በትግራይ የመደፈር ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች በዋነኝነት ጥቃት የሚደርስባቸው በኤርትራ ወታደሮች መሆኑን ገለጹ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በትግራይ ክልል የመደፈር ጥቃት የተፈፀመባቸው ሴቶች እና ልጃገረዶች ቁጥር ከ1,400 መብለጡን ገለፀ። የጥቃቱ ሰለባዎች በዋነኝነት ጥቃት የሚደርስባቸው በኤርትራ ወታደሮች ስለመሆኑ መናገራቸውን ወ/ሮ ኢተነሽ ንጉሰ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፍትህ እና የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል።

በፌዴራል መንግስቱ የተሾሙት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፍትህ እና የሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ኢተነሽ ንጉሰ ፥ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ህክምና ተቋማት የሄዱ ሴቶች እና ልጃገረዶች ቁጥር 1,408 መድረሱን ተናግረዋል።

እንደትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መረጃ ፦

– በመቐለ 716

– ከዓዲግራት 362

– ከአክሱም 85

– ከሽረ 48

– ከማይጨው 37

– ከመሆኒ 18 የተመዘገቡትን ጨምሮ አጠቃላይ 1,408 ሴቶች እና ልጃገረዶች ተደፍረዋል።

የዓይደር ሆስፒታል ዋና ስቶፕ ሴንተር አስተባባሪ ሲስተር ሙሉ መስፍን ፥ በትግራይ ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ጥቃት ከመሻሻል ይልቅ እየተባባሰ መሄዱን አመልክተዋል።

ወደ ዓይደር ሆስፒታል ሄደው ስለታከሙና በመታከም ላይ ስለሚገኙ ጉዳተኞች ሲስተር ሙሉ መስፍን ሲገልፁ “ተሻሽሏ የሚባል ነገር የለም” ብለዋል።

በኤርትራም በኢትዮጵያም ወታደሮች ተደፍረው ፅንስ ለማቋረጥ ወደሆስፒታሉ የሄዱ 238 ሴቶች እና ልጃገረዶች መኖራቸውን ሲስተር ሙሉ ተናግረዋል።

ፅንስ ሲያቋርጡ በደም እና በሌላም የሰውነት ፈሳሽ መፍሰስ ምክንያት የተወሳሰበ የጤና እክል ያጋጠማቸው በኩላሊት መጎዳት ምክንያት ለዳይለሲስ የገቡ ሴቶች መኖራቸውንም ጨምረው ገልፀዋል።

ሲስተር ሙሉ ይህን ብለዋል ፦

“አብዛኞቹ ተደፍረው ካምፕ ውስጥ ነው የሚያቆይዋቸው ። ለሳምንት ለሁለት ሳምንት መድሃኒት በማያገኙበት ሁኔታ ውስጥ ተይዘው ስለሚቆዩ በሽታው ይጠናባቸዋል።

በግብረስጋ ግንኙነት ለሚተላለፉ ሁሉም አይነት በሽታዎች ተጋልጠው ነው የሚመጡት ፣ በዛ ላይ የስነልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል። ማልቀስ ፣ መረበሽ፣ እንቅልፍ ማጣት በጣም ከባድ በሆነ የአእምሮ ስቃይ ላይ ነው የሚገኙት።

ተደብድበው የአካል ጉዳት የአጥንት መሰበር፣ የደረሰባቸው አሉ። ብረት በማጋል በማቃጠል ከደፈሯቸው በኃላ በብልቃጥ አሲድ ይዘው ሆዳቸው እና ብልታቸው ላይ ማርከፍከፍ ምን ልበል ሁሉም ከነበረበት እየከፋ ነው።

እኛ እየተናገርን ነው ። ዓለምም እየሰማ ነው። ግን እየከፋ ነው እየሄደ ያለው። በገንዘብ፣ በትራንስፖርት እጥረት ፣ በፀጥታ ስጋት ያልመጡ ብዙ እንዳሉ ተጎጂዎቹ እራሳቸው ይነግሩናል።

እየተጠቁ ያሉት ምንም የማያውቁ ህፃናትን ጨምሮ ሴቶች እና ልጃገረዶች በአጠቃላይ ሲቪል ማህበረሰብ በመሆናቸው ሆነ ተብሎ የሚፈፀም ግፍ ነው።

መንግስት እንዲያውቀው እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ለ6 እና ለ7 ወር ስህተት ሊፈፀም አይችልም ፤ ፈፃሚዎቹ በመንግስት የሚመሩ አካላት ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በበኩሌ እየተበረታቱ እንደሆነ ነው የምገነዘበው።”

ምናልባት ከኤርትራ እና ኢትዮጵያ ወታደሮች ውጪ በሴቶች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ይኖሩ ይሆን (የመደፈር ጥቃት ደርሶባቸው ዓይደር ሆስፒታል የገቡ ሴቶች ይኖገሩ እንደሆነ) የተጠየቁት ሲስተር ሙሉ ፥ አሉ ነገር ግን ጥቂት ናቸው ብለዋል።

ከ95 በመቶ በላይ በሁለቱ የመከላከያ ኃይሎች እና ወታደሮች ጥቃት እንደተፈፀመባቸው ነው ተጎጂዎቹ የሚናገሩት ።

5% ወይም 10% የሚፈፀመው በሲቪሎች እንደሆነ የሚናገሩት ሲስተር ሙሉ በግላቸው እይታ ይህ የሚፈፀመው ህግ የለም በሚል እንደሆነ ይናገራሉ አክለውም ውጤታማ የፖሊስ ጥበቃ ቢኖር፣ ህግ ቢኖር እንዲህ አይሆንም ነበር ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት የUSAID ተወካይ ቴራ ቻርለስ በትግራይ ስላለው የሴቶች ጥቃት ይህን ተናግረው ነበር፦

“በታጣቂ ተዋንያን ስለሚፈፀሙ በደሎች ዘገባዎች ደርሰውናል። ሪፖርቶቹ የሚያሳዩት የመደፈር እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ብዙ ጥቃቶች ብቻ ሳይሆን ህብረተሰቡን ለማፍረስ እና ቤተሰቦችን ለማጥፋት የሚፈፀሙ ስልታዊ ሙከራዎች ናቸው። አድራጎቱን የሚፈፅሙ አንዳድን ተዋንያኖች የካህናት ሚስቶችን ይደፍራሉ። ሴቶችን በቤተሰቦቻቸው ፊት ይጎዳሉ፣ ብልታቸው እስኪጎዳ ድረስ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃትም ፈፅመውባቸዋል። የጥቃቱ ክብደት በሁለት አስርት ዓመታት የሰብአዊ እርዳታ ስራዬ ውስጥ ካየሁት እጅግ ከከፉ ግፎች መካከል አንዱ ነው”

በትግራይ የሴቶች መደፈር እየከፋ ስለመሄዱ ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቀው እንደሆነ የተጠየቁት የትግራይ ፍትህ እና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ኢተነሽ ፥እሳቸው ቢሮውን ከተረከቡ 3 ሳምንት እንደሆናቸው ገልፀው ከሚመለከታቸው የበላይ አካላት ጋር አንድ መድረግ ለማዘጋጀት መታሰቡን ተናግረዋል።

የችግሩን ስፋት በማንሳትም እየከፋ እና እየባሰበት በመሄዱ እነሱ እንዴት ሊያግዙ እንደሚችሉ ለመመካከር ከተሳካ በቅርቡ አንድ መድረክ ይዘጋጃል ብለዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች በዋነኝነት ጥቃት የሚደርስባቸው በኤርትራ ወታደሮች ስለመሆኑ መናገራቸውን ወ/ሮ ኢተነሽ ንጉሰ ተናግረዋል። የትግራይ ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አበራ ንጉሰ የተደፈሩ ሴቶች እና ልጃገረዶች በሚገኙባቸው በአክሱም፣ ዓድዋ፣ ሽረ፣ ዓዲግራት እና መቐለ ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ፣ ማይጨው ሆስፒታል በሚገኙ ዋና የሴቶች ማዕከላት መርማሪ ፖሊሶች እና አቃቢያነ ህግ አሰማርተው ለመመርመር ጥረት እያደረግን ነው ብለዋል።

አቶ አበራ እንስካሁን የአክሱም፣ የዓድዋ፣ ዓዲግራት ስቶፕ ማዕከላት መመርመር እንዳልቻሉ እና በእጃቸው ያለው የህክምና ሰነድ ብቻ መሆኑን አመልክተው ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ጥቂት መሆቸውን አስአድተዋል።

አቶ አበራ ፦

“አሁን ክስ የመሰረትንባቸው በጣም ጥቂት ናቸው። የተወሰኑ ሲቪሎችም አሉ። እስካሁ የታወቁት 10 ናቸው እስካሁን የተያዙት ሁለት የፌዴራል ፖሊስ አባላት እና አንድ ወታደር ናቸው በመያዝ ደረጃ ያለው። ያጣራናቸው የምርመራ መዝገቦች 180 ናቸው። ይህ ማለት ፈፃሚዎቹ አልተለዩም ማለት ነው ። ተደፍረው የመጡት በአጠቃላይ ቁጥራቸው 1,408 ነው እነዚህ ወደጤና ተቋማት የመጡት ብቻ ናቸው። ማነው የተደፈረው ብለን የፀጥታ ኃይል ልከን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ቤት ለቤት አሰሳ አድርገን ያመጣነው ሪፖርት አይደለም።”

አቶ አበራ ንጉሰ ጥቃት እየፈፀሙ ስላሉት አካላት የተናገሩ ሲሆን ከተደፈሩት ሴቶች ውሥጥ ከ80% በላይ በሻዕቢያ እና በኢትዮጵያ ወታደሮች ሲሆን የሚበዛውን ግን የፈፀሙት የሻዕቢያ ኃይል ነው ብለዋል።

እየተባባሰ መጥቷል ስለሚባለው የሴቶች መደፈር እና ጥቃት ጉዳይ ያሉት ነገር ባይኖርም ሰሞኑን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅ/ቤት በተሰጠ መግለጫ ላይ የተገኙት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዮስ በትግራይ ግጭት ውስጥ ተፈፅመዋል ስለተባሉ ፅታዊ ጥቃቶች እና የሲቪል ሰዎች ግድያዎች ባወታደራዊ ፍርድ ቤት ፣በክልሉ ፖሊስ እና አቃቤ ህግ ፣ በፌዴራል ፖሊስ ምርማሪዎች እና በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢሰመኮ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ገልፀው ነበር።

በተለይ ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ የደረሰበትን ደረጃ ያሳወቁት ዶ/ር ጌድዮን ፥ ወታደራዊ መርማሪዎች ፆታዊ ጥቃት በፈፀሙ እና አስገድዶ በመድፈር ወንጀል በተጠረጠሩ 25 ወታደሮች ላይ ክስ መስርተዋል፤ የክስ ሂደቱም ቀጥሏል ፣ በቅርቡ ውሳኔ ይኖራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ 3 ወታደሮች በአስገድዶ መድፈር ጥፋተኛ ተብለው ተፈርዶባቸዋል። አንድ ወታደር ሲቪል በመግደል ጥፋተኛ ተብሎ ተፈርዶበታል ብለዋል።

ስለተላለፈው የቅጣት መጠን ግን በወቅቱ ያሉት ነገር የለም።

በመከላከያ ላይ ስለሚቀርበው ውንጀላ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ እንዲሁም የኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር/ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ምላሽ እንዲሰጡበት ሙከራ ቢደረግም አልተሳካም።

ይህ ያነበባችሁት በትግራይ ሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ ስለሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት የቀረበው ሪፖርት በቪኦኤ የተዘጋጀ ነው። – tikvah ethiopia