ለዩንቨርስቲ መምህራን ተለይቶ ደሞዝ ሊጨመር አይችልም – ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

የፈተና ስርቆት እና ኩረጃ በአደረጃጀት ጭምር እየተመራ መሆኑን የጠቀሰው ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች በየዓመቱ ፈተናው እየተጠበቀ መነገጃ እየሆነ መምጣቱን የ12 ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ መፍጠሪያ እንዲሆን የማድረግ ልምምድ ማደጉን አስታውቋል።  የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የጥቅማ ጥቅም በተለይ የደሞዝ ጥያቄ ጎልቶ መነሳቱ ተጠቅሶ የተጠየቁት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ አሁን ባለው ሁኔታ ለመምህራኑ ተለይቶ ደሞዝ ሊጨመር አይችልም ብለዋል። በዚህ ዓመት ውድመት ከደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች መካከል 200 ያህሉን እገነባለሁ የሚለው ትምህርት ሚኒስቴር በተለያዩ ሃገራት ኤምባሲዎች ሥር የሚተዳደሩ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ማጭበርበር ውስጥ ገብተዋል በማለት ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ገልጿል።

የትምህርት ሚኒስቴር ያለፉት 5 ወራት ሥራዎቹን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት የሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ በሀገሪቱ ከሚገኙ 47 ሺህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 90 በመቶ ያህሉ ከደረጃ በቻች የሚገኙ ናቸው ብሏል። በተለያዩ ችግሮች ውድመት እና ጉዳት የደረሰባቸው ከ 4 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም በዚህ ዓመት መልሼ እገነባቸዋለሁ ያላቸው ትምህርት ቤቶች ቁጥር ዝቅተኛ ነው በሚል ከቋሚ ኮሚቴው፤ «ውድመት የደረሰባቸው ትምህርት ቤቶች የሚታይ ነው። ከችግሩ ስፋት ጋር የሚመጣጠን ሥራ እየተሠራ ነው ብላችሁ ታስባላችሁ ወይ?» ተብሎ ተጠይቋል

በአደረጃጀት ጭምር የሚመራ የፈተና ስርቆት እና ኩረጃ ከመንሰራፋቱ በላይ በማኅበራዊ መገናኛዎች ይህንን የሥራ ዘርፍ መነገጃ የማድረግ ችግር እየገጠመው መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። የግል ትምህርት ቤቶች የሚቆጣጠራቸው አልነበረም ያሉት ሚኒስትሩ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ይህ እንዲታረም እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። ጥሩ የሚባሉ የግል ትምህርት ቤቶች የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እስኪስተካከሉ እና አዳሪ ትምህርት ቤቶች እስኪስፋፉ በውድድር ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ተማሪዎች 10 በመቶ በነፃ እንዲያስተምሩ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

«የመንግሥት ባለሥልጣናት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት የግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው። አንዱ ችግሩ ደሃው የሚማርብትን ትምህርት ቤት የሚከታተል ሰው አልነበረም። ደሃውን የበለጠ ለድህነት የሚዳርገው ትምህርት የሚያገኝበት ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። ልዩነት በገንዘብ ብቻ ሳይሆን በእውቀት ሰፊ ልዩነት የሚፈጠርበት ሁኔታ ተፈጥራል።» ብለዋል ፕሮፌሰሩ

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ትምህርት ቤት ትእቢትም ፣ ማጭበርበርም ውስጥ እንደሚገኙ ተገልጿል። ይህንን ለማስተካከል እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊ የውጭ ዜጎችን በዩሮ የትምህርት ቤት ክፍያ እየጠየቀ ያለው የጀርመን ትምህርት ቤት እንዲያስተካክል ቢነገረውም ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑን ተናግረዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የደሞዝ ጥያቄን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል። «ዩኒቨርሲቲዎች በሲቪል ሰርቪስ ሕግና የደረጃ መስፈርት እስከሰሩ ድረስ የተሻለ ገንዘብ ሊያገኙ [ የዩኒቨርሲቲ መምህራን] አይችሉም። መንግሥት ደሞዝ ልጨምር ቢል የሚጨምረው ለመምህራን ብቻ አይደለም። ለሌሎችም መጨመር አለበት። ያ ግን አሁን ሊሆን የሚችል አይደለም።» ብለዋል የትምሕርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ