በኢትዮጵያ ትላልቅ ተቋማት ላይ ሰሞኑን የተፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶች በውስጥ “ወንበዴዎች” የተፈጸሙ ናቸው

ተቋምት የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውንና ኔትዎርኮቻውን የሚያስተዳድሩ አካላትን የስነ ምግባር ማጣራት እንዳለባቸው አሳስበዋል

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ትላልቅ ተቋማት ላይ የተፈፀሙ የሳይበር ጥቃቶች ከውስጥ መፈፀማቸውን ታሳቢ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

2ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር “የሳይበር ደህንነት የጋራ ኃላፊነት! እንወቅ! እንጠንቀቅ!” በሚል መሪ ቃ የመክፈቻ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢንሳ/ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በዚሁ ወቅት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የዲጂታል ስነ ምህዳሩን በመጠቀ የሳይበር ጥቃቶች በተለያየ መንገድ ሊከሰቱ እንደሚችል ገልጸዋል።

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የተለያዩ ‘ማልዌሮችን’ በመላክ ወይም የተለያዩ ሲስተሞች ውስጥ ሰርጎ በመግባት ሲስተሞቹ እንዳይሰሩ መጥለፍ እና መረጃዎችን መስረቅ ነው ብለዋል።እነዚህ አካላት የሳይበር ምህዳሩ ተጠቃሚው እያደገ በሄደ ቁጥር የሚያገኙት ጥቅም ስለሚጨምር የተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎችን በመከተል ማስቆም እንደሚቻል አስታውቀዋል።

ሁለተኛው በተቋማት ውስጥ ባሉ ግለሰቦች አማካኝነት ከውስጥ የሙፈጸሙ የሳይበር ጥቃቶች እና ማጭበርበሮች መሆኑንም አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ትላልቅ ተቋማት ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በውስጥ “ወንበዴዎች” የሚፈፀሙ መሆኑን አስታውቀዋል።

“ለአብነትም በኢቢሲ የፌስቡክ ገጽ ላይ የበዓለ ሲመቱ እለት ለተወሰነ ጊዜ ሌሎች ሰዎች የግላቸውን ሀሳብ ሲለቁበት ነበረ፤ ይህ የተፈጠረው እዛ ውስጥ ባሉ የፌስቡክ አካውንቱን በሚያስተዳደርሩ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች አማካኝነት ለሀገራቸው፣ ለተቋማቸው እና ለሙያቸው ታማኝ ባለመሆን ከውስጥ የፈፀሙጽ መሆኑን ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በአፍሪካ ህብረት የትዊተር ገጽ ላይም በውስጥ ባለ ሰው አማካኝነት የተቋሙ ያለሆነ ሀሳብ ተለቆ እንደነበረ ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ የተፈጠረውም ተመሳሳይነት እንዳው የገለጹት ዶ/ር ሹመቴ፤ “አየር መንገዱ የተለያዩ ኤርያ ማናጀሮች አሉት፣ እነዚህ ማናጀሮች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፌስቡክ ገጽንም ስለሚያስተዳደሩ የአየር መንገዱ አቋም ያልሆነ አቋም ባልተገባ መልኩ ለቀዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

ስለዚህም ከውጪ ብቻ ሳይሆን በውስጥም ጥቃቶች ሊሰነዘሩ እንደሚችሉ ታሳቢ በማድረግ መጠንቀቅ እና መስራት እንደሚያስፈልግም ነው ዶ/ር ሹመቴ ያስጠነቀቁት።

የቋማት መሪዎች ይህንን ታሳቢ በማድረግ የማህበራዊ ሚዲያዎቻቸውን፣ ድረ ገጾቻቸውን፣ እና ኔትዎርኮቻውን የሚያስተዳድሩ አካላትን ትክክለኛ የሆነ የስነ ምግባር ማጣራት ማድረግ እንዲሁም ለሙያቸው እና ለሀገራው የሚታመኑ መሆኑን ማጣራት አለባው ሲሉም አሳስበዋል።

የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው በ2ኛው ሀገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት ወር መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግርም፤ በኢትዮጵያም የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትና የጥቃት ሙከራዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የመጣ መሆኑን አንስተዋል።

ለአብነትም በ2012 ዓ.ም ከተሰነዘሩት አደገኛ የሳይበር ጥቃቶች አሃዝ 1 ሺህ 87 ከነበረበት ባሳለፍነው ዓመት በ2013 ከ150 በመቶ በላይ ጨምሮ ከ2800 በላይ የሳይበር ጥቃቶች መሰንዘራውን ጠቅሰዋል።

የሳይበር ጥቃት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር አለም አቅፋዊ በሆነው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ 1ኛ እና 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌቶች፣ በ2013 የተካሄደውን ሀገራዊ ምርጫ እና በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻ ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

ይህም በሀገሪቱ ቁልፍ መሠረተ ልማቶችና ተቋማት እንዲሁም በዜጎች ላይ የሚደርሰው የሳይበር ጥቃት ከአመት ወደ አመት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “እንደ ሀገር ችግሩን የሚመጥን ቅድመ ዝግጅት ካላደረግን እና ዘላቂ መፍትሄ ካላስቀመጥን በሀገራችን የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ ከማሳደሩም ባሻገር ለህልውናችንም አደጋ ሊጋርጥ እንደሚችል ልንገነዘበው ይገባል” ብለዋል።

አል ዐይን አማርኛ