የአማራ ብሄራዊ ንቃንቄ- አብን፣  ሕወሃትን የሽብር ቡድን ብሎ፣ በሕግ እንዲታገድ ጠየቀ 


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ(አብን) በምእራብና መካከለኛ ጎንደር ዞኖች በቅማንት ስም የተደራጁና በሕወሃት የሚትገዙ ቡድኖች እየፈጠሩ ባሉት ቀውሱ ዙሪያ ማወጣው መግለጫ፣ ሕዝብን እያሸበረ ነው ያለው የኢሕአዴግ አባል ደርጅት የሆነው ሕወሃትን ከሷል።

“በአማራ ሕዝብ በአጠቃላይ፤ በሰሜን ምዕራብ አማራ በተለይ እየደረሰ ላለው የሽብር ድርጊቶች ጠንሳሽ እንዲሁም የሥልጠና፣ የትጥቅና ፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር–ሕወኃት ነው” ያለው አብን ” ቡድኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በፈፀማቸውና እየፈፀማቸዉ ባሉ የዘር ማጥፋት፣ ዘር ማፅዳት፣ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ከፍተኛ ዘረፋና ውንብድና እንዲሁም በአገርና በሕዝቦች አንድነት ላይ እየፈፀመ ባለው የሽብርና የጥፋት ድርጊቶች መነሻነት በአሸባሪነት ተፈርጆ ከማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መታገድ እንዳለበት አብን በጽኑ ያምናል። ስለሆነም ሕወኃት ከአገሪቱ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲፋቅ አብን እየጠየቀ ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ የሚሰሩ የንግድ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች/የጥፋት ቡድኖች ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ አብን በአንክሮ ያሳስባል። ከሕወኃት ጋር ግንባር የፈጠሩ ፓርቲዎችም ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ አብን ይጠይቃል” ሲል በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ጠንካራ መግለጫ ነው ያወጣው።

አብን ሕወሃት እንድታገድ ጥሪ ክማቀረቡ በተጨማሪ፣ የአማራ ክልል መንግስትና እሪ ደርጅቱ አዴፓ ፣ በጎንደር ለተፈጠረው ችግር ሃላፊነት መዉሰድ እንዳለበትም አሳስቧል። “የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ገዥ ፓርቲ አዴፓ የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ አኳያ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ የተነሳ በሕዝባችን ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ጥፋት ኃላፊነቱን መዉሰድ እንዳለንበት ይገለጸው የአብን መግለጫ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥትና ፓርቲ ኃላፊዎች ላይም እርምጃ እንዲወስድ አብን አሳስቧል።

የአብን ሙሉ መግለጫ እንሆ፡

——

በወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ከአብን የተሰጠ የአቋም መግለጫ
*****
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ(አብን) በሰሜን ምዕራብ አማራ (ደምቢያ፣ጭልጋና መተማ አካባቢዎች) በሕዝባችን ላይ በተከፈተው ጥቃትና ወረራ በደረሰው ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀልና ኃብት ንብረት መውደም የተሰማውን ጥልቅ ኃዘን በቅድሚያ ይገልፃል። ንቅናቄው በሕዝባችን ላይ የተከፈተውን ጥቃትና ወረራ አስመልክቶ ኅዳር 29 እና 30/2011 ዓ/ም በጎንደር ከተማ ባደረገው ድንገተኛ አስቸኳይ ስብሰባ በዝርዝር ተወያይቶ የውሳኔ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።

በዚሁ መሰረትም፦
1) «የቅማንት ጥያቄ» በሚል ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ባለፉት 4 ዓመታት «የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላታችን ነው» ብለው የተነሱ ኃይሎችን አጀንዳ በመሸከም የሕዝባችንን ውስጣዊ አንድነትና ሰላም በማናጋት ተደጋጋሚ ሁከትና ሽብር በመፍጠር አማራውን ለሞት፣ አካል ጉዳት፣መፈናቀል፣ ኃብትና ንብረት መውደም እንዲሁም ማኅበረ–ኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በከፍተኛ ሁኔታ በማስተጓጎል መጠነሰፊ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ። ለአብነት እንኳን ባለፉት ቀናት በጭልጋ፣መተማ፣ ደምቢያና አካባቢው በበርካታ የገጠር ቀበሌዎችና ከተሞች በታቀደ አኳኋን በሲቪል ደረጃ ሊያዙ የማይገቡ የጦር መሣሪያዎችን ጭምር ታጥቀው እየፈፀሙት ባለው የሽብር ድርጊት የበርካታ ወገኖቻችን ሕይወት አልፏል፤ አካል ጎድሏል፤ ሕፃናትን አፍኗል፤ ሰዎችን በማገት ውንብድና ፈፅሟል፤ መኖሪያ መንደሮች እንዲሁም የንግድና ማኅበራዊ ተቋማት ወድመዋል።

በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝባችን ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ በመጋለጥ ላይ ይገኛል። የግጭቱ መነሻ በትሕነግ/ሕወኃት/ የተፅዕኖ ዘመን የነበረው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ባልተሰጠው ሥልጣንና ሕጋዊ አካሄዶችንም ባልተከተለ ሁኔታ በመጀመሪያ 42 ቀበሌዎችን፣ ቀጥሎ 27 ቀበሌዎችን፤ በድምሩ 69 ቀበሌዎችን ያለ ሕዝብ ተሳትፎና ይሁንታ ኃላፊነት ለማይሰማው ቡድን እንዲያስተዳድር መስጠቱን ተከትሎ፤ ይኸው የሕወኃት ተላላኪ ቡድን ከሕግ ውጭ የተሰጡትን ቀበሌዎች በሰላማዊ መንገድ ከማስተዳደር ይልቅ አካባቢውን የብጥብጥና ሁከት ማዕከል ማድረግን መርጦ በሕዝባችን ላይ የወሰደው ጥቃትና ወረራ ነው።

ስለሆነም የጥፋት ቡድኑ ዓላማው የራስ ገዝ አስተዳደር መስርቶ ማስተዳደር ሳይሆን አማራውን ዘላለማዊ እረፍት የመንሳት የሕወኃት ቋሚ ተልዕኮ አስፈፃሚ ስለሆነ እያደረሰ ያለው ጥፋት ከቁጥጥር ውጭ ሳይወጣ በአስቸኳይ ወደ ሕግ እንዲቀርብ፤ ያለሕዝብ ይሁንታና ፈቃድ በፖለቲካ ውሳኔ የተሰጡት 69 ቀበሌዎችም ውሳኔ ሕዝብ እንዲሰጥባቸውና ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ እንዲበጅለት አብን በጥብቅ ያሳስባል።

2) በአማራ ሕዝብ በአጠቃላይ፤ በሰሜን ምዕራብ አማራ በተለይ እየደረሰ ላለው የሽብር ድርጊቶች ጠንሳሽ እንዲሁም የሥልጠና፣ የትጥቅና ፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር–ሕወኃት ነው። ይህ ቡድን ከአፈጣጠሩ ጀምሮ በአማራ ጥላቻ የሰከረ፤ በተለይ ደግሞ በለስ ቀንቶት የአገሪቷን ሥልጣን ከያዘ በኋላ ይዞት የመጣውን አማራ ጠል ትርክት መንግሥታዊ መመሪያ በማድረግ በሕዝባችን ላይ ተነግሮ የማያልቅ ጥፋት አድርሷል፤ በማድረስ ላይም ይገኛል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ በፈፀማቸውና እየፈፀማቸዉ ባሉ የዘር ማጥፋት፣ ዘር ማፅዳት፣ መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ከፍተኛ ዘረፋና ውንብድና እንዲሁም በአገርና በሕዝቦች አንድነት ላይ እየፈፀመ ባለው የሽብርና የጥፋት ድርጊቶች መነሻነት በአሸባሪነት ተፈርጆ ከማናቸውም የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መታገድ እንዳለበት አብን በጽኑ ያምናል። ስለሆነም ሕወኃት ከአገሪቱ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝርዝር ውስጥ እንዲፋቅ አብን እየጠየቀ ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልኩ የሚሰሩ የንግድ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች/የጥፋት ቡድኖች ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ አብን በአንክሮ ያሳስባል። ከሕወኃት ጋር ግንባር የፈጠሩ ፓርቲዎችም ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ አብን ይጠይቃል።

ይህንን በመተላለፍ በሕዝባችን ላይ በጥፋት ተግባር ላይ ተሰማርተው በሚገኙ ማናቸውም አካላት ላይ ከሕዝባችን ጋር በመሆን አስፈላጊውን እርምጃ የምንወስድ መሆኑን እናስጠነቅቃለን።

3) በመንገድ ሥራ ሽፋን በሰሜን ምዕራብ አማራ ተሰማርቶ የሚገኘው ሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት ለጥፋት ኃይሎች የትጥቅና ትራንስፖርት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ደርሰንበታል። ይህ ድርጅት ለግንባታ ሥራ በሚጠቀምባቸው ቦቴዎችና የኮንስትራክሽን መኪናዎች እያጓጓዘ ለጥፋት ኃይሎች ባቀበላቸው ከባድ የጦር መሣሪያዎችና ተቀጣጣይ ፈንጂዎች በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ የሕይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ደርሷል።

ስለሆነም ሱር ኮንስትራክሽን ከተቋቋመበት ዓላማ ውጭ ተሰማርቶ በመገኘት በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ መሰረት ድርጅቱና የሥራ ኃላፊዎችም በሕግ እንዲጠየቁ፤ ላደረሰው በደል ካሳ እንዲከፍል፣ ኃብትና ንብረቱ እንዲወረስ እንዲሁም ድርጅቱ ፈቃዱ እንዲሰረዝ አብን ይጠይቃል።

4) የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ገዥ ፓርቲ አዴፓ የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ አኳያ ኃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ የተነሳ በሕዝባችን ላይ ለደረሰው ከፍተኛ ጥፋት ኃላፊነቱን በመውሰድ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባልተወጡ በየደረጃው በሚገኙ የመንግሥትና ፓርቲ ኃላፊዎች ላይም እርምጃ እንዲወስድ አብን በጥብቅ ያሳስባል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የክልሉ መንግሥትና አዴፓ የሕዝባችንን ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያደርገው ጥረት አብን ከጎኑ እንደሚቆም ዝግጁነቱን ይገልፃል።

5) የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በክልሉ ውስጥ ካሉት ካምፖች በተደጋጋሚ ጊዜ እየወጣ ሕግን ያልተከተለ ጣልቃገብነት ሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ ይገኛል። ይህ የሆነውም ተቋሙ ለረጅም ዘመናት በሕወኃት አገዛዝ ሥር በነበረባቸው ጊዜያት ገልለተኛ ያልነበረ ከመሆኑም በላይ የአማራ ጠል ኃይሎች በውስጡ የተሰገሰጉበት በመሆኑ አጋጣሚ እየፈለጉ በሕዝባችን ላይ በቀጥታ ጥቃት ከመፈፀም ጎን ለጎን ለጥፋት ቡድኖች ሽፋንና ድጋፍ የሚሰጡ በመሆኑ ነው።

ስለሆነም አብን የመከላከያ ሰራዊት ስምሪቱን በሕግ አግባብ እንዲያደርግ እየጠየቀ እስካሁን ድረስ በሰራዊቱ ውስጥ ተሰግስገው በአማራ ሕዝብ ላይ ጥፋት ያደረሱ ኃይሎችን ለሕግ እንዲያቀርብ ይጠይቃል።

6) በሰሜን ምዕራብ አማራ በደረሰው ጥቃትና ወረራ ሕዝባችን ለከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ተጋልጧል። ስለሆነም መላው የአማራ ሕዝብ፣ የአማራ ባለሐብቶች፣ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት፣ ወንድም ሕዝቦች እንዲሁም ዓለማቀፍ ግብረሰናይና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች ሰብአዊ እርዳታና ድጋፍ እንዲያደርጉ አብን ይጠይቃል።

7) የአማራን ሕዝብ የውስጥ አንድነት ለማናጋት ለጥፋት ኃይሎች የሚድያ ሽፋን በመስጠት ግጭት በማባባስ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው አንዳንድ የሚድያ ተቋማትና ግለሰቦች ከጥፋት ድርጊታቸው እንዲቆጠብ አብን ያስጠነቅቃል። የብሮድካስት ባለሥልጣንም የግጭት ነጋዴ በሆኑ ሚድያዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።

8: በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ አመራሮችና ስታፎች ከመደበኛ የመማር–ማስተማርና አስተዳደራዊ ሥራቸው ውጪ ከጥፋት ኃይሎች ጋር ተሰልፈው በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ በደል እየፈፀሙ ይገኛሉ። መንግሥት ጉዳዩን አጣርቶ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።

9) በአማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተውን ጥቃትና ወረራ የሚመለከታቸው አካላት በአስቸኳይ ማስቆም ካልቻሉ መላው ሕዝባችንን በማስተባበር ራሱን እንዲከላከል ጥሪ የምናቀርብ መሆኑን እናሳውቃለን።

በመጨረሻም እነዚህን የጥፋት ኃይሎች በመመከት የአማራ ሕዝብ አለኝታነታቸውን ላሳዩ አርሶአደሮች፣ፋኖዎችና የፀጥታ ኃይሎች ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረብን በተሰዉ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ኃዘን እንገልፃለን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው አማራ መጽናናትን እንመኛለን። ሕዝባችን ከጫፍ እስከጫፍ ላሳየው አንድነት አብን የተሰማውን ኩራት እየገለፀ በቀጣይም ጉዳዩን በንቃት እንዲከታተልና እንዲጠብቅ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!

ኅዳር 30/2011 ዓ/ም
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ
ጎንደር፥ አማራ፣ ኢትዮጵያ