ዓለም ለማሸነፍ ይዘጋጃል እኛም እንደ አንድ ትልቅ አገር ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል – ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ


የመረጃ ቲቪን 24/7 የሳተላይት ስርጭት በመደገፍ የኢትዮጵያ ህዝብ አማራጭ እና ትክክለኛ መረጃ በማግኘት እራሱን ከተጋረጠበት አደጋ መከላከል እንዲችል እናግዝ። በአሁኑ ወቅት ከመረጃ ቲቪ በስተቀር ሌሎች ሁሉም በኢትዮጵያ ያሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመንግስት የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ናቸው። ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ የከፈትነው የመረጃ ቲቪ የሳተላይት ስርጭት የአንድ ዓመት ወጪን ለመሸፈን ነው። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ድጋፍዎትን ይለግሱ » https://gofund.me/54405070

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዜዳንት የሆኑት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በቶኪዮ ኦምፒክ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው ቡድን ውጤት ለማስመዝግበ በጣም ጥሩ የሚባል ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል። ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ለቢቢሲ አማርኛው ክፍል በሰጡት ቃል ፥ “አንዳንድ ችግሮች አይታጡም ግን ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነው” ብለዋል። አክለውም ፤ ” ዓለም ለማሸነፍ ይዘጋጃል። እኛም እንደ አንድ ትልቅ አገር ለማሸነፍ ተዘጋጅተናል” ሲሉ ተናግረዋል። “ፈጣሪ ከረዳን ጥሩ ውጤት እናመጣለን ብለን እናስባለን” ያሉት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ “እንደ ልባችን እንዳንሰራ የረበሸን ነገር ኮቪድ-19 ወረርሸኝ ነው” ብለዋል።

በሌላ በኩል የረዥም ርቀት ዋና አሰልጣኝ የሆኑት ኮማንደር ሁሴን ሺቦ ለቢቢሲ በሰጡት ቃል፥ “ሀገራችን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ አትሌቶቻችንም፤ እኛም በአካልም በአእምሮም ዝግጁ ሆነናል” ብለዋል። አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ፤በውድድር ላይ 4 ቡድን ማለትም የሴቶች እና የወንዶች 5 ሺህ እና 10 ሺህ ሜትር ውድድሮችን እንደሚመሩ ተናግረው አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ አቅደን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። በተመሳሳይ ኢትዮጵያን ወክለው ቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ የሚወዳደሩ አትሌቶች የሀገሪቱን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እና ጥሩ ውጤት ለማስመዝገብ እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።

አትሌቶችከነገ ወዲያ በሚጀመረው የቶኪዮ ኦሎምፒክ ውድድር ላይ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆናቸውን አትሌቶች እና አሰልጣኞች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በጃፓን መዲና የሚካሄደው የቶኪዮ ኦሎምፒክ የፊታችን ዓርብ ሐምሌ 16 ጀምሮ ነሐሴ 8 ይጠናቀቃል።

ኢትዮጵያ በቶኪዮ ኦሎምፒክ ከአትሌቲክሱ በተጨማሪ በውሃ ዋና፣ በብስክሌት ውድድር እንዲሁም ለመጀመሪያ ጊዜ በቴኳንዶ ውድድር ትወከላለች።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 35 አትሌቶችን ይዞ ወደ ቶኪዮ የሚያመራ ሲሆን አትሌቶች በ7 የተለያዩ ርቀቶች ተወዳዳሪ ሆነው ይቀርባሉ።

በኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ውስጥ የወቅቱ የ5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ክብረ ወሰን ይዛ የምትገኘው ለተሰንበት ግደይ ትገኝበታለች።

በኮቪድ-19 ስርጭት ምክንያት በአንድ ዓመት ዘግይቶ ለሚከናወነው የኦሎምፒክ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ያለፉትን 8 ወራት በሆቴል ቆይተው ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

የአትሌቲክስ ቡድኑ ዝግጅት ምን ይመስል ነበር? ሕዝቡ ምን አይነት ውጤት ይጠብቅ? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ ለማግኘት በዝግጅት ላይ የነበሩ አትሌቶችን ጠይቀናል።

ሰለሞን ባረጋ

ሰለሞን ባረጋ አገሩን ወክሎ በ10ሺህ ሜትር ተወዳዳሪ ሆኖ ይቀርባል።

”ጥሩ ነጥብ እናመጣለን ብዬ አስባለሁ። እስካሁን 5ሺህ ሜትር ስወዳደር ነበር። በ10ሺህ ከእኔ ጋር ከሚወዳደሩት ጋር ተወዳድሬ ባላውቅም አሯሯጣቸውን ግን አውቃለሁ። ባለ ሪከርድ ከሆኑ የኬንያ እና ኡጋንዳ አትሌቶች ጋር ነው የምወዳደረው” በማለት አትሌት ሰለሞን ባረጋ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የ10ሺህ ሜትር ውድድር ዓርብ ሐምሌ 23 ይካሄዳል። በዚህ ውድድር ከሰለሞን ባረጋ በተጨማሪ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሪሁ አረጋዊ ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

ባለፉት ሁለት የኦሎምፒክ ውድድሮች ማለትም በሪዮ እና ለንደን ኦሎምፒክ በ5ሺህ እና በ10ሺህ ኦሎምፒክ የወርቅ ተሸላሚው መሐመድ ፋራህ መስፈርት ማሟላት ባለመቻሉ ከመድረኩ ቀርቷል።

ሹራ ቂጣታ

አትሌት ሹራ ቂጣታ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሎምፒክ ይወዳደራል። አትሌት ሹራ ኢትዮጵያን በማራቶችን የሚወክል ሲሆን፤ “በዚህ ውድድር ለአገርም ለግልም ወርቅ ማምጣት አለብን በሚል ነው እየተዘጋጀን ያለነው” በማለት ይናገራል።

ከአንድ ዓመት በፊት በለንደን ማራቶን የኬንያውን ኢሊዩድ ኪፕቼጌን ያሸነፈው ሹራ፤ በቶኪዮ ኦሎምፒክም የማራቶን ክብረ ወሰን ባለቤት ኪፕቼጌ ጋር ይወዳደራል።

ከአትሌት ሹራ ጋር አትሌት ሌሊሳ ዴሲሳ እና ሲሳይ ለማ አገራቸውን ወክለው በማራቶን ይሳተፋሉ።

አሰልጣኝ ሁሴን ሺቦ

የረዥም ርቀት ዋና አሰልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሺቦ በኦሎምፒክ ውድድር ላይ ተሳታፊ ሲሆኑ የቶኪዮ ኦሎምፒክ 6ኛው ሆኖ ይመዘገባል።

“ለአገራችን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ አትሌቶቻችንም፤ እኛም በአካልም በአእምሮም ዝግጁ ሆነናል” በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሰልጣኝ ሁሴን በ5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ውድድሮች የሚሳተፉ አትሌቶችን ይመራሉ።

“አራት ቡድን እመራለሁ። የሴቶች እና የወንዶች 5ሺህ እና 10ሺህ ሜትር ውድድሮችን። 1ኛ እና 2ኛ ደረጃን ለመያዝ አቅደን እየሰራን እንገኛለን” የሚሉት አሰልጣኙ፤ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበ ውጤት በቶኪዮ ኦሎምፒክ ውጤት ይመዘገባል ብዬ እገምታለሁ ብለዋል።

አሰልጣኝ ሁሴን በዘንድሮ የቶኪዮ ኦሎምፒክ የሚሳተፉት አብዛኛዎቹ አትሌቶች በኦሎምፒክ ውድድር ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።

“ከአጠቃላይ አትሌቶች 98 በመቶ የሚሆኑት ከዚህ ቀደም በኦሎምፒክ ውድድር ተሳትፈው የሚያውቁ ስላልሆኑ በከፍተኛ ተነሳሽነት በውድድሩ ተሳትፈው አመርቂ ውጤት ያስመዘግባሉ የሚል እምነት አለኝ” ብለዋል።