በተከዜ ግንባር 21 ጊዜ የማጥቃት ሙከራ ያደረገው አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በምኒልክ ብርጌድ በተደጋጋሚ አሳፋሪ ሽንፈት ደርሶበታል።

May be an image of 7 people, people standing and outdoorsበአማራ ልዩ ኀይል ጀግናው የምኒልክ ብርጌድ ጠላትን መድረሻ የሚያሳጣ ማዕበል ነው። ገና ስሙ ሲጠራ ጠላትን ያርበደብዳል፣ እንደ ነበልባል በሚያስፈራው ፈርጣማ ክንዱ አሳፍሮ መመለስ ያውቅበታል። በተካነበት ውጤታማ የማጥቃት ስልት ጦሩን በወሳኝ ቦታ አስፍሮ አሸባሪውን የትህነግ ወራሪ ቡድን ተከዜን እንዳይሻገር የማያዳግም ርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛል።
የምኒልክ ብርጌድ ወደ ተከዜ ግንባር ካቀናበት ጊዜ ጀምሮ 21 ጊዜ የማጥቃት ሙከራ ያደረገው አሸባሪው የትህነግ ወራሪ ቡድን በተደጋጋሚ አሳፋሪ ሽንፈት ደርሶበታል። በተከዜ ቀጣና ሁሉም ቦታዎች ለጠላት እንቅስቃሴ በማያመች መልኩ ተዘግተዋል፣ በዚህም ጠላት ቀጥታ የማጥቃት ሙከራ እያደረገ መሆኑን በብርጌዱ የሻለቃ መሪዎች ተናግረዋል።
የልዩ ኀይል አባላቱ በአስተማማኝ መረጃ ላይ የተመሰረተ ስምሪት ስለተሰጣቸው ጠላት ወደ ተከዜ በተጠጋ ቁጥር ተመልሶ እንዳይሄድ የመደምሰስ ርምጃ እየተወሰደበት እንደሆነም አስታውቀዋል። “አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት ነው የሚታዘዝለት” ያሉት የሻምበል አዛዦቹ ጠላት ላደረጋቸው ሙከራዎች ሁሉ ተገቢውን አጸፋ ተሰጥቷል ነው ያሉት።
የመሪዎች ጥንካሬ፣ የልዩ ኀይሉ አባላት አስተማማኝ ዝግጁነት እና ቆራጥ አቋም ፣ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፋኖ እና ከሚሊሻ ጋር የተሳለጠ ቅንጅታዊ ስምሪት መኖሩ እና የደጀን ሕዝብ ጥንካሬ አካባቢው በጠላት እንዳይደፈር ማድረጉን ጠቅሰዋል። በቅርቡ ጠንካራ ወታደራዊ ብቃት ያላቸው አባላት ብርጌዱን ተቀላቅለዋል። እነዚህ የልዩ ኀይል አባላት ተከዜን ተሻግሮ ጠላትን የማጥፋት ፍላጎት፣ ወኔ እና ዝግጁነት አላቸው። “በቅርብ ጊዜ የሚሠራ ታሪክ ይኖራል፣ ይህንንም አሸባሪው ያየዋል” ነው ያሉት።
May be an image of 10 people and outdoorsከ21 ጊዜ በላይ ሙከራ አድርጎ ያልተሳካለት አሸባሪው ኀይል አሁንም ትንኮሳ ከማድረግ አልተቆጠበም። የአሚኮ የጋዜጠኞች ቡድን በማይጋባ ግንባር ተገኝቶ ይህንን አረጋግጧል። ሀገር ሊያፈርስ የተዘጋጀው አሸባሪ ቡድን ቀጣይ ሊያደርግ የሚችላቸውን ሙከራዎች ታሳቢ በማድረግ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ ሁሌም ዝግጁ ነው።
የልዩ ኀይል አባላቱ ሕዝብና መንግሥት የሰጣቸውን አደራ በአግባቡ ተቀብለው ተልዕኳቸውን በውጤታማነት እየፈጸሙ ነው የሚገኙት። ሀገርን እና ሕዝብን ከውርደት ለመታደግ አሁንም ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ ራበኝ፣ ጠማኝ ሳይሉ የዝናብ እና የፀሐይን ተጽዕኖ ተቋቁመው በተጠንቀቅ መሽገዋል።
ለዘመናት ማንነቱን ተነጥቆ አንገቱን ደፍቶ የኖረው የአማራ ሕዝብ ከዚህ በኋላ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር ማንም አይፈቅድም ያሉት የሻምበል መሪዎች ሂሳብ ለማወራረድ የመጀመሪያው ቀመር ቀላል ቢሆንም ወደ መሃል ሲገባ ይከብዳል፤ እነጌታቸው ይህን ስለማይችሉ ሕዝባቸውን እያስፈጁ ነው ብለዋል። አዲሱ ዓመት ጠላት ከኢትዮጵያ ምድር ጠፍቶ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖር በትኩረት የሚሠራበት ዓመት እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን በተለይ አሸባሪው ቡድን በመሸገበት የኢትዮ-ሱዳን አዋሳኝ አካባቢ እና በተከዜ ወንዝ ቀጣና ያለው የኀይል አሰላለፍ አስተማማኝ እና ጠንካራ በመሆኑ ጠላት ወደ ወልቃይት ጠገዴ ለመሻገር ሙከራ ለማድረግ አልደፈረም፤ ከ41 ዓመታት በላይ ይህንን አሸባሪ ቡድን ሲዋጋ የኖረው የዞኑ ሕዝብም ከሠራዊቱ ጋር ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ የጠላትን እንቅስቃሴ በንቃት እየተከታተለ ነው፣ መረጃ በመስጠት፣ በጸጥታ ሥራው በቀጥታ በመሳተፍ እና የስንቅ ድጋፍ በማድረግ ሥምሪቱ ውጤታማ እንዲሆን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

(አሚኮ)

May be an image of 2 people and outdoors