ቀን ተኝተው የሚውሉ ኤርትራውያን ስደተኞች ለሊት ለሊት የነዋሪዎችን ሰላምና ደሕንነት እየረበሹ የዜጎችን የመኖር መብት እየተጋፉ መሆኑ ተሰማ።

አንዳንድ ኤርትራውያን ስደተኞች የኮንዶሚኒየም ነዋሪዎችን በማፈናቀልና ሰላም በመንሳት ቅሬታ ቀረበባቸው

በሦስት ወራት 156 ኤርትራውያን በወንጀል ተጠርጥረው ታስረዋል

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል መንግሥት ገንብቶ ባስተላለፋቸው  የጋራ የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ  አንዳንድ ተከራይ ኤርትራውያን ስደተኞች፣ የኅብረተሰቡን ሰላም በመንሳትና  ተከራዮችን በማፈናቀል ከነዋሪዎች ቅሬታ ቀረበባቸው።

ሪፖርተር በአያት፣ በባልደራስ፣ በጎተራና በጎፋ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም  በመገኘት ስለሚባለው ነገር ለማጣራት ጥረት አድርጓል።

ምንም እንኳ በአያትና በባልደራስ አካባቢ በሚገኙ የካና ፈረስ ቤት  ኮንዶሚኒየሞች በቅርቡ  ከትግራይ ክልል ሕግ ማስከበር ጋር ተያይዞ በክልሉ አዲሀሩሽና ሽመልባ ከተባሉ የስደተኞች መጠለያ ካምፖች ለቀው የመጡትን ጨምሮ በርካታ የኤርትራ ስደተኞች ተከራይተው እንደሚኖሩና ችግሩ አልፎ አልፎ  ቢኖርም፣ የከፋ እንዳልሆነ ከነዋሪዎቹ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይሁን እንጂ በጎተራና በጎፋ መብራት ኮንዶሚኒየሞች የሚኖሩ የኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የተባለው ችግር ስለመኖሩ፣ ከነዋሪዎች አንደበት ማረጋገጥ ተችሏል።

በጎተራ ኮንዶሚኒየም ግቢ ውስጥ የጀበና ቡና የምትሸጥ ትዕግሥት መኩሪያ (ለደኅንነቷ ሲባል ስሟ የተቀየረ) ስለጉዳዩ ስትናገር፣ አብዛኛውን ጊዜ ኤርትራውያኑ ስደተኞች በቡድን ይንቀሳቀሳሉ ትላለች፡፡ ቀን ቤት ተኝተው የሚውሉ በመሆናቸው  ነዋሪዎች ቀን ሠርተው በምሽት በሚተኙበት ጊዜ፣ ስደተኞቹ ሌሊት በመጮህ የግቢውን ሰላም እንደሚነሱት አስረድታለች፡፡

ከዚህ ባለፈ ሰዎች ባሉበት ሥፍራ መንግሥት ሲጋራ እንዳይጨስ ሕግ ያወጣ ቢሆንም፣ ስደተኞቹ በዛ ብለው ተቀምጠው ስለሚያጨሱ ልጆችና ሕፃናት እንደፈለጉ መንቀሳቀስ አይችሉም በማለት ገልጻለች፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቱ አስተዳደር ኮሚቴ አባል የሆኑና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ ግለሰብ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ፣ በጎተራ ኮንዶሚኒየም ካሉ 2,457 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሩብ የሚሆነው በኤርትራውያን ስደተኞች በኪራይ ተይዟል፡፡

ከውጭ አገር በሚላክ ዶላር ሕይወታቸውን የሚመሩት ኤርትራውያን ያለ ምንም ድርድር ከአከራይ እንዲከፍሉ የተጠየቁትን በመክፈል በቡድን እስከ ሰባት አንዳንዴም ከዚያም በላይ ስለሚኖሩ፣ ኢትዮጵያዊ ሠርቶ አደር የተከራየውን ቤት ባልተገባ ጭማሪ ምክንያት ሳይፈልግ በግድ ከሚኖርበት ቤትና አካባቢ ለቆ እንዲወጣ እየተደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በስደተኛ መታወቂያ የሚከራዩት ኤርትራውያን በተለይም በቅርቡ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ዕርቅ አወረድኩ ካለ ጀምሮ የቤት ፈላጊዎቹ ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ እንደሆነ፣ ቢያንስ አምስት ኤርትራዊያን ስደተኞቹ በየቀኑ ለመከራየት ወደ ግቢው እንደሚመጡ አክለው አስረድተዋል፡፡

ለነዋሪዎቹ የኤርትራዊያን ስደተኞች ቁጥር መብዛት ችግር እንዳልሆነ የጠቆሙት የኮሚቴው አባል፣ አሳሳቢ ሆኗል ያሉት  የሌሊት ጭፈራቸውና ሰላም ከመንሳት ጋር ተያይዞ ለአንድ ኮንዶሚኒየም ቤት ባልተገባ የኪራይ ዋጋ እስከ 27,000 ብር በመክፈል፣ በሰላም ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ማፈናቀላቸው  እንደሆነ ገልጸዋል።

የጎተራ ኮንዶሚኒየም መኖሪያ ሳይት የነዋሪዎች ጉባዔ ስለጉዳዩ ለመነጋገር ቢፈልግም፣ በኮቪድ-19 ምክንያት መሰብሰብ እንዳልቻለና በቅርቡ በሚያደርገው ስብሰባ እንድ አቋም ላይ እንደሚደርስ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከጎረቤት አገር ሶማሊያ የመጡ ስደተኞች ተመሳሳይ ዓይነት ችግር በነዋሪው ላይ  ሲያደርሱ እንደነበር፣ በመጨረሻ ግን ጉባዔው ተወያይቶ ላለማከራየት ወስኖ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‹‹አሁን ኤርትራውያንን አናከራይም እንዳንል መንግሥት መደመር ብሎ በሩን ከፍቶታል፣ ስናከራይ ደግሞ ሌላ ችግር ይመጣል፡፡ ሕዝቡ ተረበሽን እያለ ይጮሃል፡፡ በመሆኑም ችግሩን መንግሥት ካልፈታው ነዋሪው ራሱ ሊፈታው ይገባል፤›› ብለዋል።

ችግሩ ሰፋ ያለበትና ከአጠቃላይ 5,400 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በትንሹ 50 በመቶ የሚሆኑትን የኤርትራ ስደተኞች እንደሚኖሩበት፣ ለበርካታ ሰዎች መፈናቀልና ሌሊቱና ቀኑ የተደበላለቀበት ዓይነት ኑሮ የሚኖርበት አካባቢ እንደሆነ የተነገረለት ደግሞ የጎፋ መብራት ኃይል ኮንዶሚኒየም ነው።

ሪፖርተር በቦታው ተገኝቶ ከነዋሪዎችና ከመኖሪያ ቤቶቹ አስተዳዳር እንዳሳሰበው መረጃ፣ በስደተኛ ካርድ የሚኖሩ ኤርትራውያን በሺዎች ይቆጠራሉ፡፡ ብዙዎቹ ከቀን ይልቅ ሌሊት መንቀሳቀስ እንደሚያበዙ አንድ በዕድሜ ገፋ ያሉ ነዋሪ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ አከራዮች ኤርትራውያኑን ያለ ምንም ይሉኝታ በተጋነነ  ዋጋ በአንድ ቤት እስከ 30,000 ብር ድረስ በወር እንደሚያከራዩ፣ ተከራዮቹም ያለ ቅድመ ሁኔታ ስለሚከፍሉ በተመጣጣኝ ዋጋ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሳይፈልጉ እየተፈናቀሉ እንደሆነ አንድ ስማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይጠቀስ የፈለጉ የጋራ መኖሪያ ቤት የኮሚቴ አባል ገልጸዋል፡፡

በጎፋ መብራት ኮንዶሚኒየም ግቢ  በርካታ ኤርትራውያን የያዙ ‹‹አባ ሻውል›› እና ‹‹እንደ ሃራ›› ተብለው የተሰየሙ ሠፈሮች፣ በተለይም ከብሎክ 19 እስከ 39 ያሉት  የኤርትራ ስደተኞች ዋነኛ መንደር መሆናቸውን ተናግረዋል።

‹‹የነዋሪዎች አቤቱታ በዝቶብናል፤›› ያሉት የኮሚቴው አባል፣ ‹‹መንግሥት ከውጭ የሚያገኘው ዶላር ይቀርብኛል በሚል ብቻ ጉዳዩን በዝምታ ሊያልፈው አይገባም፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ ኤርትራውያን ወጣቶች ተደራጅተው ለመዝረፍ እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ አክለው ገልጸዋል።

በጎፋ ኮንዶሚኒየም በርከት ላሉ ዓመታት ተከራይቶ እየኖረ ያለ አንድ ኤርትራዊ ስለጉዳዩ ለሪፖርተር ሲናገር፣ ችግሩ በተደጋጋሚ እንደሚነሳና አከራዮች ከማከራየታቸው በፊት በግቢው ውስጥ መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች አስጠንቅቀው ማስገባት አለባቸው ብሏል፡፡ ‹‹እዚያ ማዶ ሆነው በባንክ የሚላከውን ገንዘብ ከመሰብሰብ፣ ግቢው የጋራ በመሆኑ እየመጡ ነገሮችን መከታተል አለባቸው፤›› በማለት ያስረዳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ ስለጉዳይ ሪፖርተር ጠይቋቸው በሰጡት ምላሽ፣ ባለፉት ሦስት ወራት በተለይም መንግሥት በትግራይ ክልል  የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረ ወዲህ በርካታ ኤርትራውያን ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል ብለዋል፡፡ ከገቡ በኋላም እርስ በርሳቸውና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመጣላት በተደጋጋሚ ለፖሊስ አቤቱታ  እንደሚቀርብ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በሦስት ወራት ብቻ በቡድን ፀብ፣ በስርቆት፣ ደንብ በመተላለፍና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር ባለመግባባት ፖሊስ 156 ኤርትራውያንን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ገልጸዋል፡፡ አንዳንዶቹን ለጥቂት ቀናት አስሮ በማስተማር በዋስትና እንደተለቀቁ፣ ሌሎች ደግሞ በወንጀል ተከሰው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ እንደሆነ ኮማንደር ፋሲካ አስረድተዋል፡፡

ከትግርኛ ውጪ ሌላ ቋንቋ የማይችሉ አንዳሉ በመረዳት ፖሊስ ከ800 በላይ ብሮሸሮችን በየቦታው በመለጠፍ፣ እንዲሁም ኮሚቴ በማቋቋም የመስተማር ሥራ በማከናወን ላይ ስለሆነ ችግሩ የመቀነስ አዝማሚያ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

መታወቂያ የሌላቸው እንዳሉ የተነገረ ሲሆን ፖሊስ ሲያገኛቸው ወደ ስደተኞች ኤጀንሲ የማስገባት ሥራም እንደተከናወነ ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡

ይሁን አንጂ ፖሊስ ኤርትራውያኑ ወንጀል እንዳይፈጽሙ መጠበቅ፣ ፈጽመው  ሲገኙ በማስተማርና በመቅጣት ዕርምጃ የመውሰድ ሥራው እንደሚቀጥል አክለው ገልጸዋል፡፡

ቤቶቹን ከተፈለገው አገልግሎት ውጪ በተለይም ወደ እንግዳ ማረፊያነት በመለወጥ ስለሚያከራዩ የኮንዶሚኒየም ባለቤቶችን በተመለከተ፣ ለአዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር በመደወል ለማጣራት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

በቅርቡ በትግራይ ክልል ሕፃፅና ሽመልባ በተባሉ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የነበሩ 20,000 የሚጠጉ ኤርትራውያን ስደተኞች፣ መንግሥት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያከናውን በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ የመጠለያ ጣቢያዎቹን ለቀው እንደወጡ መገለጹ ይታወሳል፡፡