ቆቦ ሙሉ በሙሉ ነፃ ወጥታለች ጥምር ጦሩ ወደ ፊት እያጠቃ ጉዞዉን ቀጥሏል።

ጎብዬ ላይ፣ በላጎ ላይ ደግሞም አራዱም ላይ ከባድ ምሽግ ነበር ህወሓት አዘጋጅታ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር ስትዋጋ የከረመችው። ሺ የትግሬ ወጣቶች እንደቅጠል የረገፉትም እዚሁ ምሽግ ውስጥ መሽገው ነበር። የሃገር መከላከያው ጦር ከነ ባንዳው፣ የምሥራቅ ዐማራ ፋኖ ጦር፣ የዐማራ ልዩ ኃይልና የዐማራ ሚኒሻም ሊወጋው ከፊቱ ከቆመው የትግሬ ሠራዊት ጋር ሲጋደል የነበረውም በእነዚህ ምሽጎች ዙሪያ በተደረጉ እልህ አስጨራሽ ጦርነቶች ነው።

ህወሓት ላለመልቀቅ፣ ጥምር ጦሩ ደግሞ ለማስለቀቅ ሲተጋተጉ ከርመዋል። ከህወሓት ዕድል ቀንቷቸው የተማረኩም አሉ። ከጦሩም ተቆርጦ በሴራ የተማረከ ነበር። የሆነው ሆኖ ዛሬ ግን ህወሓት አቅም አጥታለች። ጉልበትም ከድቷታል። አኬሯም ወድቋል። በቀደም ዕለት ከእኛ መከላከያ ሆኖ ሲያዋጋ የነበረውንና በብዙ ጀግኖች ተጋድሎ ተይዞ የነበረን ገዢ መሬት አስለቅቆ ጦሩን ያስመታው ሻለቃ ላይ ጦሩ የርሸና እርምጃ ከወሰደ በኋላ፣ ለምሥራቅ ዐማራ ፋኖም እንደ ልቡ በሚያውቀው ጋራና ሸንተረር ላይ ይፈነጭ ዘንድ ነፃነት ከተሰጠው በኋላ፣ መከላከያው ተተኳሽ፣ ለምሥራቅ ዐማራ ፋኖ በገፍ ማቅረቡን ከቀጠለ በኋላ፣ የአየር ሽፋኑ በተገቢው መልኩ ለተዋጊው ሠራዊት ከተደረገ በኋላ፣ እነሆ ይኸው ዛሬ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ድል ተገኝቷል።

ዛሬ ቆቦ፣ ሮቢት፣ ጉብዬ ነፃ ይወጡ ዘንድ ግን ከላይ የተጠቀሱት ምሽጎች መሰበር፣ ብዙ የኢትዮጵያ ልጆችም መስዋዕትነት መክፈል ነበረባቸው። በመጨረሻ ግን ማንም ይሁን ማን ኢትዮጵያን ሲኦል ማድረግ አይቻለውምና የማታ ማታ በራያ ምድር ሲዋደቁ የከረሙት በተለይ የምሥራቅ ዐማራ ፋኖ ጀግኖች ቀድመው ዛሬ የቆቦ ከተማን ነፃ አውጥተዋል።