ኦባሳንጆ በመቀሌ ፊልትማን በናይሮቢ ከሕወሓት አመራሮች ጋር ተነጋግረዋል።

ኦባሳንጆ በመቀለ ከህወሓት መሪ ጋር ተገናኝተው እንደተነጋገሩ ተገለጸ። አምባሳደር ፌልትማን ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን በአዲስ አበባ እንዲሁም የህወሓት ተወካዮችን በናይሮቢ አግኝተው ማነጋገራቸውን ከሳምንታት በፊት ተናግረዋል።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ወደ ትግራይ ሄደው መቀለ ውስጥ ከህወሓት አመራሮች ጋር መነጋገራቸው ተገለጸ።

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ ኦባሳንጆ በአፍሪካ ቀንድ ለተከሰተው ቀውስ መፍትሄ ለማፈላለግ በሚያደርጉት ጥረት ማክሰኞ ጥር 3/2014 ዓ.ም. “ከትግራይ መሪ ጋር መልካም ውይይት ስለማድረጋቸው ተስፋ አድርጋለሁ” ሲሉ አስፍረዋል።

ኦባሳንጆ ከጥቂት ወራት በፊት በተመሳሳይ ጉዞ ወደ መቀለ መሄዳቸው የሚታወስ ሲሆን ስለአሁኑ ጉዟቸው ግን ብዙም የተባለ ነገር አልነበረም።

ከትናንቱ ውይይታቸው በኋላ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕከተኛው ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምረው አመልክተዋል።

ከጥቅምት ወር ወዲህ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት በተባባሰበት ጊዜ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ቢያንስ ለሁለት ጊዜያት ያህክል ወደ ትግራይ ተጉዘው ከህወሓት መሪዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ከወራት በፊት በነበራቸው ጉዞ ከትግራይ በተጨማሪ ጦርነቱ ተስፋፍቶባቸው የነበሩትን የአማራ እና የአፋር ክልል ባለሥልጣናትን ስለመነጋገራቸው ተዘግቦ ነበር።

ይህኛው ዙር የኦባሳንጆ ጉዞ ከቀደሙት የተለየ የሚሆነው የህወሓት ኃይሎች ይዘዋቸው ከነበሩ በርካታ የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች ወጥተው በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር ከገቡ በኋላ መሆኑ አንዱ ነው።

በተጨማሪም የህወሓት ሊቀመንበር ፖለቲካዊ ላሏቸው ልዩነቶች መፍትሔ ለመሻት ለንግግር ዝግጁ መሆናቸውን በይፋ በገለጹበት እና የፌደራሉ መንግሥቱ የአገር አንድነትን ለማጠናከር በሚል የህወሓት አንጋፋ አባላትን ጨምሮ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ከእስር በፈታበት ወቅት መሆኑ ነው።

ከአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑኩ በተጨማሪ የጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት ለማስቆም እና ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ መፍትሔ ለመፈለግ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ እንደነበሩ ተነግሯል።

አምባሳደር ፌልትማን ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይን በአዲስ አበባ እንዲሁም የህወሓት ተወካዮችን በናይሮቢ አግኝተው ማነጋገራቸውን ከሳምንታት በፊት ተናግረዋል።

ከሁለት ወራት በፊት የሕብረቱ ልዩ መልዕክተኛ ወደ ትግራይ ተጉዘው ከህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ጋር ውይይት አድርገው ከተመለሱ በኋላ የፌደራል መንግሥቱን ከትግራይ ኃይሎች ጋር ለማደራደር የሚያደርጉትን ጥረት ‘አልቀበልም’ ያለ ወገን እንደሌለ ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ኦባሳንጆ በወቅቱ “ለማደራደር የማደርገውን ጥረት ‘አልቀበልም’ ያለ የለም” ሲሉ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ይህን ይበሉ እንጂ የአሜሪካ እና የአፍሪካ ሕብረት አሸማጋዮች እስካሁን ድረስ ጥረታቸው ይህ ነው የሚባል አዎንታዊ ለውጥ በይፋ አላሳየም።

በአሁኑ ጊዜ የእርስ በእስር ጦርነቱ ጋብ ይበል እንጂ የፌደራሉ መንግሥት ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን እየፈጸመ ስለመሆኑ እና የህወሓት ኃይሎችም ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የአሜሪካ መንግሥትን ጨምሮ ምዕራባውያኑ ግጭቱ እንዲቆም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲገቱ እና የሰብዓዊ እርዳታ ያለ አንዳች ክልከላ ለተጎጂዎች እንዲደርስ ሲጠይቁ ሰንብተዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ የትግራይ ኃይሎች በፌደራሉ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ከተነገረ በኋላ ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎች የሚቆጠሩትን በመቅጠፍ በሚሊዮን የሚገመቱ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።