የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከስልጣን ተነሱ

ዶ/ር ሹመቴ ግዛው፤ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ከጥር 2012 ጀምሮ ለኹለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በዋና ዳይሬክተርነት መርተውታል። ዶ/ር ሹመቴ ወደ ኢንሳ ከመምጣታቸው በፊት ለስምንት ወራት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ዶ/ር ሹመቴ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንትም እንደነበሩም ኢትዮጵያ ኢንሳይደር በዘገባው አመላክቷል።

ካለፈው ህዳር ወር 2014 ጀምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ሰለሞን ሶካ፤ ለኹለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ የመሩትን ዶ/ር ሹመቴ ግዛውን በመተካት ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ መሾማቸው ተገልጿል።

ሰለሞን ሶካ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነ መሾማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን መቆጠባቸው ተገልጿል።

ከማይክሮ ሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በሶፍት ዌር ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት ሰለሞን፤ በ“ኢንሳ” ከሶፍት ዌር መሐንዲስነት እስከ ቡድን መሪነት ባሉት ቦታዎች አገልግለዋል።

አዲሱ ተሿሚ በኮምፒውተር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከቻይና ኤሌክትሮኒክ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ ከዘጠኝ ወር በፊት የምክትል ዳይሬክተርነት የኃላፊነት ቦታ ተሰጥቷቸው ወደ “ኢንሳ” ከመመለሳቸው በፊት፤ “ቴክ ማሂንድራ” በተባለ የህንድ የመረጃ ቴክኖሎጂ አገልግሎት እና አማካሪ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሆነው ለአምስት ዓመታት ሰርተዋል።

በሰኔ 2013 በተካሄደው ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ዕጩ የነበሩት ሰለሞን፤ የተወዳደሩበትን የደቡብ ክልል ኮንሶ ዞንን ወክለው የፓርላማ አባል መሆን ችለዋል። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ከተቀላቀሉ በኋላ የምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ተሰይመዋል።

የኢንፎርሜሽን እና ኮምፒውተርን መሰረት ያደረጉ ቁልፍ መሰረት ልማቶች ደህንነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት የተጣለበት ኢንሳ፤ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ነው። ተቋሙ በአዋጅ ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል፤ በተመረጡ ድንበር ዘለል የብሔራዊ ደህንነት ስጋት እንቅስቃሴዎች ዙሪያ መረጃ የመሰብሰብ፣ የመተንተን እና ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይገኝበታል።

የሳይበር ወንጀሎችን በመከላከልና በመመርመር ሂደት ለፖሊስ እና ሌሎች በህግ ስልጣን ለተሰጣቸው አካላት ትብብር የማድረግ እና ድጋፍ መስጠትም ከተቋሙ ተግባራት መካከል የሚጠቀስ ነው።