ዓለም ምግብ ፕሮግራም በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው ኮምቦልቻ ውስጥ ያሉት የሰብዓዊ እርዳታ ማከማቻ መጋዘኖቹ መዘረፋቸውን ገለጸ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም ምግብ ፕሮግራም በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው ኮምቦልቻ ውስጥ ያሉት የሰብዓዊ እርዳታ ማከማቻ መጋዘኖቹ መዘረፋቸውን ገለጸ።

Last week, WFP was granted access to humanitarian warehouses in Kombolcha, Amhara region. substantial amounts of food looted from the facilities.

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ቶምሰን ፊሪ፤ ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ድርጅት በአማራ ክልል ኮምቦልቻ የሰብዓዊ እርዳቃ እንዲያቀርብ ፍቃድ አግኝቷል ብለዋል።

ቃል አቀባዩ ይህን ዝርፊያ ማን እንደፈጸመው እና መቼ እንደተፈጸመ ያለው ነገር የለም። ይሁን እንጂ የህወሓት ታጣቂዎች ከሳምንታት በፊት የኮምቦልቻ እና የደሴ ከተሞችን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

ቃል አቀባዩ ቶምሰን ፊሪ፤ የዓለም ምግብ ድርጅት መጋዘኖች መዘረፍ ማለት የዓለም ምግብ ፕሮግራምና አጋሮቹ የሚያቀርቡት የእርዳታ መጠን የተገደበ እንዲሆን ያደርገዋል ብለዋል።

ይህ ቢሆንም የዓለም ምግብ ፕሮግራም አሁን ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ጭምር እርዳታ እየሰጠ እንደሆነና ከዛሬ [ማክሰኞ] ጀምሮ በኮምቦልቻና ደሰ ከተሞች ለ450 ሺህ ሰዎች እርዳታ መስጠት እንደሚጀምር ቶምሰን አሳውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ባለው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ አካላት የሰብዓዊ እርዳታ እንቅስቃሴውን እንዲያከብሩ ጠይቋል።

የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጄኔቫ ከሚገኘው ጽህፈት ቤት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የግጭቱ ተሳታፊዎች የሰብዓዊ እርዳታ ያለችግር ለሚፈልጉት ሰዎች እንዲደርስ መንገድ እንዲከፍቱ ጠይቀዋል።

እስከዛሬ ባለው አሃዝ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ክልል ከ2.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች፤ በአፋር ክልል ለ124 ሺህ ሰዎች እንዲሁም በአማራ ክልል ለ220 ሺህ ሰዎች እርዳታ ማቅረቡን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ድርጅቱ ይህን እርዳታ ያደረገው ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች ጭምር መሆኑን ያስታወቁት ቃል አቀባዩ፤ ወደ አማራና ትግራይ ክልሎች የሚወስደው ዋና መንገድ መዘጋቱንም ጠቁመዋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በሰሜን ኢትዮጵያ እርዳታ የሚሹ 3.7 ሚሊዮን ሰዎችን ለመድረስ ከሁሉም አካላት ትብብር ጠይቆ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች እርዳታ እንዲደርስ መንገዶች እንዲከፈቱ ተማፅኗል።

ከግጭቱ ባለፈ ያልተጠበቀ የገንዘብ እርዳታ መቋረጥ በኢትዮጵያ ያለውን የእርዳታ ሥራ እንዳስተጓጎለው ቃል አቀባዩ አክለው ገልፀዋል።

ፕሮግራሙ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን የምግብ እጥረት ለማስታገስ ቢያንስ 279 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ነው ቶምሰን ለጋዜጠኞች የተናገሩት።

በመላው አገሪቱ ያለውን የምግብ እጥረት ለመቋቋም ደግሞ 546 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ገልፀው ይህ ከተሳካ በሚቀጥቀሉተ ስድስት ወራት 12 ሚሊዮን ሰዎችን መርዳት እንደሚቻል አሳውቀዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ግጭት ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በሚሊዮን የሚቀጠሩ ሰዎች እርዳታ ጠባቂ መሆናቸው በተደጋጋሚ ተዘግቧል።

BBC Amharic