የቅማንት እና የጉሙዝ ታጣቂዎች በቤንሻንጉልና አማራ አዋሳኝ ቦታዎች ጥቃት ፈፀሙ

ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ዳንጉር ወረዳና በአማራ ክልል ቋራ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች ታጣቂዎች ጥቃት ማድረሳቸውን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የቋራ ወረዳ አስታወቀ ፣ የወረዳው አስተዳደር “ከህወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው” ያላቸው ታጣቂዎች ጥቃቱን ፈፅመዋል ብሏል፡፡ የቋራና የዳንጉር ወረዳ የፀጥታ አካላት በጋራ ባደረጉት ኦፕሬሽን ታጣቂዎችን ከአካባቢው እንዲሸሹ አድርገዋልም ተብሏል፡፡

አንድ የዓይን እማኝ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት በእለተ ፋሲካ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዳንጉር ወረዳንና በአማራ ክልል በኩል ቋራ ወረዳን በሚያገናኘው “ዓይማ” ወንዝ አካባቢ ታጣቂዎች ተኩስ ከፍተው ሰላማዊ ሰዎችን አቁስለዋል::

ታጣቂዎቹ የቡድን መሳሪያ ይዘው በቤኒሻንጉል ክልል ዳንጉር ወረዳ ዓባይ ዳር ቀበሌና በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ ባምባሆ ቀበሌዎችን ለማጥቃት መንቀሳቀሳቸውን የቋራ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ይርዳው ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና አስተዳዳሪው ታጣቂ ኃይሉን ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ወረዳ የፀጥታ አካላት ጋር ከአካባቢው እንዲርቅ ማድረጋቸውን አመልክተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የዳንጉር ወረዳ አስተዳዳሪ አስተያየት እንዲሰጡኝ ሞክሬ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

የቅማንት ዴሞክራሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አውግቸው ማለደ “ ’የቅማንት ፅንፈኛ’ እየተባለ በየጊዜው በመንግስት የሚነገረው ወቀሳ የተለመደ ታርጋ የመስጠት አባዜ ነው” ብለውታል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚመለከታቸውን የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና “የጉሙዝ ታጣቂዎች“ የተባሉ ተወካዮችን አስተያየት በስልክ ለማካተት ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም፡፡