ሦስት ባለሥልጣናት ምዕራብ ሸዋ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተገደሉ

በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ሚዳቀኚ ወረዳ ሦስት የአካባቢው ባለሥልጣናት ባደፈጡ ታጣቂዎች ሲገደሉ አንደኛው የመቁሰል ጉዳት ደረሰባቸው።

ግድያው የፈጸመው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ሲሆን የተገደሉት ግለሰቦች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ያሉ መሆናቸውን የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጋቢሳ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ወደ አምቦ ከተማ ሄደው ሲመለሱ በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና የድርጊቱ ፈጻሚዎች የኦነግ-ሸኔ ታጣቂዎች መሆናቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ግድያው የተፈጸመባቸው አቶ ለሚ ገብሬ የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ኃላፊ፣ ወ/ሮ ደራርቱ ተስፋዬ የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ተጠሪ እና አቶ ወንድሙ ዱጋሳ የወረዳው የኅብረት ሥራ ኃላፊ መሆናቸውን የምዕራብ ሸዋ ዞን ኮምዩኒኬሽን አቶ ተስፋዬ ምሬሳ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አብደና አብሹ የመቁሰል ጉዳት ደርሶባቸው መትረፋቸው ታውቋል።

ታጣቂዎቹ የፀጥታ አካላት በማይኖሩበት ስፍራ ላይ አድፍጠው በመጠበቅ ግለሰቦቹን ይጓዙበት ከነበረ ተሽከርካሪ ላይ አስወርደው የገደሏቸው መሆኑንና ከተገደሉት ሰዎች መካከል አንዷ ሴት መሆናቸውን አቶ ግዛቸው ጠቅሰው “የግድያው ድርጊት እጅግ ጭካኔ የተሞላበትና በሰው ላይ የማይፈጸም” ነው ብለዋል።

ኃላፊው ጨምረውም ግድያው የተፈጸመው ሦስቱ ግለሰቦች ከዞን ወደ ወረዳ እየተመለሱ ባሉበት ወቅት መሆኑን አመልክተው፤ “ሰዎቹ የአካባቢያቸውን ሕዝብ በማገልገል የሚታወቁና በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፉ ናቸው” ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል።

የአካባቢው ባለሥልጣንት እንዳሉት ግድያ የተፈጸመው በሽብርተኛ ቡድንነት በተሰየመው ሸኔ በተባለው ታጣቂ ኃይል መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን የኦሮሞ ነፃነት ጦር ቡድኑ ቃል አቀባይ የሆኑት ኦዳ ተርቢ እንዳሉት በእንዲህ አይነት ድርጊቶች ውስጥ የቡድናቸው ታጣቂዎች እጅ እንደሌለበት አመልክተው፣ ሌሎች በሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ቡድናቸው እየተከሰሰ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

ታጣቂዎቹ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች በተወሰኑ ሰዎች ላይ ያተኮረ ሳይሆን በሁሉም የአካባቢው ነዋሪ ላይ ያነጣጠረ ነው ይላሉ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግዛቸው ጋቢሳ።

“በአቡና ግንደ በረት ወረዳ ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ 3 ሰዎችን ገድለዋል። የመንግሥት አመራር ብቻ ሳይሆን በቀያቸው ያሉ ንጹህንን እና ትምህርት ቤት ያሉ ልጆችን ጭምር ገድለዋል።”

የአካባቢው ባለሥልጣንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ታጣቂ ቡድኑን ከምዕራብ ሸዋ ዞን በማስወገድ የሕግ የበላይነት የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ ነው።

በዚህም “እንደ አቡና ግንደ በረት እና ጀልዱ ባሉ ወረዳዎች እንዲሁም በሌሎችም አካባቢዎች በሕዝቡ ላይ ጥቃት በሚፈጽሙ የታጠቁ ኃይሎች ላይ በተከታታይ እርምጃ እየተወሰደ ነው” ሲሉ አቶ ግዛቸው ጋቢሳ ገልጸዋል።

ጨምረውም በአካባቢዎቹ ተደብቆ ያሉት ታጣቂዎች “በሕዝቡ ላይ ግድያን፣ ዘረፋንና ሀብትና ንብረትን እያቃጠሉ ከባድ ችግር ሲፈጥሩ ቆይተዋ” ብለዋል። ይህንንም ለማስቆም የፀጥታ ኃይሎች እርምጃ እየወሰዱ መሆናቸውን አመልክተዋል።

መንግሥት ሸኔ የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተሰየመው የዚህ ቡድን ታጣቂዎች በምዕራብና በደቡብ የኦሮሚያ ክፍሎች እንደሚንቀሳቀስ ይነገራል።

ከዚህ በፊትም በተለያዩ የምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ውስጥ ባሉ ነዋሪዎች እና በባለሥልጣናት ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ስሙ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

ቡድኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደሥልጣን መምጣትን ተከትሎ የትጥቅ ትግል በማቆም ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ከተመለሱት አማጺያን መካከል አንዱ ከሆነው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተነጥሎ የወጣ ታጣቂ ቡድን ነው።

BBC AMHARIC