በኢትዮጵያ የቴሌኮም ፍቃድ የተሰጠው ጥምረቱ በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛውን የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ያደረጋል ተባለ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በኢትዮጵያ የቴሌኮም ፍቃድ የተሰጠው ጥምረት በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛውን የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንደሚያደርግ የኬንያ መንግሥት ገለጸ።

ትናንት በኢትዮጵያ መንግሥት እና የቴሌኮም አገልግሎት ለማቅረብ ፍቃድ ባገኘው ጥምረት መካከል የፍቃድ ስምምነት ፊርማ መካሄዱን ተከትሎ የፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ቤተ መንግሥት በትዊተር ገጹ ላይ ጥምረቱ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት 864 ቢሊየን ሽልንግ (8 ቢሊየን ዶላር) የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ይዞ እንደሚገባ አስፍሯል።

ኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፍ እንዲሳተፍ የተቋማት ስብስብ ለሆነው ኩባንያ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ መስጠቷ ይታወሳል። በዚህም መሠረት ግሎባል ፓርትነርሽፕ ፎር ኢትዮጵያ የተባለውና የስድስት ኩባንያዎች ጥምረት የሆነው ተቋም የቴሌኮም ፍቃድ በማሸነፍ በዘርፉ ይሰማራል።

ይህን ጥምረት የሚመራው የኬንያው ሳፋሪኮም ሲሆን፤ የዩናይትድ ኪንግደሙ ቮዳፎን እና ሲዲሲ ግሩፕ፣ የደቡብ አፍሪካው ቮዳኮም፣ የጃፓኑ ሱሚቶሞ እንዲሁም ዲኤፍሲ በጥምረቱ ተካተዋል።

የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ ፒተር አንዴግዋ ጥምረቱ በኢትዮጵያ ሊያከናውን ስላሰበው ሥራ ዝርዝር ማብራሪያ ለቢቢሲ ሰጥተዋል።

ጥምረቱ ሥራውን መቼ ይጀምራል?

የሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስኪያጅ የሚመሩት ድርጅት “በኬንያ እጅግ በጣም ስኬታማ የሆነ ኩባንያ” መሆኑን ተናግረው፤ ኩባንያው ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ለመግባት የነበረው ፍላጎት የቆየ መሆኑን አስታውሰዋል። ይህንንም ለማሳካት ፍቃድ ማግኘታችን በጣም አስደሳች ነው ብለዋል።

ፒተር እንዴግዋ፤ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲሰጥ ፍቃድ ያገኘው ጥምረት ሥራውን እአአ በ2022 አጋማሽ ላይ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

“2022 አጋማሽ ላይ በኢትዮጵያ እያካሄድን ያለው የንግድ እንቅስቃሴ ይጀመራል” ብለዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ጥምረቱ ጥራቱን የጠበቀ የድምጽ እና የኢንተርኔት አገልግሎት በማቅረብ፤ የኢትዮጵያን ወደ ዲጂታል ሥርዓት የመቀየር ፍላጎትን እውን ማድረግ እና የሰዎችን ሕይወት ማሻሻል ዓላማ እንዳደረገ ተናግረዋል።

“ኢትዮጵያ የ110 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ ነች። የሕዝብ ቁጥሩ እየጨመረ ነው። አንድ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ብቻ ነው ያለው። ዝርዝር ነገር መናገር አልፈልግም። ነገር ግን ብዙ ሕዝብ ጋር ተደራሽ መሆንን ነው የምናስበው። በመጀመሪያዎቹ 5 ዓመታት አብዛኛው ሕዝብ ጋር እንደርሳለን ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።

የሳፋሪኮም ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፒተር አንዴግዋ

የፎቶው ባለመብት, SIMON MAINA = የምስሉ መግለጫ, – የሳፋሪኮም ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ፒተር አንዴግዋ

የሥራ እድል ፈጠራ

ኢትዮጵያ የቴሌኮም ዘርፏን ክፍት ማድረጓ ከፍተኛ መጠን ያለው መዋዕለ ነዋይ ወደ አገሪቱ ከማስገባቱም በላይ ለበርካቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ተነግሯል።

ፒተር እንዴንግዋ፤ ጥምረቱ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ከንግድ በተጨማሪ ለበርካቶች የሥራ እድልን ይፈጥራል ይላሉ።

“በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከ1 ሚሊዮን እስከ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ እድል ይፈጠርላቸዋል። ምርት እና አገልግሎት የሚያቀርቡ የአገር ውስጥ አቅራቢዎች ይኖሩናል። በዛ የንግድ ሰንሰለት ውስጥ በርካቶች ተሳታፊ ይሆናሉ” ብለዋል።

ዋና ሥራ አስኪያጁ ከመንግሥት ጋር በመጣመር ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት የኢንተርኔት ግንኙነት እንዲኖራቸው በማስቻል የትምህርት እና የጤና ሥርዓቱን ዲጂታል የማድረግ እቅድ አለን ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኢንቨስት የማድረግ ስጋት

በኢትዮጵያ ከጸጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ የኢንተርኔት አገልግሎት በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ይስተዋላል።

በሰሜን የአገሪቷ ክፍል ጦርነት ተከስቷል። በበርካታ የአገሪቷ ክፍልም ብሔርን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በስፋት እየታዩ ነው።

የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የደኅንነት እጦት በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ስጋት አይሆኑም? ተብለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፦

“በኢትዮጵያ ኮሚኒኬሽን ባለሥልጣን የሚተገበር የፖሊሲ ፍሬምወርክ እንዳለ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። ይህ የፖሊሲ ፍሬምወርክ በሌሎች አገራት ጤናማ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እንደምንሠራው እንድንሠራ ማረጋገጫ ሰጥቶናል” በማለት የኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ስጋት ላይሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

በትግራይ እና በተቀረው የአገሪቷ ክፍል ያለው አለመረጋጋት በንግድ ሥራው ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ በተመለከተ ደግሞ፤ “በኢትዮጵያ የምናገደርገው ኢንቨስትመንት የረዥም ጊዜ እቅድ ነው። ሰፊ እድል እንዳለ ሁሉ ተያይዞ ሊመጣ የሚችለውን አደጋም ማሰብ ያስፈልጋል። ሁልግዜም ቢሆን ወደ አዲስ አገር ሲገባ የፖለቲካ አለመረጋጋት አደጋዎች እና የማይክሮ ኢኮኖሚ አደጋዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የመገበያያ ገንዘብ አደጋዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህን አደጋዎች በሙሉ ከግምት አስገብተናል። በኦፕሬሽናችን ውስጥ ያሉ ችግሮችን እየለየ የሚያሳውቀን ኩባንያም ኮሚሽን አድርገናል” ሲሉ መልሰዋል።