ትግራይ ውስጥ በአየር ጥቃት ከ100 በላይ ተገድለዋል – ተመድ

ከታኅሣስ ወር መጨረሻ ቀናት ወዲህ እስካሁን ባለው ጊዜ ትግራይ ውስጥ በአየር ጥቃት ቢያንስ 108 ሰዎች ተገድለዋል ሲል የባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አመለከተ። በአየር ጥቃት ሌሎች 75 ሰዎችም መጎዳታቸውን ገልጿል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኦቻ ባወጣው ዘገባ ሰብዓዊ ቀውስ በአካባቢው አንዣቧል ሲልም አሳስቧል። ወታደራዊ ያልሆኑ ቦታዎች የጥቃት ኢላማ ሆነዋል ያለው ድርጅቱ አክሎም የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የሲቪሎችን ደህንነት እንዲያረጋግጡም ተማጽኗል። የድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳይ ዘርፍ ቃል አቀባይ ሊዝ ትሮስል የተጎዱ ሲቪሎች እና ንብረቶችን የሚያመላክቱ ዘግናኝ ዘገባዎች እንደሚደርሷቸው እና በዚህም ስጋት እንደገባቸው ዛሬ ጄኔቫ ላይ ለዘጋቢዎች ተናግረዋል።

ደደቢት ላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የተጠለሉበት ስፍራም የአየር ጥቃት ኢላማ እንደነበር ባለፈው ሳምንትም በርካታ የአየር ጥቃት መድረሱን የሚያመለክት መረጃ እንደደረሳቸው መናገራቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል። ዶቼ ቬለ ከአየር ጥቃት ጋር ተያይዞ የሚቀርበውን ወቀሳ በማንሳት ጥያቄ ያቀረበላቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ የሆኑት ጄኔራል ባጫ ደበሌ ሲቪሎችን ኢላማ ያደረገ ጥቃት አልተደረገም ሲሉ ክሱን አጣጥለዋል።

ይኽ በእንዲህ እንዳለም የዓለም የምግብ ድርጅት የሚያከፋፍለው የርዳታ ክምችት እያቀበት መሆኑን አመልክቷል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ቶማስ ፒሪ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በትግራይ አጎራባች አካባቢዎች ውጊያ በመጠናከሩ ነዳጅ እና ምግብ ማሳለፊያው መስመር ተዘግቷል።