ከቅንጅት ተሳትፎ በማግለል የእናት ፓርቲን እንቅስቃሴ መገደብ አይቻልም!
የእናት ፓርቲን ከቅንጅት መሰረዝ አስመልክቶ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳለፈው ውሳኔ ላይ የተሰጠ መግለጫ
እናት ፓርቲ አገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ የምዝገባ ምስክር ወረቀት ካገኘበት ከ 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአጭር ጊዜ ዝግጅት በምርጫ በመሳተፍ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩዎችን በማስመዝገብ ቀላል የማይባል የመራጮች ድምፅ አግኝቷል። ከምርጫው በኋላም ባሉት ዓመታት መንግሥት የሚሄድባቸውን ሕገ ወጥ አሰራሮች አብዛኛዎቹን ለሕዝባችን ይፋ በማድረግና በመተቸት እንደ ጣሪያ ግድግዳ ያሉ በማን አለብኝነት በሕዝብ ላይ የተጫነ ቀንበርን ደግሞ ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ እና ክርክር አድርጎ በመርታት ላለፉት 5 ዓመታት አፉ ተለጉሞ ስለመብቱ እንዳይናገር ለተፈረደባት ሕዝባችን ድምጽ ሆኖ ቀጥሏል። በዚኹ ጊዜ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች በሕዝባችን ላይ የሚደርሰውን ስቃይ፣ መከራ፣ ስደትና ግድያ ከምንጩ መረጃዎችን በመሰብሰብና ለሕዝብ፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ለመገናኛ ብዙኃን በማሳወቅ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ይገኛል።
ፓርቲያችን ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለገዢው ፓርቲ ከሰላሳ ዓመታት በላይ በስልጣን ተቆናጦ በአምባገንነት መቀጠል ምሥጢር የገዢው ፓርቲ ጥንካሬና ገዥ ሀሳብ ይዞ መገኘት ሳይኾን የተቃውሞው ጎራ የተበታተነ መኾን እንደኾነ በመረዳት ከስድስተኛ ዙር አገር አቀፍ ምርጫ ዝግጅት ጊዜ ጀምሮ ከፓርቲያችን ጋር ተቀራራቢ ምልከታ ያላቸውን አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች በማቀራረብ የምርጫ እንቅስቃሴያችን እንዲቀናጅ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ይሁን እንጂ በወቅቱ በሰፈነው የተጋነነ የእኔነት/የትልቅነት እሳቤ የተፈለገውን ጥምረት መፍጠር ያልተቻለ ቢሆንም ከመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጋር የምርጫ እንቅስቃሴውን ለማቀናጀት ጥረት በማድረግ በጎ የሚባል መሠረት ለመጣል ሞክሯል። ከምርጫ 2013 በኋላ ፓርቲያችን ተስፋ ባለመቁረጥ የተቃውሞው ጎራውን በድጋሚ በማሰባሰብ በጋራ ለመታገል ያቀረበው የአብረን እንሥራ ጥሪ በአብዛኞቹ አገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎች የተገፋ ቢሆንም ከመኢአድ እና የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ጋር የትብብር መግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ላለፉት አራት ዓመታት በትብብር ሲሰራ ቆይቷል። የትብብሩን በጎ ጎዳና የተመለከቱ አንድ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ትብብሩን በሂደት በመቀላቀል አምስት ፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈና ጠንካራ መሰረት የጣለ ትብብር ፈጥረን ስንንቀሳቀስ ቆይተናል።
ትብብሩ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም በመያዝ ጠንካራ የሕዝብ ድምጽ መሆን የቻለ ሲሆን ይህ አቋሙና አካሄዱ ፓርቲውን እና የትብብሩን አባል ፓርቲዎችን በገዥው ፓርቲም ሆነ በመንግሥት በጠላትነት እንዲፈረጁ አድርጓል። የገዥው ፓርቲና መንግስት እንደዚህ አይነት እሳቤ ፓርቲያችንን ሳይገድብ ሕዝባችን ለተከታታይ ዓመታት “ተባበሩ ወይም ተሰባበሩ” በማለት ለሚያስተጋባው ጥሪ ትብብሩ ሕጋዊ መልክ ይዞ በአዋጅ በተደነገገው መሠረት ወደ ቅንጅት እንዲያድግ እናት ፓርቲ ከሌሎች የትብብሩ አባል ፓርቲዎች ጋር ጋር ከፍ ያለ ጥረት በማድረግ መስከረም 10 ቀን 2018 ዓ.ም. ሦስት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተወካዮች በተገኙበት ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በይፋ ተመስርቷል። በቅንጅቱ ምስረታ ዝግጅት ወቅት የቅንጅቱ አባል ለመሆን የየፓርቲዎቹ የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅትን ለመፍጠር ያሳለፉትን ውሳኔ ቃለ ጉባኤ እና የሚመሠረተው ቅንጅት ረቂቅ መተዳደሪያ ደንብ ለምርጫ ቦርድ ተልኮ ቦርዱም ሰነዶቹን ከመረመረ በኋላ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ብቻ መጠነኛ ማስተካከያዎች እንዲደረጉ በማሳሰብ የቀረቡለትን ሰነዶች መርምሮ በቅንጅቱ መስራች ጉባኤ ተገኝተው የሚታዘቡ ሠራተኞቹን ልኳል። እነዚሁ የቦርዱ ተወካዮች በታዛቢነት በታደሙበት ጉባዔ በዕለቱ የቅንጅቱ ምስረታ ተፈጽሟል።
የቅንጅቱ ምስረታ በዚህ መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ በሁለተኛው ቀን መስከረም 12 ቀን 2018 ዓ.ም. አስፈላጊ ሰነዶች በሙሉ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሸኚ ደብዳቤ ገቢ የተደረጉ ቢሆንም ቦርዱ ከእጅግ ብዙ ውትወታና ደጅ ጥናት በኋላ በ55 ኛው ቀን ኅዳር 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የሰባተኛ ዙር ምርጫ እጩዎች ምዝገባ ጥሪ ለማድረግ ኹለት ቀናት ብቻ ሲቀረው ለፓርቲያችን እንዲደርስ ባደረገውና ለቅንጅቱ አባል ፓርቲዎች በተጻፈ አምስት ገጽ ደብዳቤ የአራቱን ፓርቲዎች ቅንጅት ምስረታ ሲያጸድቅ እናት ፓርቲ ያስገባው ሰነድ የተሟላ አይደለም በማለት ፓርቲያችንን ከቅንጅቱ አባልነት ሰርዟል።
እናት ፓርቲን ከቅንጅት አባልነት ለመሰረዝ ቦርዱ ያቀረበው ሰንካላ ምክንያት ለቅንጅት ምስረታ ፓርቲያችን ያቀረበው ጉባኤ ያልተሟላ እና “ከአባላት በቀረበ ተቃውሞ” (ለፓርቲው ባልደረሰ ወይንም ግልባጭ ባልተደረገ ደብዳቤ) መሆኑን ገልጿል። በኹለቱም መልኩ ቦርዱ የሰጠው ምክንያት ተቀባይነት የሌለው ሲሆን ለ 14 ወራት ፓርቲውን ለማፍረስ ሲደረግ የከረመው ጥረትና ቦርዱ በአጋፋሪነት ሲመራ የነበረውን ይህንኑ ተግባር ለማስፈፀም በዕቅድ የተሠራ መሆኑን እናት ፓርቲ ለሕዝባችን ይፋ ሊያደርግ ይወዳል። ይኸው ፓርቲውን የማፍረስ ሥራ በነዚህ አሥራ አራት ወራት፡-
ፓርቲው በእለት ተእለት ተግባሩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንዳይሰራ ረብ በሌለው የድብዳቤ ምልልስ ቦርዱ ፓርቲውን ሲያዳክም የከረመበት፤
የፓርቲው ምክር ቤት የተጣለበትን ኃላፊነት እንዳይወጣ እንቅስቃሴውን በመገደብ፤
ያልባከነ የፓርቲውን 38,500 (ሰላሳ ስምንት ሺህ አምስት መቶ) ብር እንደባከነ አድርጎ በማቅረብ የ 2017 በጀት ዓመት በጀት በመከልከል፤
ይህንኑ ባከነ ያለውን “ላም ባልሆነበት ኩበት ለቀማ” እንዲሉ ያልባከነ ገንዘብ አባከኑ ባላቸው የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲካሄድ በማዘዝና (የቦርዱ የራሱ የዋና ኦዲተር ግኝት በወንጀል ምርመራ እንዳልተያዘ ልብ ይሏል) በመሳሰሉት አፍራሽ ተግባራት ሲሠራ የከረመ ቢሆንም ፓርቲያችን ይህን ገመድ ጉተታ ወደ ጎን በመተው በዋና ተግባሩ ላይ ብቻ ለማተኮር ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
የደብዳቤ ምልልሱ በቀጠለበትና ፋይዳ እንደሌለው ፓርቲያችን በተረዳ ጊዜ ከቦርድ ሰብሳቢ ጋር የፓርቲያችን ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ በአካል ቀርቦ መወያየትና ችግሮች ካሉ በውይይት ለመፍታት ቀጠሮ የጠየቀ ቢሆንም በብዙ ደጅ ጥናት ከ25 ቀናት በኋላ ሊመቻች በቻለው ስብሰባ (የስብሰባው አሳሳቢ ፓርቲያችን እንደመሆኑ) ስብሰባውን የጠየቅንበትና የመጣንበት ምክንያት እንዲሁም ቅሬታችን በፓርቲያችን ፕሬዚደንት አማካይነት ማብራሪያ ተሰጥቶ እንዳበቃ የተነገረው እውነታ በእጅጉ የጎመዘዛቸው የቦርዱ አመራሮች “ከዚህ በላይ ለመስማት ፈቃደኛ አይደለንም” በማለት የዲሞክራሲ ግንባታ ተቋማት ተብለው ከሚጠቀሱት ተቋማት አንዱ የሆነው የቦርዱ አመራሮች አሳፋሪ በሆነ መልኩ ሥራ አስፈጻሚውን በራሳቸው አዳራሽ ውስጥ ትተው ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን ዛሬ ላይ መግለጽ ተገቢ ይሆናል። እናት ፓርቲ በተቋማት መካከል ያለው ግንኙነት የጌታና የሎሌ ሳይሆን በሕግ እና በሕግ አግባብ ብቻ የሚመራ ግንኙነት መሆን እንደሚገባውና ከዚያ የዘለለ ነገር ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ያምናል።እናት ፓርቲን ከቅንጅቱ አባልነት ለማስወጣት የተወሰደው እርምጃ ቦርዱ በፓርቲው ዝርዝር አሠራር እጁን በማስገባት እና አንጃ ፈጥረው ራሳቸውን ከለዩና ፓርቲውን ለማፍረስ እለት ተእለት ለሚተጉ ስምንት የቀድሞ አባላት አይዞአችሁ ባይ በመሆንና አንደኛው የተማሰ ጉድጓድ ሲደፈን አጋዥ ሆኖ ሌላ ጉድጓድ እየፈጠረ የመሄዱ አንዱ ማሳያ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
ቦርዱ የእናት ፓርቲ የቅንጅት ቃለ ጉባዔ በላዕላይ ምክር ቤት አልተወሰነም ያለበትን አስመልክቶ የፓርቲያችን የምክር ቤት አባላት ቁጥር በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት 36 ቢሆንም በሞት፣ በሚደርስባቸው ዛቻ እና ማስፈራራት ምክንያት በመልቀቅና ሦስት የምክር ቤት አባላት ደግሞ በከፍተኛ የሥነ ሥርዓት ጥሰት በመባረራቸው የፓርቲያችን ላዕላይ ምክር ቤት አባላት ወቅታዊ ቁጥር መጋቢት 9 ቀን 2017 ለቦርዱ በተጻፈ ደብዳቤ በግልጽ የተብራራ ሲሆን ቦርዱ ይህን አስመልክቶ ለስምንት ወራት ማለትም እስካሁን የሰጠው ምላሽ አለመኖሩ ማብራሪያውን ተቀብሎ ያጸደቀው መሆኑን የሚያሳይ ነው። ምክር ቤቱም ከዚህ ጊዜ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት ስብሰባ አድርጓል። በተመሳሳይ መልኩ ቦርዱ በፓርቲው ውስጥ ተከስቷል ባለው ችግር ዙሪያ በሥነ ሥርዓት ጥሰት ምክንያት ከምክር ቤቱ እና ከፓርቲው በተሰናበቱት የቀድሞው የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የምክር ቤቱ ስብሰባ ተጠርቶ የቦርዱ ተወካዮች በታዛቢነት በተገኙበት ለተከሰተው ችግር እልባት እንዲሰጥ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ መመሪያ የሰጠ ሆኖ ሳለ ተጠቃሾቹ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ ስብሰባ እንዲጠሩ ሥራ አስፈጻሚው ኹለት ጊዜ በደብዳቤ ቢያሳስብም ስብሰባ ጠርተው ምክር ቤቱን ማወያየት ባለመቻላቸው ምክር ቤቱ የተሰናበቱ ሰዎች ግዞተኛ ሆኖ መቀጠል እንደሌለበት በማመን ቀደም ሲል ያሳለፈው ውሣኔ እንዲፀና ለቦርዱ መጋቢት 12 ቀን 2017 ለጻፈው ደብዳቤ ቦርዱ ምንም ምላሽ ያልሰጠና ስብሰባ እንዲጠራ መመሪያ የተሰጠው አካል በምን ምክንያት ስብሰባ ሳይጠራ እንደቀረ ማብራሪያ እንዲሰጠን ለቦርዱ ላቀረብነው ጥያቄ ቦርዱ ምንም ምላሽ ያልሰጠና ባሳለፈው ውስኔ መሠረት ስብሠባው ባለመካሄዱ የወሰደውን እርምጃ ለፓርቲው አለማሳወቁ ወይንም ሆን ብሎ ከዚህ ለማፈግፈግ መሻቱ ፓርቲውን የማፍረስ ሥራ በስምንት የፓርቲው የቀድሞ አባላት እየተመራና በቦርዱ ድጋፍ እየተቸረው በመከናወን ላይ መሆኑን ፓርቲያችን ለመረዳት ችሏል። ይህ ደግሞ ፓርቲያችንን ይበልጥ ያጠነክረው ካልሆነ በስተቀር በምንም ዓይነት መልኩ እንደማያንበረክከው ለመግለጽ እንወዳለን።
እናት ፓርቲ በቅንጅቱ እንዳይቀጥል የተኬደበት መንገድም የዚሁ ተልዕኮ አካል እንደሆነ ፓርቲያችን ያምናል ከሕግ አግባብ ውጭ እየተገፋ ያለውን መብቱንም በሕግ ለማስከበር አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳል።
እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ!
እናት ፓርቲ.
ኅዳር ፲ ቀን ፳፻፲፰ ዓ. ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ