በትግራይ ክልል ማይጸብሪ ከተማ ባንድ ወፍጮ ቤት አካባቢ ትናንት ተፈጸመ በተባለ የአየር ጥቃት 17 ሰዎች ሞቱ

በትግራይ ክልል ማይጸብሪ ከተማ ባንድ ወፍጮ ቤት አካባቢ ትናንት ተፈጸመ በተባለ የአየር ጥቃት 17 ሰዎች እንደሞቱ ከረድዔት ድርጅቶች መስማታቸውን ጠቅሰው ዓለማቀፍ ዜና ወኪሎች ዘግበዋል። በጥቃቱ የሞቱት አብዛኞቹ ሴቶች እንደሆኑ እና ቁጥራቸው ለጊዜው ያልታወቁ ሰዎች ደሞ እንደቆሰሉ ዘገባዎቹ አመልክተዋል። በክልሉ ባለፈው ሳምንት ተፈጽመዋል ከተባሉ የአየር ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ዓለማቀፍ ረድዔት ድርጅቶች ደደቢት፣ ሽራሮ እና ማይጸብሪ ከተሞችን ጨምሮ በሰሜን ምዕራብ ትግራይ የዕርዳታ ሥራቸውን ማቋረጣቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በትግራይ ክልል ተፈጽሟል በተባለ የአየር ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች ሞተዋል መባሉ እንዳሳዘናቸው በቃል አቀባያቸው በኩል ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የአየር ድብደባው ተፈጸመ የተባለው በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ደደቢት ከተማ በሚገኝ የተፈነቃዮች መጠለያ ላይ እንደሆነ ዘገባዎች አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት በማይ ዓይኒ ስደተኞች መጠለያ ተፈጸመ በተባለ ሌላ የአየር ጥቃት ሁለት ሕጻናትን ጨምሮ ሦስት ኤርትራዊያን ስደተኞች መሞታቸውን መስማታቸውን ጉተሬዝ ገልጸዋል። ጉተሬዝ በአካባቢው የአየር ድብደባን ጨምሮ ባጠቃላይ ግጭቱ ባስቸኳይ እንዲቆም እና ተፋላሚ ወገኖችም በዓለማቀፍ ሕጎች መሠረት የሰላማዊ ሰዎችን ደኅንነት እንዲጠብቁ እና የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እንዲቀላጠፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።