ከሰው ተኳርፈው፣ አምጸው፤ ባርነትን ጠልተው/ በጦርነት ተበትነው/ ለ500 ዓመት በቁንድዶ ተራራ ኤጀርሳ ጎሮ የኖሩት የዱር ፈረሶች

የቁንድዶ ፈረሶች እንደመናኛ ያረጀ ፈረስ የትም አይጣሉም፡፡ ጀግና ፈረሶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እንጂ ዓለም ላይ የትም የሉም፡፡

ጊዜው እንዴት ይጋልባል! BBC Amharic

የቁንድዶ ፈረሶች እንደመናኛ ያረጀ ፈረስ የትም አይጣሉም፡፡ ጀግና ፈረሶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ እንጂ ዓለም ላይ የትም የሉም፡፡ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ቁንድዶ ተራራ ላይ ይዞን ከወጣ ድፍን 13 ዓመት።

“የጋዜጠኛው ማስታወሻ!”

በዚህ መጽሐፉ 31 ታሪኮች ተሰድረው ነበር። 12ኛው ታሪክ ግን አይረሳም። ቱባ ታሪክ።

በብዙ አንባቢዎች የአእምሮ ጓዳ እንደ ካራማራ ገዝፎ የተቀመጠ ታሪክ።

ያውም እኮ የሰው ታሪክ አይደለም። የፖለቲካ ሐሜትም አልነበረም። የፈረሶች ታሪክ ነው። ፈረስ ቢሏችሁ…የጋሪ ፈረስ ነው እንዴ?

አይደለም!

“አሁንስ የሰው ልጅ አበዛው! እንዳሻው አይጋልበንም” ብለው ያመጹ ፈረሶች ታሪክ።

የሰው ልጆች ንብረት እንደነበሩ ፈጽሞ ስለረሱ አስገራሚ ፈረሶች የሚያወሳ የጉዞ ማስታወሻ።

በሰው ልጆች የባርነት ቀንበር ከመኖር፣ ፍግም ብሎ መሞትን የመረጡ ፈረሶች…የወል ታሪክ።

ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ያን ተራራ የወጣው፣ ‘አንድ እንደ ብረት የጠነከረ ክንድ ባለው የኤጀርሳ ጎሮ ገበሬ’ እና ሌሎች ሦስት አንጋቾች በልዩ ሁኔታ ተመድበውለት ነበር።

ደግነቱ በአንጋች ታጅቦ ወጥቶ ባዶ እጁን አልተመለሰም። ቧጦ የወጣውን ተራራ ቧጦት ሲወርድ ቱባ ታሪክ ይዞ ነበር የተመለሰው።

በአጭሩ፣ የቁንድዶ ፈረሶችን በተባ ብዕሩ ህያው አደረጋቸው።

ተስፋዬ ገብአብ

የፎቶው ባለመብት, Tesfaye gbreabe/fb

የዛሬ 13 ዓመት እሱ ሲጎበኛቸው በግምት 50 አካባቢ ነበሩ። እሱ ሲጠፋ እነሱም ጠፉ። ከዓመታት በኋላ ተመናምነው 7 ቀሩ። አሁን በብዙ ጭንቅ 28 ደርሰዋል እየተባለ ነው። እውነት ከሆነ ተመስገን ነው!

ገና ከተራራ መውረዳችን ነው። ደግመን ተራራውን መውጣታችን አይቀርም። እዚህ ጋ አረፍ እንበልና አንድ ቀላል ጥያቄ እናንሳ፡-

የፈረሶቹ ቁጥር ለምን ያሳስበናል? ሕያውነታቸው ለምን ግድ ይለናል? ደግሞ ለዱር ፈረስ! ሲሻቸው ለምን ፍግም አይሉም! ደግሞ ስለፈረስ ልጨነቅ እንዴ!?

በእርግጥ እንዲያ ካሰብን ተሳስተናል።

የቁንድዶ ፈረሶች እንዲህ አይባሉም።

የቁንድዶ ፈረሶች እንደመናኛ ያረጀ ፈረስ የትም አይጣሉም። ጀግና ፈረሶች ናቸው።

ለካንስ ቁንድዶዎች በኢትዮጵያ እንጂ ዓለም ላይ የትም የሉም።

ለካንስ አንጡራ የኢትዮጵያ ሀብት ናቸው። እንደ ቀይ ቀበሮ፣ እንደ ዋሊያ…።

ለካንስ ነገሮች ቢመቻቹላቸው በየዓመቱ ሚሊዮን ዶላሮችን ለኢትዮጵያ የሚያስገኙ ‘የጋማ ነዳጆች፣ የተራራ ወርቆች’ ናቸው።

እኛ ይሄን መቼ አወቅን? ማንስ ነገረን?

ነገሮች ቢመቻቹላቸው በየዓመቱ ሚሊዮን ዶላሮችን ለኢትዮጵያ የሚያስገኙ ‹የጋማ ነዳጆች፣ የተራራ ወርቆች› ናቸው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Kefena Effa

የምስሉ መግለጫ, ነገሮች ቢመቻቹላቸው በየዓመቱ ሚሊዮን ዶላሮችን ለኢትዮጵያ የሚያስገኙ ‹የጋማ ነዳጆች፣ የተራራ ወርቆች› ናቸው፡፡

በቁንድዶ ፈረሶች ላይ ፒኤችዲ የሠሩት ኢትዮጰያዊ ምሁር

ዶ/ር ከፈና ኢፋ፣ ደራሲ ተስፋዬ ገብረ አብ ይህን መጽሐፍ ሲያሳትም ሐሮማያ ነበሩ።

ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለመሥራት ደፋ ቀና የሚሉበት ዋዜማ ነበር።

“…ዕሴት የሚጨምር፣ ብዙም ባልተዳሰሰ ርዕሰ ጉዳይ ጥናቴን ብሠራ እያልኩ እመኝ ነበር” ይላሉ፣ ዓመታትን ወደ ኋላ በሐሳብ ጋልበው።

ሐሳባቸውን ለያኔው የዓለማያ ዩኒቨርስቲ አማካሪያቸው ለፕሮፌሰር መሐመድ ዩሱፍ ይነግሯቸዋል።

ፕሮፌሰር መሐመድ በበኩላቸው ተስፋዬ ገብረ አብ ስለጻፈው አንድ ጉዳይ ያጫውቷቸዋል። ስለ ቁንድዶ ፈረሶች።

“እኔ ያኔ በዱር የሚኖር ፈረስ እንዳለ በጭራሽ አላውቅም ነበር። ተስፋዬ ነው መነሻ የሆነኝ” ይላሉ።

ከዚያ ምን ሆነ?

“ስለ ፈረሶቹ እንደሰማሁ ሁሉን ነገር ጥዬ ወዲያውኑ ወደ ጉርሱም ሄድኩኝ። ቁንድዶ ተራራን ወጥቼ አየኋቸው። እውነት እንደሆነ አረጋገጥኩ። መነሻ ሐሳብ ጻፍኩኝ። አማካሪዎቼ ማመን አልቻሉም። ነገሩ በቃ ፌሽታ ነበር ማለት ይቻላል” ሲሉ ወቅቱን ያስታውሳሉ።

ዶ/ር ከፈና ረቂቅ ሐሳቡን ይዘው ሦስተኛ ዲግሪ ሊሠሩ ወዳሰቡበት አገር ፖርቹጋል አቀኑ። በዚያም ተመሳሳይ ስሜት ነበር የጠበቃቸው።

“ፈረንጆቹ የዱር ፈረሶቹን ታሪክ ለማመን ስለከበዳቸው ሽሚያ ውስጥ ገቡ፤ ሁሉም ፕሮፌሰሮች ከኔ ጋር ሥራ፣ ከኔ ጋር ሥራ የሚል ሽሚያ ያዙ…።”

ቁንድዶ ተራራ የሚገኘው በኤጀርሳ ጎሮ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልልና በሶማሌ ክልል ድንበር የሚገኝ ረዥም አስደናቂ ተራራ ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Kefena Effa

የምስሉ መግለጫ, ቁንድዶ ተራራ የሚገኘው በኤጀርሳ ጎሮ ነው። በኦሮሚያ ክልልና በሶማሌ ክልል ድንበር የሚገኝ ረዥም አስደናቂ ተራራ ነው፡፡

ሁለት ዓመት ተኩል በቁንድዶ ተራራ

ዶ/ር ከፈና ሦስት ዓመት ከ10 ወራትን በፈጀው በዚህ የፒኤችዲ ጥናት፣ 2 ዓመት ተኩሉን ያሳለፉት ከቁንድዶዎቹ ሰፈር እየተመላለሱ ነው።

ቁንድዶ ተራራ የሚገኘው በኤጀርሳ ጎሮ ነው። በኦሮሚያ ክልልና በሶማሌ ክልል ድንበር የሚገኝ ረዥም አስደናቂ ተራራ ነው።

ለዶ/ር ከፈና ያን ተራራ እንደ ዝንጀሮ እየቧጠጡ መውጣት መውረድ አድካሚ ነበር። ከፈረሶቹ የዘረ-መል ናሙና መውሰዱም ሌላው ፈተና።

ምክንያቱም ፈረሶቹ የዱር ናቸው። ከሰው ልጆች ጋ ቋሚ ጠብ ላይ ያሉ ይመስላል። እነሱን ለመጠጋት ከፍተኛ ጥንቃቄን ይሻል።

“ናሙና ለመውሰድ ራሱ መጀመርያ ፊታቸውን ሸፍነን፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው፤ አደገኞች ናቸው፤ ይናከሳሉ።”

ለነገሩ ተስፋዬ ገብረአብም በመጽሐፉ ያን መስክሯል።

የኤጀርሳ ጎሮ ገበሬዎች ወደ ተራራው ይልኳቸው የነበሩ ማቲ እረኞች ሳይቀሩ በፈረሶቹ ይነከሱ፣ ይገደሉም እንደነበረ ጽፏል።

ተስፋዬ በዚያ ትረካው ስለ ቁንዱዶ ፈረሶች ባህሪ ይህን ብሎ ነበር።

“…አመጸኛ ናቸው፤ ሰዎችን ሲያዩ ማንፏረር፣ ጆሮ መቀሰር፣ ለጸብ መጋበዝ ይቀናቸዋል…።” (የጋዜጠኛው ማስታወሻ)

ዶ/ር ከፈናን፣ ይህ ገለጻ በደራሲው ብዕር በከፊል ፈጠራ የተለወሰ ግነት ይሆን? ስንል ጠየቅናቸው። እንዳልተጋነነ ነገሩን።

ደራሲ ተስፋዬ ከባህሪያቸው ባሻገር ስለ ፈረሶቹ ተክለ ሰውነት ይህን ብሎ ነበር።

“…ኮረብታ ያክላሉ፣ ታፋቸው እንደ ማዕበል ይገለባበጣል። ቆዳቸው ወዛም ነው፤ ያብረቀርቃል። ቁስላምና የዝንብ መጫወቻ አይደሉም…።” (የጋዜጠኛው ማስታወሻ፤163)

ዶ/ር ከፈና በዚህ ገለጻውም ቢሆን ከሞላ ጎደል ይስማማሉ።

“ትክክል ነው፤ በጣም ግዙፍ ናቸው። ጋማቸው ከአንገታቸው ወደታች ተንጠልጥሎ ነው ያለው። እንዲሁ ግርማ ሞገስ አላቸው። ግልገሎቹ ራሱ ግዙፍና ንቁ ናቸው። ድምጽ ከሰሙ ጆሯቸውን ይቀስራሉ። ጠላትን በደቦ መከላከልን ያውቃሉ።”

ዶ/ር ከፈና እንደሚገምቱት ይህ ንቃታቸው ለዘመናት በዱር ከመኖር የመጣ ሊሆን ይችላል። ከነብርና ከጅብ ሲተናነቁ ነዋ የኖሩት።

አካባቢያቸውን ሲጠራጠሩ ደግሞ እርስ በእርስ ተጠራርተው በአንድ ይቆማሉ። ኅብረታቸው አስደማሚ ነው።

“ከተጠጋሃቸው ሊነክሱህ ይችላሉ። ዕድሜ ዘመናቸውን የኖሩት በዱር ነዋ። የዱር ባህሪም ነው ያላቸው። ቁጡ ናቸው። ብቻ የሚገርም ተፈጥሮ ነው የምታይባቸው” ይላሉ ዶ/ር ከፈና።

"ናሙና ለመውሰድ ራሱ መጀመርያ ፊታቸውን ሸፍነን፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው፤ አደገኞች ናቸው፤ ይናከሳሉ፡፡"

የፎቶው ባለመብት, Kefena Effa

የምስሉ መግለጫ, “ናሙና ለመውሰድ ራሱ መጀመርያ ፊታቸውን ሸፍነን፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው፤ አደገኞች ናቸው፤ ይናከሳሉ፡፡”

ከኤጀርሳ ጎሮ እስከ ፖርቹጋል-ፖርቶ

ዶ/ር ከፈና ከፈረሶቹ ጋር ያሳለፉትን ጊዜ “በሕይወቴ እጅግ የምወደው ጊዜ ነው” ይላሉ። ለዚያም ይሆናል ድካሙ ያልተሰማቸው።

አንድ ጊዜ ናሙና ሲሰበስቡ፤ ሌላ ጊዜ ናሙናውን ይዘው ፖርቹጋል ሲከንፉ፣ እንደገናም ለሌላ ናሙና ኤጀርሳ ጎሮ ሲመለሱ፣ እንደገና ቁንድዶ ተራራን ሲቧጥጡ…።

እንዲህ ነበር የዶ/ር ከፈና 2 ዓመት ከ10 ወራት እ…ልም ያሉት።

ይህ የእርሳቸው ብቻ ስሜት አልነበረም። በዩኒቨርስቲ ኦፍ ፖርቶ ጥናታቸው ያማክሯቸው የነበሩትም ፕሮፌሰሮች እንዲያ ነበሩ።

“…እጅግ እጅግ በጣም ነው የተገረሙት። እንዲህ ዓይነት የዱር ፈረሶች ይኖራሉ ብለው በፍጹም አልጠበቁም። ለእነሱ ተአምር ነው የሆነባቸው” ይላሉ በዚያ ያለውን ስሜት ለቢቢሲ ሲያስረዱ።

ለመሆኑ ቁንድዶዎች ይህን ያህል ለምን አነጋጋሪ ሆኑ?

ዶ/ር ከፈና እንደሚሉት የዱር ፈረስ በሌሎች ዓለማት እምብዛምም አይታወቅም። በአፍሪካ፣ ምናልባት ናሚቢያ ውስጥ እንዳለ ብቻ ነው የሚገመት።

ሌላው ምክንያት ደግሞ ፈረሶቹ ዝርያቸው የትም አለመኖሩ ነው። ከየት እንደመጡ እስከዛሬም ምሥጢር መሆኑ ነው።

ይህ እንቆቅልሽ አለመፈታቱ ፈረሶቹን ልዩ ያደርጋቸዋል።

ስለ ቁንድዶ ፈረሶች እስከዛሬም ብዙ መላምቶች እንጂ አንድ ዕውነት ላይ አልተደረሰም።

የቁንድዶ ፈረሶች የግራኝ አሕመድ ፈረሶች ይሆኑ?

ዶ/ር ከፈና በአጠቃላይ ፈረሶች ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር እንዴት ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ያስረዳሉ።

ከግራኝ አሕመድ እስከ አድዋ ድረስ ነገሥታት ያለ ፈረስ አይታሰቡም።

ይህ በታሪክም ተጽፎ ያለ ነው።

ፈረሶች ለድሮ ሥርወ መንግሥታት ‘ድሮኖች’ እንደማለት ነበሩ ብለን ነገሩን ልናደምቀው እንችላለን።

ነገሥታትና ፈረሶቻቸው በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ እንኳ ጥብቅ ናቸው። አባ ታጠቅ፣ አባ ኮስተር፣ አባ ጤና፣ አባ ሻንቆ፣ አባ ዳኘው፣ አባ በዝብዝ እያልን ነገሥታቱን ሁሉ፣ አርበኛውን ሁሉ በፈረሶቻቸው ልንወክል እንችላለን።

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ገነው ከሚወሱ የፈረስ ዝርያዎች መካከል ደግሞ፣ የሰላሌ ፈረስ እና ዊልዋል የሚባሉት የሶማሌ ፈረሶች ይወሳሉ። ሁለቱም የግልቢያ ፈረሶች ናቸው።

ቁንድዶዎች ታዲያ ከየት መጡ? ለምንስ የዱር ፈረስ ሆኑ? እውነት ከሰው ልጆች ተኳርፈው ነው?

የዶ/ር ከፈና አጭሩ መልስ “አይታወቅም!” የሚል ነው። ነገር ግን መላምቶችን ሳያስቀምጡ አላለፉም።

የመጀመሪያው መላምት ፈረሶቹ የጦር ፈረስ ስለመሆናቸው የሚያረጋግጥ ነው። ይህም ከባህሪያቸው ይነሳል።

“አንዱና ልዩ ባህሪያቸው ሲንቀሳቀሱ ኮሽታ አያሰሙም። ወላ ሌሊት ራሱ ኮቴያቸውን አይሰማም። ይህ ደግሞ የጦር ፈረስ ባህሪ ነው።”

ከዚህ በመነሳት ምናልባት የነዚህ ፈረሶች ምንዥላቶች የጦር ፈረሶች እንደነበሩ ጥርጣሬን ፈጥሯል።

እሺ፣ የጦር ፈረስ መሆኑንስ ይሁኑ፤ ነገር ግን ከየት መጡ? እንዴት የዱር ፈረስ ሊሆኑ ቻሉ?

ተስፋዬ ገብረአብ ከሰው ተኳርፈው፣ አምጸው፤ ባርነትን ጠልተው… ይለናል።

ዶ/ር ከፈና በዚህ የደራሲው መላምት በጭራሽ አይስማሙም። ቆይ ምክንያታቸውን ወደ በኋላ ያስረዱናል።

አሁን ወደ ሁለተኛው መላምት እንለፍ፡-

ሁለተኛው የዶ/ር ከፈና መላምት የሆነ ዘመን በነበረ አንድ ትልቅ ጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ የዋሉ ፈረሶች ናቸው የሚል ነው።

ለዚህ መላምት ያበቋቸውን ምክንያቶችንም ጠቅሰዋል።

አንዱ እነሱ የሰፈሩበት ተራራ (ቁንድዶ) ለጦርነት የተመቸ፣ ግዢ (ስትራቴጂክ) የሚባል መሆኑ ነው።

ሁለተኛው አስደናቂ ነገር ደግሞ ይህን ተራራ አንዳንዶች አሁንም ድረስ ከሰሜን እየመጡ ቦታውን እንደ ማምለኪያነት መጠቀማቸው ነው።

“ይሄ ለምን ሊሆን ቻለ? ብለን እንደ አንድ የምርምር ጥያቄ ወሰድነው” ይላሉ ዶ/ር ከፈና።

ከዚህ በመነሳት ነው ወደ ሦስተኛው መላምት የሚሄዱት።

ወደ ግራኝ አሕመድ ጦርነት።

ፈረሶቹ ዝርያቸው የትም የለም፡፡ ከየት እንደመጡ እስከዛሬም ምሥጢር ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Kefena Effa

የምስሉ መግለጫ, ፈረሶቹ ዝርያቸው የትም የለም፡፡ ከየት እንደመጡ እስከዛሬም ምሥጢር ነው፡፡

የዐጤ ገላውዲዮስ ፈረሶች ይሆኑ?

ይህን አፈ ታሪክ ለመረዳት የኢትዮጵያን መካከለኛው ዘመን ታሪክ በሽውታ ማለፍ ግድ ይለናል።

በዐጤ ልብነ ድንግልና በግራኝ አሕመድ መካከል የተደረገ የ30 ዓመታት ጦርነት ነበር።

ሽምብራ ኩሬ ላይ ልብነድንግል በግራኝ ተሸነፉ። በዚያ ጦርነት ግራኝ 16 ሺህ ፈረስ አሰልፎ ነበር ይባላል። አነዚያ ፈረሶች የቁንድዶ ፈረሶች ይሆኑ እንዴ?

የልብነ ድንግል ልጅ ገላውዲዮስ ትግሉን ቀጠለ። ግራኝ አሕመድ በወይን አደጋ ጦርነት ጣና ሐይቅ አካባቢ ተገደለ።

የልብነ ድንግል ጦር የግራኝን ጦር ገፍቶ ሐረር አደረሰው።

ባቲድል ወንበሬ ትባል የነበረችው የግራኝ ሚስት ግን ቂም ይዛ ነበር። የባሏን ሞት መበቀል ትመኝ ነበር።

በዚያው ሰሞን ከግራኝ ዘመድ የታገቢኛለሽ ጥያቄ ቀረበላት። ምናልባት ኑር ኢብን ሙጃሂድ ሳይሆን አይቀርም ይህን ጥያቄ ያቀረበው።

የዐጤ ገላውዲዮስን አንገት ቆርጠህ ካመጣህ ብቻ አገባኻለው አለችው።

ይህ ሰው ፍልሚያ ገባ። ቃሉን ጠበቀ። የአጤ ገላውዲዮስን አንገት ቆርጦ አመጣላት።

በዚህ ወቅት ከባድ ጦርነት የተደረገው ምናልባትም በቁንድዶ ተራራ ላይ ነበር።

የገላውዲዮስ አንገት ሲቀላ ምናልባት እዚያ ተራራ ላይ የነበሩ የገላውዲዮስ ፈረሰኛው ጦር እግሬ አውጪኝ ብሎ ሳይበታተን አልቀረም።

ወታደሩ ፈረሶቹን ጥሎ ከተራራው ሲያመልጥ ፈረሶቹ የት ይሂዱ? ቁንድዶ ተራራ ላይ እንደወጡ ቀሩ።

ይሄ እንደ ተራራው የተንዥረገገ አፈ ታሪክ የአካባቢው ሽማግሌዎች የሚያወሩት ነው።

ይህን መላምት ከተቀበልን፣ እነዚህ ፈረሶች ለ500 ዓመት በቁንድዶ ተራራ ኖረዋል ማለት ነው።

በዚህ ረዥም ዘመን የራሳቸውን ግዛት ፈጥረዋል። ከተፈጥሮ ጋር ታግለዋል። ዝግመተ ለውጥን ተቀብለዋል ማለት ነው።

ቅማያት፣ ምንዥላታቸው ለማዳ የጦር ፈረስ ቢሆንም በመቶ ዓመታት ቆይታ ዱር ቤት ብለዋል ማለት ነው።

ዶ/ር ከፈና ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር የማይስማሙት እዚህ ላይ ነው።

ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ፈረሶቹ ከሰው ልጆች ባርነት ያመጹ ናቸው ብሎ ሊያሳምነን ይሞክራል።

ዶ/ር ከፈና ግን ይህ በጭራሽ የሚያስኬድ ሐሳብ አይደለም ይላሉ።

ምክንያታቸውን ሲያስረዱም አንደኛ ፈረሶቹ በምንም ተአምር ያን ተራራ በራሳቸው ሊወጡት አይችሉም። ተራራውን እንዲወጡ ካልተገደዱ በስተቀር።

“ለፈረስ አይደለም እኛ ራሱ ቧጠን ወጥተን፣ ቧጠን ነው እኮ የምንወርደው” ይላሉ የተራራውን አስቸጋሪነት ሲያብራሩ።

በራሳቸው ካልወጡት፣ የሆነ ሰው ይዟቸው ወጥቷል ማለት ነው። ምናልባትም የገላውዲዮስ ወታደሮች።

“ምን መሰለህ! ፈረሶች ከዕለታት አንድ ቀን ከሰው ልጅ አምልጠው ተራራ ላይ ሊወጡ አይችሉም። ተስፋዬ ምናልባት ታሪኩን ለፖለቲካ ይዘት ተጠቅሞት ይሆናል እንጂ በምንም ዓይነት የቁንድዶ ፈረሶች ከሰው አምልጠው ተራራ ወጥተው ሊሆን አይችልም” ይላሉ ዶ/ር ከፈና።

ዶ/ር ከፈና ሦስት ዓመት ከ10 ወራትን በፈጀው በዚህ የፒኤችዲ ጥናት፣ 2 ዓመት ተኩሉን ያሳለፉት ከቁንድዶዎቹ ሰፈር እየተመላለሱ ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Kefena Effa

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ከፈና ሦስት ዓመት ከ10 ወራትን በፈጀው በዚህ የፒኤችዲ ጥናት፣ 2 ዓመት ተኩሉን ያሳለፉት ከቁንድዶዎቹ ሰፈር እየተመላለሱ ነው፡፡

ከቁንድዶ ፈረሶች ኢትዮጵያ ምን ታተርፋለች?

ዶ/ር ከፈና ደጋግመው እንዲህ ይላሉ። “እኛ ኢትዮጵያዊያን ሀብታችንን አናውቀውም፣ ብናውቀውም ታቅፈነው ተኝተናል…”

የቁንድዶ ፈረሶች ትልቅ ሀብት እንደሆኑ በቁጭት ይናገራሉ።

ቁንድዶዎቹ ፈረሶች በሌላ ዓለም ቢሆኑ የቱሪስት ጎርፍ ሊከሰት ይችል እንደነበር ያብራራሉ።

“ፈረንጆች እንኳንና እንዲህ ዓይነት ለማመን የሚያስቸግር ተፈጥሮን አግኝተው አይደለም፣ ትንሿን ነገር እኮ ነው አዳንቀው፣ የሚዲያ ሞቅታ ፈጥረው ታሪክ የሚሠሩበት…”

ከዚህ ሌላ ፈረሶቹ የዘረ-መል (ጄኔቲክ) ሀብት ናቸው ይላሉ። ዱር ስለኖሩ ብዙ የተለየ አቅምና ብቃት አላቸው። በሽታን ይቋቋማሉ። ቢዳቀሉ ሌላ ትልቅ ሀብት ነው የሚፈጥሩት።

ከሰሞኑ ጥሩ ዜና ተሰምቷል። ቢዘገይም ቁንድዶዎች አስታዋሽ አግኝተዋል።

በቅርቡ ሦስት ተቋማት አብረው ሊንከባከቧቸው ተስማምተዋል።

የኢትዮጵያ ብዘኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት፣ የኦሮሚያ የአካባቢ ጥበቃ፣ ደንና አየር ንብረት ባለሥልጣን ከሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ጋር አንድ ሰነድ ተፈራርመዋል።

በቀጣይ አሥር ዓመት ፈረሶቹን ተንከባክቦ ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ነው ውጥኑ።

ይህ ከተሳካ ጃርሶና ጉርሱም ወረዳዎች ሺህ ጎብኚዎች የሚሽሎከለኩባቸው ሊሆኑ ይችላሉ።

ኤጀርሳ ጎሮ ሌላ አክሱም፣ ሌላ ላሊበላ፣ ሌላ ኤርታሌ ሆነ ማለት ነው።

“ቁንድዶ የሚገርም ተራራ ነው። ተራራው ጫፍ ላይ ውሃ አለ። አረንጓዴ ነው። እንደ ወንጪ ሐይቅ ነው። ተፈጥሮ ራሱ እንዴት እንደዚህ እንደጠበቀችው ይደንቀኛል” ይላሉ ተመራማሪው።

“ሀብታችንን አናውቀውም፣ ብናውቀውም ተኝተንበታል” የሚሉት ዶ/ር ከፈና አሁን የሆለታ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ናቸው።

እሳቸው የቁንድዶ ፈረሶችን በተመለከተ የጥናት ውጤታቸውን በስመጥር ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ማሳተማቸውን ተከትሎ ዕውቅ ሳይንቲስቶች ለነገሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው እየደወሉላቸው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዱር ውስጥ የሚኖሩ ፈረሶች ማለት ለዓለም ተአምር ነው የሚሉት ዶክተሩ፣ በሚገባ ከተዋወቀ በእርግጠኝነት በኢትዮጵያ ትልቅ የቱሪስት መዳረሻ ይሆናል ይላሉ።

ዶ/ር ከፈና ኢፋ አሁንም መላልሰው እንዲህ ይላሉ፡-

“እኛ በእጃችን ያለውን ሀብት አናውቀውም እኮ፣ ብናውቀውም ተኝተንበታል።…”

በጣም ግዙፍ ናቸው፡፡ ጋማቸው ከአንገታቸው ወደታች ተንጠልጥሎ ነው ያለው፡፡ እንዲሁ ግርማ ሞገስ አላቸው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Kefena Effa

የምስሉ መግለጫ, በጣም ግዙፍ ናቸው፡፡ ጋማቸው ከአንገታቸው ወደታች ተንጠልጥሎ ነው ያለው፡፡ እንዲሁ ግርማ ሞገስ አላቸው፡፡