: https://www.facebook.com/share/r/19wghsZ58y/)
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በዚህ ንግግራቸው ላይ “ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጥሮ ጣና፣ አብያታ፣ ሻላ፣ ላንጋኖ የሚባሉ ሁሉም ሀይቆች ተደምረው አሁን ያላቸው አቅም 70 ቢልየን ሜትር ኪዩብ ነው” ብለዋል።
አክለውም “ህዳሴ በሚሞላበት ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሀይቆቹን በሙሉ የሚበልጥ አቅም አለው ማለት ነው። አንድ ሰው ሰራሽ ግድብ በተፈጥሮ እስካሁን ኢትዮጵያ ያላትን ሀይቆች በሙሉ የሚበልጥ መጠን (size) የውሀ ክምችት ያለው ሆኖ ይታያል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ቼክ በዚህ ንግግር ዙርያ ማጣራት ያደረገ ሲሆን ‘ንጋት’ የሚል ስያሜ የተሰጠው የህዳሴ ግድብ በሚይዘው የውሀ መጠን ከኢትዮጵያ ቀዳሚው ሰው ሰራሽ ሀይቅ ቢሆንም ሁሉም ሀይቆች ተደምረው ግን ከህዳሴ ግድብ ሀይቅ በላይ ይይዛሉ እንጂ አያንሱም።
የተለያዩ በመንግስት ጭምር የተለቀቁ መረጃዎች እንደሚያሳዩት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዳሉት የህዳሴ ግድብ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ውሀ የመያዝ አቅም 74 ቢልዮን ኪዩቢክ ሜትር ገደማ ነው።
ይሁንና በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ሀይቆች ውሀ የመያዝ አቅም ከ87 እስከ 97 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሆነ የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥናቶች ያሳያሉ።
ለምሳሌ ‘International Journal of Applied Earth Observation and Geoinformation’ የተባለው የምርምር ተቋም ለ30 ዓመት በ10 የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀይቆች ላይ ያደረገውን ጥናት ተንተርሶ አምና ባወጣው ሪፖርቱ ሀይቆቹ ውሀ የመያዝ አቅማቸው 97.6 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር መሆኑን ጠቁሟል (ሊንክ: https://www.sciencedirect.com/…/pii/S1569843224003613….)
በተመሳሳይ ‘ResearchGate’ የተባለው ተቋም ‘A systematic review of studies on freshwater lakes of Ethiopia’ በሚል የዛሬ ሶስት ዓመት ባሳተመው እና አራት ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች በተሳተፉበት ጥናት የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀይቆች ውሀ የመያዝ አቅም 87 ቢልዮን ኪዩቢክ ሜትር መሆኑን አሳይቷል።
ሌሎች ሪፖርቶች ደግሞ የተፈጥሮ ሀይቆች የውሀ መጠን እስከ 90 ቢልዮን ቢልዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሚደርስ ይናገራሉ።
እነዚህ የጥናት ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት የህዳሴ ግድብ ሀይቅ በሚይዘው የውሀ መጠን አንደኛ ቢሆንም በአጠቃላይ በሀገሪቱ ያሉት ሀይቆች ተደምረው ከሚይዙት የውሀ መጠን ግን አይበልጥም።
-ኢትዮጵያ ቼክ-