ህወሓት ከአማራ እና አፋር ክልል ጠቅልሎ ወጣ እንጂ ወጊያ አቆመ የሚባል ነገር የለም – ጄነራል ባጫ ደበሌ

የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የግንባታ ስራዎች ዋና አስተባባሪ ጄነራል ባጫ ደበሌ ፥ ህወሓት ከአማራ እና አፋር ክልል ጠቅልሎ ወጣ እንጂ ወጊያ አቆመ የሚባል ነገር የለም ሲሉ ተናግረዋል።

ይህን ያሉት ለጀርመን ድምፅ በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው።

ህወሓት ከአፋር እና አማራ ክልል ለቆ ወጥቷል ከተባለ በኃላ በምድር በአብአላ፣ አበርጌሌ፣ ማይፀብሪ አካባቢ፣ እንዲሁም በአየር በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነት እንዳለ ይነገራል።

ጄነራል ባጫ ፥ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ እንደ ትናንሽ ግጭቶች የሚቆጠሩ እንጂ ትላልቅ ግጭቶች አይደለም ያሉት ብለዋል።

አክለው ፥ ” ይህ ማለት ግን አሁንም በተለያዩ ቦታዎች ወጊያ አይከፍትም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ውጊያ የሚከፍትበት መሰረታዊ ነገሮች አሉ አንዱ አልጠፋም ነው፤ መጥፋት አለበት ይሄ ሃይል የገቡበት ተገብቶ ወንጀለኞች መያዝ አለባቸው አለዚያ መጥፋት አለባቸው። ሁለተኛ ይሄ ኃይል ከውጭ ኃይሎች ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሚፈጥርበት መንገድ የለውም ወደሱዳን መውጫ መንገድ የለውም ፤ በሚሌ በኩል ቆርጠን በጅቡቲ በኩል እናስገባለን ሲል የነበረው ነገር አሁንም ይሁን በፊትም እንዲቻልም አልፈቀድንም እኛ፤ ይሄን ኮሊደር ለመክፈት የእሱ የመዋጋት አቅም አዳክመን እስክናጠፋው ይሄን ማድረጉ አይቀርም ” ብለዋል።

ጦርነቱ ከአሁን በኃላ በሰላማዊ መንገድ የመጠናቀቅ እድል ይኖረው ይሆን ተብለው የተጠየቁት ጄነራል ባጫ ይሄን እኔ አልገልፅም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ጄነራሉ ፥ ” ይሄንን እኔ አልገልፅም ፤ ይሄ የኔ ስራ አይደለም። ይሄን ለማሰብ ጊዜ አልወሥድም። እኔ ተዋግቼ እነዚህን ማጥፋት አለብኝ የሚል ትዕዛዝ ነው የተሰጠኝ ” ብለዋል።

የጦርነቱን አውዳሚነትም እንዲህ ሲሉ ነው የገለፁት ፥ ” እነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያ ምንም ሳታደርጋቸው ፤ ይቅርታ ተብሎ ሁሉ ነገር ባለቀበት የእሳትራት ሆኑ ህዝቡንም የእሳትራት አደረጉት። በሁለቱም ወገን መስዋእትነት አለ “

በአሁን ወቅት ትግራይ ላይ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ስለሚፈፀም የአየር ጥቃት ጄነራል ባጫ ተጠይቀው መልሰዋል።

ከሰሞኑን የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ክልል በተፈፀሙ የአየር ጥቃቶች ንፁሃን መገደላቸውን ማሳወቃቸው ፤ የአሜሪካ ፕሬዜዳንት ጆ ባይደን ከጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጋር በተወያዩ ጊዜ ይህ ጉዳይ እንደማያሳስባቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

የጉዳዩን ተጨባጭነት በተመለከተ ጄነራል ባጫ ፤ ” የትግራይ ህዝብ ከማንም በላይ ለእኔ ወንድሜ ነው፤ ህዝባችን ነው። ከማንም በላይ የምንሳሳለት እኛ ነን። አየር ኃይል ይሁን፣ እግረኛ ይሁን ፣ መድፈኛ ይሁን ፣ የድሮን ቡድን ይሁን፣ ሁሉም Rules of engagement አላቸው ንፁሃን ዜጎችን በአየር የሚደበድብ ማንም እብድ የለም አልተደረገም። ” ብለዋል።

ተፈፀሙ ከተባሉ የአየር ጥቃቶች ጋር በተያየዘ ፦ በትግራይ ክልል በሚፈጸሙ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶች ሳቢያ ከ100 በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደልና የንብረት ውድመትን በተመለከተ የደረሱት ሪፓርቶች እንዳሳሰበው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ዛሬ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈፀመ በተባለው የአየር ጥቃቶች ቢያንስ 108 ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውንና እና 75 ሰዎች መቁሰላቸውን ቃል አቀባይዋ ሊዝ ትሮሴል ገልጸዋል።

ጥቃቶቹ የደረሱት ባለፉት ሁለት ሳምንታት (ከፈረንጆቹ ጥር 1 ማለትም ታኅሣሥ 23 ጀምሮ ሲሆን) ተደጋጋሚና ክፉኛ የሚረብሹ ሪፖርቶች ደርሰውናል ብለዋል።

በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት በተፈጸመ የአየር ጥቃት አንድ የ72 ዓመት አዛውንት ተገድለዋል ብሏል።

ማክሰኞ ጥር 03/2014 ዓ.ም የመንግሥት ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ማሰልጠኛ ተቋም ላይ በደረሰ ጥቃት ሦስት ወንዶች ሲገደሉ 21 ሰዎች መቁሰላቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን አብዛኞቹ የቆሰሉት ሴቶች ናቸው። ሰኞ ዕለት ጥር 02፣ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ወፍጮ ቤት ላይ በተፈጸመ የአየር ጥቃት በአካባቢው ተሰበስበው ከነበሩት መካከል 17 ሰዎች ሲገደሉ 21 ሰዎች ቆስለዋል፣ አብዛኛዎቹም ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል።

ከሁሉ የከፋው የአየር ጥቃት የደረሰው የገና ዕለት ታኅሣሥ 29 ሲሆን በደደቢት የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ በተፈጸመው ጥቃት 56 ሰዎች ሲገደሉ 30 ሰዎች ቆስለዋል።

ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸውና ሆስፒታል በህክምና ላይ ከነበሩት መካከል ሦስቱ መሞታቸውን የገለጹት ቃለ አቀባይዋ የሟቾችም ቁጥር 59 ደርሷል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ባወጣው መግለጫ ከታኅሣሥ 10 አስከ 15 ድረስ በትግራይ ውስጥ በተፈጸሙ የአየር ጥቃቶች በርካታ ሰዎች መሞታቸው ሪፖርት መደረጉን አስፍሯል።

ኦቻ ታኅሣሥ 21/2014 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ከጥቅምት ወር ወዲህ ከተከሰቱት በጣም አስከፊና በርካታ ሞቶች ሪፖርት የተደረጉበት ተከተታይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን አመልክቷል።

በርካታዎቹ ጥቃቶች ሪፖርት የተደረጉት በደቡብ ትግራይ ከተሞች በአላማጣ፣ ኮረም፣ ማይጨው፣ መኮኒ እና ሚላዛት መሆኑን ጠቅሷል።

ነገር ግን በአካባቢው ባለው ውስን ተደራሽነት እና የፀጥታ ችግር ምክንያት የሰብአዊ አጋሮች የሟቾችን ትክክለኛ ቁጥር እስካሁን ማረጋገጥ እንዳልቻሉም ጠቅሷል።

ከሰሞኑም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) ሦስት ኤርትራውያን በማይ አይኒ የስደተኞች ጣቢያ በአየር ጥቃት መገደላቸውን አስታውቋል::

ምንጭ: የጀርመን ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ , UNOCHA , UNHRC , ቢቢሲ, Tikvah