” ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ጨዋታ አቁሙ !! ” – ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ምን አሉ ?

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፦

” … እሱ ውጭ ሆኖ ወይም ደግሞ ጥግ ይዞ ወይም ህወሓት አዲስ አበባ ይጋባል ብሎ ሻንጣ ሲያዘጋጅ የቆየ መከላከያን ሊገመግም ይፈልጋል።

በዚህ ወጣ፣ በዚህ ወረደ፣ ይሄን አላደረገም፣ እንዲህ ነው እንዲያ ነው እያለ ይገመግማል።

ለምሳሌ መከላከያ ለምን ጠላት ወደ አማራ ክልል እንዲሰፋ አደረገ ይልሃል ፤ ጦርነት እግር ኳስ ይመስለዋል። ሁለቱ ቡድኖች የሆነ ስታዲየም ተሰርቶ እዛ ውስጥ ተገብቶ በግራ እና ቀኝ በሜትር ተሰምሮ እና ተለክቶ እዛ ውስጥ የምትጋጠም አድርጎ የሚያስብ አለ።

ጦርነት የእግር ኳስ ግጥሚያ አይደለም። አጥር የለውም። ልክ እንደእግር ኳስ ስታዲየም አጥር የለውም። ከአጥሩ ለምን ወጣህ የሚል ህግ የለውም። ሲመችህ ጠላትን ትገፋለህ 400 ኪ/ሜ ታስለቅቀዋለህ፤ ሳይመችህ ደግሞ እስኪመችህ ትከላከላለህ።

ጦርነትን እንደ አዲስ አበባ ስታዲየም ተከልሎለት የምትገጥም የሚደረግ ግጥሚያ አድርጎ የሚረዳ ሰው ነገሮችን የሚረዳበት መንገድ በጣም ደካማ ነው ወይም ሆን ብሎ ነው ለማበጣበጥ ሊሆን ይችላል። ሆን ብሎ ለማበጣበጥ ደግሞ ግንባር ቀደም ተዋናይ TPLF ነው፤ ወገን መስሎ፣ አማራ መስሎ፣ ኦሮሞ መስሎ ሰራዊቱን ለመገምገም ይሞክራል።

ሰራዊት ለመገምገም ቢያንስ 40 ዓመት ሰራዊት ውስጥ ማገልገል አለብህ። ጦርነት ለመገምገም ጦርነት ማወቅ አለብህ፤ ሳይንስ ጥበብ ማወቅ አለብህ። ወጥተህ ወርደህ የሰራዊትን ስነልቦና ማወቅ አለብህ።

ብድግ ብሎ የማንም እንትን … Balloon ሲፈነዳ የሚደነግጥ ሰው ሰራዊት መገምገም የለበትም። ሰራዊት የመጨረሻ ምሽግ ነው። የሉአላዊነት የመጨረሻ ምሽግ ነው። ሰራዊት ብሄር የለውም። ሰራዊት ኢትዮጵያዊነት ነው ያለው።

ሰራዊት ውስጥ ገብተህ በፈተፈትክ ቁጥር ፣ ለማጋጨት በሰራህ ቁጥር ፣ በብሄር በከፋፈልከው ቁጥር ፣ በጓደኛ አንዱን ከፍ አድርገህ አንዱን ዝቅ ባደረከው ቁጥር ሀገር ላይ ነው አደጋ የምትፈጥረው። በነገራችን ላይ የኛ ሰራዊት ለእንደዚህ አይነት ነገር ፣ ለአሉባልተኛ ቦታ የለውም፤ ቦታ አይሰጥም። የተገነባባት መሰረቱ ግንቡ ጠንካራ ነው። ለዛ ምቹ አይደለንም እኛ። ለጎጥ፣ ለብሄርተኝነት ምቹ አይደለንም።

እኛ ብሄር የለንም ብለን ቃል ገብተናል፣ ለኢትዮጵያዊነት ነው የምንሞት ያለነው። ለኢትዮጵያዊነት ነው ሰው 48 ሰዓት ሳይበላ ሳይጠጣ የሚዋጋ ያለው። ለሀገሩ ነው። ኢትዮጵያን ከመበታተን ለማዳን ነው። እኛ እንደኢትዮጵያ ነው የምናስበው።

ለመተቸትም እውቀት ያስፈልጋል። ያለእውቀት የሚተች ወይ ጠላት ነው ሆን ብሎ ለመከፋፈል፣ ለማዳከም፣ ሞራሉን ለማድቀቅ ፣ አመራሩን ለመከፋፈል ጠላት የሚሰራው ነው በአብዛኛው እሱ ነው ብዬ ገምታለሁ። ሌላው ይሄን በማድረግ ትርፍ የሚገኝ እየመሰለው ሊሆን ይችላል ወይ ሌላው ሲያራግብ ጠላት ሲያራግብ የእሱ ወገን ያራገበ መስሎት እያሟሟቀ ይሆናል።

ተውት መከላከያን ! መከላከያ ለእያንዳንዳችን ዋስትና ነው። ስለዚህ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ጨዋታ አቁሙ፤ sensitive የሆነ ቦታ እየመረጥክ የምትጫወተው ጨዋታ የጠላት ጨዋታ ነው። ተው !! ተው !! አሁን በኃላ በማያገባው ገብቶ የመከላከያን ህልውና የሚፈታተን ነገር ላይ የተሳተፈ ከሆነ እራሳችንን ለመከላከል እንገደዳለን “