መፍትሔ ያጣው የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ዞን ግጭት

በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም. በአጣዬ ከተማ ተፈጥሮ በነበረ ግጭት ከ300 በላይ ዜጎች ሕይወታቸው እንዳለፈ በተለያዩ ሪፖርቶች ይፋ የተደረገው መረጃ ያሳያል፡፡ ግጭቱ ከወር በኋላም እንደ አዲስ ከሚያዝያ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንደገና አገርሽቶ አጣዬ ከተማን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አወደማት፡፡

ጥንት ታሪኳን የሚናገሩ ሰዎች ኤፌሶን ትባል እንደነበር ያስረዳሉ፡፡ በአሁን ስሟ አጣዬ እየተባለች የምትጠራዋ ይህች ትንሽ ከተማ፣ አዲስ አበባን ከደሴና ከመቀሌ ጋር የሚያገናኘው ዋና ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡ አካባቢውን የሚያውቁ የከተማዋ ትንሽነትና የምትገኝበት ዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ቀድሞ ትዝ እንደሚላቸው ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ግጭት በባህሪው አውዳሚ በመሆኑ፣ ደጋግሞ የጎበኛት የግጭት በትር ትንሽቱን ከተማ ያላትን ትንሽ ነገር ሁሉ ሙሉ ለሙሉ ሲያወድምባት ነው የታየው፡፡

በጊዜው በአካባቢው የደረሰውን ውድመት የሚያጣራው ግብረ ኃይል እንደገለጸው፣ የአጣዬን ውድመት ደግሞ ለመጠገን 1.5 ቢሊዮን ብር ይጠይቅ ነበር፡፡ በአጣዬ ከተማ ያሉ 1‚529 ቤቶችን ጨምሮ በአካባቢው በአጠቃላይ 3‚073 ቤቶች መውደማቸውንም ይፋ አድርጎ ነበር ግብረ ኃይሉ፡፡

አጣዬና አጎራባቾቿ ይህን ከባድ ጉዳት ካስተናገዱ አንድ ዓመት ተቆጠረ፡፡ ዓምና በአካባቢው ከባድ ጉዳት በደረሰ ልክ በዓመቱ በዚህ ወር ሚያዝያ 2014 ዓ.ም. አካባቢው ሌላ ዙር ግጭት ዘንድሮም ተደገመ፡፡

አጣዬን ዋና ከተማው ያደረገው የሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ ዘንድሮ በደረሰው ግጭትም አሥር ሰዎች እንደ ሞቱ፣ ስምንት እንደቆሰሉበት ተነግሯል፡፡ በዚሁ ወረዳ በግጭቱ 125 ቤቶች የወደሙ ሲሆን፣ በተለይ ዘምቦ ቀበሌ ሞላሌ መንደር ከባድ ግጭት መካሄዱን፣ ግጭቱ አጎራባች የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ድረስ የዘለቀ መሆኑም ታውቋል፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባለሥልጣናት ከኤፍራታና ግድም የተነሱ ፋኖ የተባሉ ታጣቂዎች በሞላሌ በኩል ወደ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በመግባት ጥቃት አድርሰዋል ብለዋል፡፡ የዞኑ አስተዳዳሪዎች እንዳሉት ሙጤ ፈጫ፣ ጥቁሬ ወደዋና ወሰን ኩርኩር ከተባሉ ቀበሌዎች 3‚000 ሰዎች በጥቃቱ ተፈናቅለዋል፡፡ እንዲሁም አሥር የሚደርሱ ሰዎች ተገድለዋል 40 ደግሞ ቆስለዋል ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ኡመር አልዩ፣ ‹‹ከሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታና ግድም ወረዳ የተነሳው ፋኖ የተባለው የአማራ አሸባሪ ኃይል ነው የግጭቱ ምንጭ፤›› ይላሉ፡፡

የኤፍራታና ግድም ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ችሮታው ባሳዝን ግን፣ ‹‹ለግጭቱ ምንጭና ዋና መፍትሔውም በአካባቢው የሚንቀሳቀሰውን የኦነግ ሸኔ ኃይል ማስወገድ ነው፤›› ሲሉ ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡

የሰሜን ሸዋ ዞን በተለይ የኤፍራታና ግድም፣ እንዲሁም የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን አካባቢ በተደጋጋሚ ግጭቶችን በማስተናገድ ይታወቃል፡፡ ቀጣናው በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ደጋግሞ ግጭት የጎበኘው ቢሆንም፣ ነገር ግን ለዚህ ግጭት አንዱ በሌላው ላይ ጣት ከመቀሰርና ከመወነዳጀል ባለፈ የጋራ መፍትሔ ሲፈለግለት እምብዛም አልታየም፡፡

ዘንድሮ በደረሰው ግጭት ብቻ ሳይሆን ዓምናም ሆነ ካቻምና በደረሱ ግጭቶች ወቅት እርስ በርስ መወነጃጀል ነበር፡፡ የሰሜን ሸዋ ማለትም የአጣዬና አካባቢዋ ግጭት አካባቢያዊ ከመሆን ይልቅ፣ በትልልቆቹ የብልፅግና መሥራች ፓርቲዎች መካከል ጭምር የመግለጫ ቁርቁስ ያስነሳ ጉዳይ ነበር፡፡ ጉዳዩ በፓርላማ ጭምር የቃላት ጦርነት ያወራወረ አጀንዳ ሆኖም ያውቃል፡፡ በሽምግልናና በአካባበያዊ ዕርቅ ለወትሮው መብረዱ ይነገርለት የነበረው የአጣዬና አካባቢው ግጭት ድግግሞሹ፣ ባህሪውና አድማሱ እየሰፋ የሄደ ለመፍታትም አስቸጋሪ የሆነ የፖለቲካ ችግር ወደ መሆን ተሻግሯል፡፡

ዘንድሮ ‹‹አሸባሪው ፋኖ›› የግጭቱ መነሻ ተብሎ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባለሥልጣናት እንደተወነጀለው ሁሉ ዓምናም ሲባል ነበር፡፡ ካቻምና ግን ‹‹የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በአካባቢው ገብቶ ጥቃት ከፈተ፤›› የሚል ውንጀላ መሰማቱ ይታወሳል፡፡ ካቻምና የአማራ ልዩ ኃይል በአካባቢው ላይ ጥቃት አደረሰ ቢባልም፣ ዘንድሮ ግን የአማራ ልዩ ኃይል ፋኖ የተባሉትን ታጣቂዎች ጥቃት ለማስቆም መታገሉንና በፋኖና በልዩ ኃይሉ መሀል ግጭት መፈጠሩን በተለያዩ መረጃ ምንጮች በመዘገብ ላይ ነው፡፡ ካቻምና የግጭቱ ምንጭ የተባለው ኃይል ዘንድሮ ግጭት አርጋቢ ተብሎ መቅረቡ፣ ስለአካባቢው የግጭት ሁኔታ ውስብስብነት ፍንጭ ሰጪ ነው የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡

በተቃራኒው በኤፍራታና ግድም ወረዳ ወይም በሰሜን ሸዋ ዞንና በአማራ ክልል ባለሥልጣናት የሚቀርበው የግጭት መነሻ ጉዳይ ተመሳሳይነት ያለው ነው፡፡ በእነዚህ ወገኖች በኩል ዓምናም ሆነ ካቻምና የግጭቱ ቆስቋሽና ጥቃት አድራሹ ኃይል፣ ‹‹በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የኦነግ ሸኔ ኃይል ነው፤›› የሚል መረጃ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ለዘንድሮው ግጭትም ዋና ተጠያቂው ኦነግ ሸኔ መሆኑን ነው የተሰማው፡፡

ይህ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአማራ ክልል በኩል ሲሰጥ የቆየ የችግሩ መነሻ ተብሎ የሚቀርብ ምላሽ ግን፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ባለሥልጣናትም ሆነ በኦሮሚያ አመራሮች በኩል ቅዋሜ ገጥሞታል፡፡ ዘንድሮና ዓምና ግጭት ያነሱት ፋኖዎች መሆናቸውን፣ ካቻምና ደግሞ የአማራ ልዩ ኃይል ነው ፀጥታ አደፍራሹ የሚል መረጃ በእነዚህ ወገኖች ይሰጣል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም የግጭት ቀጣና በሆነው በዚህ አካባቢ ኦነግ ሸኔ የሚባል ኃይል አይንቀሳቀስም የሚል መረጃም ይቀርባል፡፡

የአማራና የኦሮሞ ፓርቲዎች እንዲሁም የሁለቱ ክልሎች ባለሥልጣናት በአጣዬና በዙሪያው ስላለው ተደጋጋሚ ግጭት ፍፁም የሚቃረን አረዳድ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ይህ ደግሞ ችግሩን ለመፍታት ከባድ ፈተና እንደሆነ ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችም በግራ መጋባትና በግጭት ውስጥ ሕይወትን ለመግፋት መገደዳቸው ነው በቅሬታ የሚነሳው፡፡

በሸዋ ሮቢት ከተማ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ መላከ በላይነህ፣ ‹‹ጦርነቱ በምን እንደሚነሳም ሆነ በምን እንደሚቆም አናውቅም፡፡ በርስት ይሁን በሌላ ይህን ለመጠንቆል እቸገራለሁ፤›› ሲሉ ግጭቱ የፈጠረባቸውን ግራ መጋባት ይናገራሉ፡፡ ለረጅም ዘመናት አብሮ የኖረና ብሔር ወይ ሃይማኖት ሳይለይ ተጎራብቶ የቆየ ማኅበረሰብ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት በድንገት በመሀሉ ከባድ መጨካከንና መገዳደል ሲፈጠር ብዙዎች ግራ መጋባታቸውን ነው አቶ መላከ የሚናገሩት፡፡

‹‹እንዴት እንደሚነሳ አናውቅም፣ በምን እንደሚቆምም አናውቅም፡፡ ጦርነት በየጊዜው ይነሳል፣ ብዙ ንብረትና ሕይወት ካጠፋ በኋላ ይቆማል፡፡ መነሻው ምን እንደሆነ እንኳን አንደ እኔ ያለው ተራ ሰው ቀርቶ፣ በኃላፊነት ላይም ያሉ የሚያውቁት አይመስለኝም፤›› የሚሉት አቶ መላከ፣ ስለዚህ ጉዳይ ከዚህ የተለየ ሐሳብ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡

በዚህ ግራ በገባውና አንዳችም የሰላም ዋስትና በሌለው ሁኔታ ውስጥ ሆኖ መኖር፣ ከሁሉ በላይ ፈታኝ መሆኑንም አስተያየት ሰጪው ያክላሉ፡፡ ‹‹ነገሩ ከእኛ አቅም በላይ ነው፡፡ አብሮ በኖረ ሕዝብ መሀል ጦርነት ይነሳል፡፡ የጦርነቱ ዓላማ ምንድነው ስትል መልስ የለም፡፡ ጦርነቱን ማን ፈለገው ወይም የማን ሥራ ነው ሲባል መልስ የለም፡፡ ስለዚህ ይህን እንደ እኔ ያለው ተራ ነጋዴ ሳይሆን፣ አገር የሚመራው መንግሥት ነው መልስ መስጠት ያለበት፡፡ የልዩ ዞኑና የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ይወያያሉ፡፡ ችግሩን ያውቁታልና መልስ ይስጡበት፤›› በማለት ነው አቶ መላከ ሐሳባቸውን የገለጹት፡፡

ይህን የነዋሪውን ምላሽ በመያዝ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡበት የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደርና የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ባለሥልጣናትን ለማናገር ሪፖርተር ተደጋጋሚ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡

በተደጋጋሚ የስልክ ሙከራዎች ለአጭር ጊዜ ምላሽ የሰጡት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረ ፃዲቅ በበኩላቸው፣ ‹‹የችግሩ መሠረታዊ መነሻም ሆነ ዘላቂ መፍትሔ ጥናት ይፈልጋል፤›› የሚል አጭር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከአቶ ታደሰ ጋር በድጋሚ ለመገናኘት የተደረጉ ጥረቶች ባለመሳካታቸው ከዚህ የተለየ የተብራራ መልስ ማግኘት አልተቻለም፡፡

የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አህመድ ሀሰን በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ተደጋጋሚ ቀጠሮ ቢሰጡም፣ ነገር ግን ምላሻቸው ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ ሆኖም በዘንድሮው ግጭትም ቢሆን ሁለቱ ወገኖች እርስ በርስ ሲካሰሱና ጣት ሲቀሳሰሩ ነው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በሰጧቸው አስተያየቶች የተንፀባረቀው፡፡

የሰሜን ሸዋና የልዩ ዞኑ ቀውስ መሠረት

አካባቢው ሁለት ክልሎችን የአፋርና አማራን የሚያጎራብት ቢሆንም፣ የሚያጋጥመው ተደጋጋሚ ግጭት ግን ሌሎች ክልሎችንም ይስባል ትላለች ስለዚሁ አካባቢ ጥናት ያደረችው ራቨን ሮበርትስ በጥናቷ፡፡ ‹‹Special Zones and Special Histories Conflict and Collaboration in Northren Shewa›› በሚለው ጥናቷ ተመራማሪዋ የተለያዩና ዘርፈ ብዙ የሆኑ ውስብስብ ችግሮች ተደማምረው በቅርቡ ሲደጋገሙ የሚታዩትን የአጣዬና የአጎራባች አካባቢዎች ግጭት እንደፈጠሩ ታስረዳለች፡፡

በንጉሡ ዘመን የሸዋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ የቆየው የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔር አስተዳደር ዞን ከአዲስ አበባ በ350 ኪሎ ሜትሮች የሚርቅ የደሴ ዋና መንገድ መተላለፊያ መሆኑን አፋር ክልልን በቅርብ ርቀት የተጎራበተ ቀጣና ነው ስትል አጥኚዋ ትገልጻለች፡፡ በሃይማኖትና በብሔር ብዝኃነት የሚታወቀው አካባቢው ቆላማና ወይና ደጋ የአየር ፀባይ ያለው መሆኑን፣ ከእርሻ ሥራ በተጓዳኝ አርብቶ አደርነት በሰፊው የሚካሄድበት ቀጣና መሆኑንም ጥናቷ ይጠቅሳል፡፡ ጀወሀ፣ አጣዬ፣ ቦርከናና ጨፋ የተባሉ የታላቁ አዋሽ ወንዝ ገባር የሆኑ ወንዞች የሚፈሱበት ይህ ቀጣና፣ በተለይ ለከብት ግጦሽ ፍለጋ ተደጋጋሚ ግጭቶች የሚቀሰቀሱበት መሆኑን ነው ጥናቷ የሚያስረዳው፡፡

ከምዕራብ አፍሪካ የፈለሱትና የሳውዳኒ ማኅበረሰብን ጨምሮ አርጎባዎች፣ ኦሮሞዎች፣ አፋሮችና አማሮች በንግድና በኢኮኖሚ ተሳስረውና ተጎራብተው ከጥንት ጀምሮ የኖሩበት አካባቢ ነው፡፡ ወደ ጂቡቲ ለመሻገር ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የነበረው የቀደሙ የሸዋ መንግሥታት መዲናም ሆኖ አገልግሏል፡፡ ዛሬ የኦሮሞ ፖለቲካ ልሂቃን አምርረው ቢጠሏቸውም፣ ይሁን እንጂ ለምለሙን የጨፋ ግጦሽ መንደር ለአካባቢው ኦሮሞዎች የሰጡት አፄ ሚኒልክ ነበሩ ሲልም ይኸው ጥናት ያትታል፡፡

በዘመናት ዑደት ብዙ የታሪክ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈው በደብረሲናና በከሚሴ ከተሞች መሀል የሚገኘው ይህ አካባቢ፣ በኢሕአዴግ መንግሥት የብሔር ተኮር ፖለቲካ በአዲስ አደረጃጀቶች ሲዋቀር የተለየ ገጽታን መያዝ ጀመረ፡፡ ራስን መቻል ፈተና የሆነበት አካባቢው ከሕዝብ ቁጥር ዕድገትና ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተዳምሮ በግብርናም ሆነ በአርብቶ አደርነት ኑሮን ማሸነፍ የበለጠ አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ሆኖም መጠነኛ የመሠረተ ልማት ዕድገቶች በአካባቢው የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከጂቡቲ እስከ ወልዲያ የሚዘረጋው የአዋሽ ወልዲያ ባቡር ፕሮጀክት አካባቢውን አቋርጦ ነው የሚያልፈው፡፡ የአካባቢው ወጣት ባህር ተሻግሮ ዓረብ አገር ሠርቶ መለወጥ እንደ አንድ የኑሮ ማሸነፊያ መንገድ መመልከት ጀምሯል፡፡ በአካባቢው ያለው የመስኖ እርሻ መስፋፋት፣ የከተሞች ማደግና የንግድ እንቅስቃሴ መጨመርም አካባቢውን ለውጦታል፡፡

ከሁሉ በላይ ደግሞ የብሔር ፖለቲካና የሃይማኖት መገፋፋት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ፣ የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔር አስተዳደር አካባቢዎችን ነባር ገጽታ በእጅጉ እንደለወጠው ነው የራቮን ሮበርትስ ጥናት በሰፊው ያተተው፡፡

ጀማል ሰይድ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለማስተርስ ዲግሪ ያቀረቡት ‹‹Inter-Ethnic Relations & Conflict Management Between Amhara & Oromo Communities in Ataye Town, North Shoa Zone & Amhara Region›› በሚል ርዕስ የሠሩት የጥናት ውጤት የአካባቢውን መሠረታዊ ችግሮችና የአፈታት መንገዶች በሰፊው ይዘረዝራል፡፡ የብሔር/የዘር ብዝኃነትና ማኅበራዊ መስተጋብር በአንዳንድ አካባቢዎች ፀጋ ወይም ገጸ በረከት ሊሆን ቢችልም፣ በአጣዬና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች ግን በተለይ የአማራና የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ተጎራብቶ ለመኖር እንኳ ፈተና ሆኖባቸዋል ሲል ጥናቱ ያስቀምጣል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 የቀረበው ጥናቱ ከ2018 ጀምሮ በአጣዬ ከተማና በዙሪያዋ ሦስት ጊዜ ግጭቶች ማጋጠማቸውን በማስታወስ፣ የግጭቶቹ ምንጭ ደግሞ ከአካባቢው ውጪ የሆኑ ተፅዕኖዎች ጭምር መሆናቸውን ያብራራል፡፡

የጀማል ሰይድ ጥናት ግጭቶቹ በተደጋጋሚ መፈጠራቸው በአካባቢው ላይ ያስከተለውን ከባድ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ከሁሉ በላይ ሰብዓዊ ውድመቶች ለማከም ፈተና እንደሆነ ጭምር ያትታል፡፡ ግጭቶች ሲፈጠሩ የፌዴራልና የክልል ፀጥታ ኃይሎች ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርጉም፣ ብዙ ጊዜ አንፃራዊ ሰላም የሚሰፍነው ግን በአካባቢ ሽማግሌዎች በሚደረጉ ጥረቶች መሆኑን ያትታል፡፡ አጥኚው ከዚህ ተነስተው ለአካባቢው ይበጃል የሚሉትን ምክረ ሐሳብ ሲያቀርቡም፣ ‹የአካባቢውን የሽምግልና ዕርቅ ተቋማዊ ማድረግ ጠቃሚ ነው› ይሉታል፡፡ ጀማል ሰይድ ከዚህ በተጨማሪም ከሁለቱ ዞኖች ማለትም ከኤፍራታና ግድብ ወረዳ፣ እንዲሁም ጅሌ ጥሙጋ (ኦሮሞ ብሔራዊ አስተዳደር ዞን) የተውጣጣ አካባቢያዊ የሆነ የጋራ ፀጥታ ኃይል ያስፈልጋል ሲሉ በመፍትሔነት አስቀምጠዋል፡፡

የሰሜን ሸዋ ግጭት በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ ሥምሪት አለመብረዱ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ቀደም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአካባቢው ተደንግጎም የፀጥታ ማስከበር ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ሁሉ ዘላቂ መፍትሔ ስለማስገኘቱ ያጠራጥራል፡፡ ልክ እንደ ዓምናና ካቻምናው ሁሉ አጣዬ፣ ሸዋሮቢት፣ ከሚሴ፣ ሞላሌ፣ ወዘተ እያለ ግጭቱ የአካባቢውን ከተሞችና ቀበሌዎች በዙር እያደረሰ አሁንም ድረስ ዘልቋል፡፡

ያሬድ ብቻ በሚለው ስሜ ልጠራ ያለው የሸዋሮቢት ከተማ ነዋሪ ስለዚህ ግጭት ምልከታውን ሲያጋራ፣ ‹‹በእኔ ዕድሜ አካባቢው ይህን ዓይነት ግጭት ሲያስተናግድ አላስታውስም፤›› በማለት ይናገራል፡፡ ‹‹ለውጥ መጣ አዲስ መንግሥት ሥልጣን ተረከበ ከተባለ ጊዜ ወዲህ ግን ነገሮች በፍጥነት ተለወጡ፡፡ ግጭትም በአካባቢያችን በረከተ፤›› ሲል ወጣቱ የሸዋሮቢት ነዋሪ ሐሳቡን አጋርቷል፡፡

‹‹ኦነግ ሸኔ ከኤርትራ በረሃ ሲገባ በዚህ አካባቢ ትጥቁን ሳይፈታ የቀረ ኃይል ነበር፡፡ በአካባቢው የብሔር ፖለቲካን ተመርኩዘው የተለያዩ አደረጃጀቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ተፈጠሩ፡፡ የጥላቻ ትርክቶችና የማኅበራዊ ሚዲያዎች ቅስቀሳዎች ታክለውበት፣ አካባቢያችን በተደጋጋሚ በግጭት የሚታመስ ቀጣና ሆኗል፤›› ሲል ያሬድ ይናገራል፡፡ በእሱ እምነት የብልፅግና ፓርቲ የአማራና የኦሮሚያ ብልፅግና ቅርንጫፎች ተቀምጠው በችግሩ ዙሪያ ካልተነጋገሩና የጋራ መፍትሔ ካላፈለቁ በስተቀር፣ የሰሜን ሸዋ ቀጣና ከግጭት ሊላቀቅ አይችልም፡፡

የሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔራዊ አስተዳደር ዞን ተጎራባች ወረዳዎችና ቀበሌዎች ግጭቶች ባለፉት ሦስት ዓመታት ያስከተሉት ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ግጭት እየተባባሰ የመጣው በአካባቢው ባሉ ታጣቂዎች፣ በተለይም ኦነግ ሸኔ በሚባለውና በአገሪቱ ፓርላማ በሽብርተኝነት በተፈረጀው ኃይል እንቅስቃሴ መስፋፋት መሆኑን የሚናገሩ ወገኖች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች መፍትሔ ይፈልጉ ብለው የጠቆሟቸው የኦሮሚያና የአማራ ብልፅግና ቅርንጫፎች በዚህ ላይ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው የጋራ መፍትሔ ይፈጥራሉ የሚለው ጥያቄ ግን፣ አሁንም  በእንጥልጥል ላይ መሆኑን ነው ብዙዎች የሚስማሙት፡፡

በሕወሓት ወረራ ክፉኛ የተደቆሰው ይህ አካባቢ ከራሱ የችግር ምንጮች በተጨማሪ ውስብስብ ቀውሶች እንደተደራረቡበት ነው የአካባቢውን ሁኔታ የሚታዘቡ የሚያስቀምጡት፡፡ ሕወሓት ሲወረው በአካባቢው የተፈጠሩ ችግሮች ተጨማሪ የቁርሾ ምንጭ ሆነዋል፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀም ከሕወሓት ጋር ለመተባበር ወደ እዚህ ቀጣና የገቡ የታጣቂ አደረጃጀቶች የአካባቢውን ችግር የበለጠ አወሳስበውታል የሚሉ አሉ፡፡

ለነዚህም ሆነ ለነበሩ ችግሮች መፍትሔ ሳያገኝ በተደጋጋሚ ግጭት የሚታመሰው የሰሜን ሸዋና ኦሮሞ ልዩ ዞን ግጭት ጦሱ ለአገር ጭምር እየተረፈ ነው ይባላል፡፡ በዚህ ቀጣና ኮሽ ባለ ቁጥር ዋናው የአዲስ አበባ ደሴ መንገድ በተደጋጋሚ ይዘጋል፡፡ ከግጭቱ ብዙ ርቀው ያሉና ምንም ግንኙነት የሌላቸው ጭምር፣ የአካባቢው ቀውስ በተዘዋዋሪ ሰለባ እያደረጋቸው ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡