መከላከያ ራሱን ነቢይ ባለው አዩ ጩፋ ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑ ታወቀ።

የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት በአዩ ጩፋ ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን አስታወቀ።

መከለከያ ሰራዊት የሁሉም ብሔሮች፣ እምነቶችና የሃገር ጋሻ ሆኖ ሳለ ፣ አልፎ አልፎ ጥቂቶች ፍላጎታቸውን ሊጭኑበት ሲፈልጉ ይስተዋላል።

በቅርቡ እዩ ጩፋ የተባለ በሐይማኖት ስም ፣ እየተከተሉኝ ነው ያላቸውን ግለሰቦች ክብር ባልጠበቀ መልኩ ከነ ዩኒፎርማቸው በቪዲዮና ፎቶ ቀርፆ በአደባባይ እንዲሰራጭ አድርጓል።

ይህ የሰራዊቱን ስምና ታማኝነት በማሳጣት ለግል ፍላጎትና ጥቅም በማን አለብኝነትና ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ለፈፀመው ድርጊት መከላከያ በህግ ለመጠየቅ መዘጋጀቱን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አረጋግጠዋል ።

ጥቂት የሰራዊታችን አባላትም ይህን ፍላጎት ለማሟላት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መለያ የሆነውን ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ እንደነበሩ ተረጋግጧል።

May be an image of 1 person and standingተሳታፊዎቹም በመከላከያ ወታደራዊ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተይዘውና ታስረው ጉዳያቸውን ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የማጣራት ስራ እየተሰራ ይገኛል።

በዚህ አይነት ጥፋት ከዚህ ቀደምም በተለያዩ የእምነት ተቋማት የተገኙ አባላት ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዶ እንደነበረ ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።

ወደፊትም ፣ ማንኛውም የሰራዊት አባል የየትኛውም እምነት ተከታይ ቢሆን በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ ተሳትፎ ከተገኘ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል ።

የእምነት ተቋማትና መላ ህዝባችን ዩኒፎርማችንን ለብሶ በእምነት ተቋማት፣ በህዝባችን ነውር በተባሉ የመጠጥ ፣ የሱስ ፣ የቁማር ወዘተ ቦታዎች የሰራዊት አባልም ሆነ አስመሳይ ዩኒፎርም ለባሽ ሲመለከት እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል።

ሰራዊታችን ፣ በጋብቻና በቀብር ጊዜ ፣ በእምነት ቦታዎች ክብሩን በጠበቀ መልኩ የሚከወኑ ስርዓቶች መኖራቸውና ሰራዊቱም እምነት ካለው ህዝብ የወጣ በመሆኑ ፣ በየግሉ ሐይማኖት ያለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በኛ በኩል በህጋችን የተፈቀዱና የተከለከሉ ጉዳዮችን በውስጣችን የማስረፅ ስራም ይሰራል ብለዋል።

ኮሎኔል ጌትነት ፣ ሰራዊታችን በህግ የተቀመጡለትን ትዕዛዞች አክብሮ ግዳጁን ሲወጣ የነበረና እየተወጣ ያለ ተቋም በመሆኑ ይህንንም አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።

ከግዳጁ ጎን ለጎንም የችግር ደራሽ በመሆኑ ፣ ሰሞኑን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዞኖች በተለይም በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ከሚሴ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን የተጀመረውን የገንዘብ ድጋፍ ፣ በጉልበትና በዕውቀት የማገዝ ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አረጋግጠዋል።