ትግራይ ህዝቡ ካለበት ችግር አንጻር እየተሰጠ ያለው የእርዳታ ምላሽ እጅግ አናሳ መሆኑ የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቻችን አስታወቀውናል – ተመድ

“…ህዝቡ ካለበት ችግር አንጻር እየተሰጠ ያለው የእርዳታ ምላሽ እጅግ አናሳ መሆኑ የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቻችን አስታወቀውናል” – ተመድ

ተመድ ፥ በትግራይ ክልል በችግር ላይ ላለው ህዝብ ሰብዓዊ ረድዔት በነጻነት ተንቀሳቅሶ ለማቅረብ የሚደረገው ጥረት በሀገሪቱ ባለው ውስብስብ እና የማያስተማምን የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት አሁንም መስተጓጎሉ እንደቀጠለ ባልደረቦቻችን ገልጸውልናል ሲል አስታውቋል።

ተመድ ይህን ያለው በዚህ ሳምንት በሰጠው መግለጫ ነው።

የተመድ ዋና ጸኃፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርኻን ሃቅ ፥ “በክልሉ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ 6 ወር በተጠጋው በዚህ ወቅት አብዛኛው የገጠሩ አካባቢ አሁንም የኮሙዩኒኬሽንና የኤሌክትሪክ አገልግሎቶች እንደሌለው ይህም የጤና አገልግሎቶች እና የውሃ አቅርቦት ሌላም አገልግሎት እንዳይደርስ አድርጓል” ብለዋል።

የተመድ ዋና ጸኃፊ ምክትል ቃል አቀባይ ፋርኻን ሃቅ

የክልሉ ህዝብ ያለበት የምግብ ችግር አሁንም እጅግ የከበደ እንደሆነ የተናገሩት ምክትል ቃል አቀባይ ሃቅ ፥ “በመላዋ ትግራይ በእኛ ግምት 4.5 ሚሊዮን ህዝብ የምግብ እርዳታ የሚጠብቅ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ድርጅታቸው ከሌሎች የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቹ ጋር ሆኖ ለዚህ ችግር የሚሰጠውን ድጋፍ ማሳደጉን እንደቀጠለ ገልጸው ይህም የጾታዊ ጥቃቶች ሰለባዎች መለየት እና አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግን ያካትታል ብለዋል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ድርጅት ካለፈው እ.አ.አ መጋቢት ወር ወዲህ ባከፋፈለው 9 ሽህ ቶን ምግብ በክልሉ በሰሜን ምዕራብ እና በደቡባዊ ዞን 529 ሺህ ነዋሪዎች ሊያደርስ መቻሉን በእዳጋ ሃሙስ እና አጺቢ ከተሞች ለ34 ሽህ ህዝብ የምግብ እርዳታ ማከፋፈሉን እና ባለፈው ሳምንት ከ7 መቶ ሺ በላይ ህዝብ ውሃ የማጓጓዝ አገልግሎት መሰጠቱን ዘርዝረዋል።

ቃል አቀባዩ ፥ “የረድዔት አጋሮቻችን እስካሁን ለ285 ሽህ ተፈናቃዮች የመጠለያና ምግብ ያልሆኑ ቁሳቁስ እርዳታዎችን አድርሰዋል፤ ይህ ግን በእርዳታ ዕቅዳችን ካቀድነው የህዝብ ቁጥር አስር ከመቶው ብቻ ነው” አመልክተዋል።

አስከትለውም ፥ መቐለ ከተማ ውስጥ ከ19 ሽህ በላይ ሰዎች ለማስጠለል የሚችል የተፈናቃዮች ካምፕ የማዘጋጀቱ ሥራ እንደቀጠለ ተናግረዋል።

ህዝቡ ካለበት ችግር አንጻር እየተሰጠ ያለው የእርዳታ ምላሽ እጅግ አናሳ መሆኑ የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቻችን አስታወቀውናል በሚፈለገው መጠን እርዳታ ለማቅረብ ገንዘብ እና ባልተገደበ እና የደህንነት ጥበቃ ባልተለየው መልኩ ተረጂው ህዝብ ጋር መድረስ መቻል ይኖርብናል ብለዋል።

ምንጭ ፦ ቪኦኤ