ኦህዴድ አገር አቀፍ ካልሆነ ለዶ/ር አብይና አቶ ለማ አይመጥንም #ግርማ_ካሳ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የሕወሃት/ኦህዴድ ኢሕአዴግ ፖሊሲ ሁሉንም ነገር የሚያየው በ”ብሄር ብሄርሰብና ሕዝብ” በሚለው መነጽር ዉስጥ በመሆኑ፣ በሚሊዮኖች የምንቆጠር ፣ ዘራችን ኢትዮጵያዊነት ነው በምንል ዜጎች ላይ የፈጸመው የሕልዉናና የመብት ረገጣ አንዱ የዘር ፖለቲካው ጦስና ጣጣ ሲሆን፣ ፣ ሌሎችም ያስከተላቸው መዘዞች አሉ።

አሁን በዶ/ር አብይ የሚመራዉ ኢሕአዴግ በአቶ ሃይለማሪያምና በአቶ መለስ ይመራ ከነበረው ኢሕአዴግ ዘር ተኮር ፖሊሲዎችን በማስተካከል ረገድ ያን ያህል ያደረገውን ተግባራዊና ተቋማዊ እንቅስቃሴ የለም።አሁንም የዘር አሰራሩ፣ አሁንም የዘር አወቃቀሩ፣ አሁንም የዘር አደረጃጃቱ እንዳለ ነው።

ዶ/ር አብይ ለኦሮሞዎች ብቻ የቆመውንና ኦሮሞዎችን ብቻ ያቀፈውን ኦህዴድን ይዘው ከብአዴንና ከድሃዴን ጋር በመሆን፣ ኢሕአዴግን አክስመው፣ አንድ ትልቅ አገር አቀፍ ድርጅት በመመስረት፣ ከዘር አደረጃጀት ወደ አገራዊ አደረጃጀት ይመጣሉ የሚል ተስፋ ነበረኝ። ተስፋ ብቻ ሳይሆን ቀደም ሲል ይደርሰኝ የነበረው ውስጣዊ መረጃ ያንን ነበር የሚያመለክተው።

ሆኖም ግን በተለይም አብዛኛው ኦነጋዊ አስተሳሰብ ያለው የኦህዴድ ታችኛውና መካከለኛው አመራር በኢትዮጵያዊነት ስር መንቀሳቀስ ኦሮሞነትን ማሳነስ ወይንም ኦሮሞን መጉዳት ስለመሰለው ፣ እንደ ኦነግ፣ ኦዴፍ ባሉ የኦሮሞ ብሄረተኛ ድርጅች፣ እንደ ጃዋር በመሳሰሉ አክቲቪስቶች ግፊት፣ የኦህዴድ ከሌሎች ጋር ወደ አገር አቀፍ ድርጅት መሸጋገሩን አልወደዱትም። (ልክ ኦፌኮ በመድረክ ውስጥ ሲንቀሳቀስ ሌሎች እንዋሃድ ሲሉ ከተዋሃድኩ ድጋፍ አጣለሁ ብሎ ዉህደትን እምቢ ሲል እንደነበረው) ።
ከዚህም የተነሳ ኦህዴድ ወደ አገር አቀፍ ድርጅት የመቀጠል እድሉ በጣም ጠባብ እንደሆነ እየሰማን ነው። የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ደርጅት የሚለው ስም ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ወደሚል ለመቀየር ብቻ እንደታሰበ ነው እየሰማን ያለነው። ይሄ ደግሞ ተኩላው ሊሄድ ነው ተብልን ጅቡ መጣ እንደማለት ነው።ኦህዴድም ኦዴፓም ያው ነው የሚሆኑት። ሁለቱም ለኦሮሞ ብቻ የቆሙ፣ ሁሉቱም የጎሳ ድርጅቶች። ኦሮሞውን ብቻ ያቀፉ ከሆኑ ኦህዴድ የሚለውን ስም መቀየሩ ለምን እንዳስፈለገም አይገባኝም።

ኦህዴድ አገር አቀፍ ሆኖ ፣ ከሌሎች ጋር ተዋህዶ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ማቀፍ ካልቻለ፣ ዶ/ር አብይና አቶ ለማ ኦህዴድ አይመጥናቸውም። በኦህዴድ የተሰገሰጉ ኦነጋዉያንን እዚያው ለበሰበሰውና በሽተኛው ኦነግ ትተው፣ አገር ወዳድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆችን በመያዝ፣ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር፣ ታላቂቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት የጀመሩትን ጉዞ ይቀጥሉ ዘንድ እመክራለሁ።

የዘር ፖለቲካው ከመቼዉም ጊዜ በላይ ዜጎች ጠባብ እንዲሆኑ የሚገፋፋ ነው። ለምሳሌ በሁሉም ባይሆን በብዙ የኦሮሚያ አካባቢዎች ላለፉት 25 አመታት ወጣቶች አማርኛ በበቂ ሁኔታ እንዳይማሩ ተደርጎ፣ ከሌላው ማህበረሰብ ጋር የሚገናኙበት መስመር ተበጥሶ፣ የአባቶቻቸዉን የነአቡን ጴጥሮስ (አባ መገር) ፣ የነባልቻ አባነፍን፣ የፊታወራሪ ሃብተሚክኤል ዲነግዴን፣ የነእቴጌ ጣይቱን ፣ የነአብዲሳ አጋን ….… አኩሪ የጀግንነት ገድል ሳይሆን፣ በሌላው ማህበረሰብ ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው የሚያደርጉ፣ አፈታሪኮችን ብቻ እንዲሰሙ፣ የአኖሌ፣ የጨለንቆ የመሳሰሉ የጥላቻ ሃዉልቶችም እንዲመለከቱ እየተደረገ፣ ከኦሮሞነት ዉጭ ሌላ ነገር እንዳይታያቸው፣ ለኢትዮጵያዊነት ግድ እንዳይሰጣቸው ወይንም ኢትዮጵያዊነትን እንዲጠሉት፣ ኦሮሞነትና ኢትዮጵያዊነት የተሳሰሩ ሳይሆን እሳትና ጭድ እንደሆኑ ተደረጎ እንዲያስቡ የተደረገበት ሁኔታ ነው የነበረው፤ አሁንም ያለው።

በዘር ላይ ያተኮረ የማንነት ፖለቲካ፣ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች የተለያዩ ችግሮችን አስከትሏል. አሁንም እያስከተለም ነው።

1. በወልቃይት ጠገዴና ኮረም አላማጣ በግድ “ትግሬ ናችሁ፣ ተብለናል” በሚል የማንነት ጥያቄ አንስተው ወደ ጎንደርና ወሎ ለመደባለቅ እየጠየቁ ነው። ሕወሃቶች ራሳቸው ያመጡት የማንነትና የዘር ፖለቲካ ራስ ምታት ሆኖባቸው የሕዝብን ጥያቄ ለማፈን ጥየት መተኮሱን አማራጭ አድርገዋል። በኮረም የትግራይ ልዩ ፖሊስ በሕዝቡ ላይ በመተኮስ በርካታ ወገኖች ያቆሰለበት ሁኔታ ነው ያለው። ያንንም ተከትሎ የወልቃይትና የአላማጣ/ኮረም ጥያቄ መመለስ አለበት በሚል በአማራ ክልል ወደ ትግራይ የሚሄዱ ተሽከርካሪዎችን የማስቆም እንቅስቃሴ በስፋት እየታየ ነው።

2. ከኦሮሞና ትግሬ ብሄረተኘነት የተነሳ ፣ በተወለደው የአማራ ብሄረተኝነትም ምክንያት በሰሜን ጎንደር ቅማንቶች “አማራ” አይደለንም እያሉ ነው። አገዎችም ጋር ተመሳሳይ እንቅስቃሴ እንዳለ ነው። ታይቶ የማይታወቅ ፣ ተፋቅሮና አንድ ሆኖ በኖረ ህዝብ መካከል የዘር ቆጠራ በጎንደርና በጎጃም እያየን ነው።

3. በጋምቤላ በአኙዋክና በኑር ብሄረሰቦች መካከል ትልቅ ችግር ተፈጥሮ ነበር። ችግሩ አሁንም አለ።

4. በኮንሶ ተመሳሳይ ችግሮች አሉ። የነበረንን ልዩ ወረዳ ማጣት አንፈለግም በሚል ሕዝቡ ተቃዉሞ አሰምቶ ብዙዎች ሞተዋል። ያለ ሕዝቡ ፍላጎት ሰገን በሚባል ዞን ውስጥ የኮንሶ ወረዳ ተጠቃሏል።

5. በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ዙሪያ ችግሩ እንዳለ ነው። የኦሮሞ ብሄረተኞች የሰፈር ስም እየጠሩ ፊንፊኒ የኛ ናት ይላሉ። ዘመቻቸውን አጧጡፈዉታል። ሆኖም የሸገር ልጅ ዘር ለእህል እንጂ ለሰው አይደለም ብሎ ለሚናፈሱ የዘር ጥያቄዎች ቦታ አልሰጠም።

6. እንደ አዳማ፣ ቢሾፉቱ ባሉ ከተሞች የሚኖረው ሕዝብ ለኦሮሞነት ሳይሆን ለኢትዮጵያ ብሄረተኝነት ነው ቦታ የሚሰጠው። በአብዛኛው አማርኛ ተናጋሪ ነው። በኦሮሞ ክልል ዉስጥ ከመቀጠል ከአዲስ አበባ ጋር መያያዝን የሚፈልግ ነዋሪ ነው። ሆኖም ኦህዴዶች ሕዝቡን አፍነው ይዘዉታል። ሻሸመኔ ከአዋሳ ጋር የበለጠ መቀራረብ ትፈልጋለች። የጂማ ሕዝብ እንደ ድሬዳዋ ቻርተር ከተማ መሆን ይፈልጋል።

7. ድረዳዋና ሞያሌ የኛ ነው በሚል በሶማሌና በኦሮሞዎች መካከል፣ ሃረር የኛ ነው በሚል በኦሮሞና በሃረሬ መካከል ግብግብ አለ። በምስራቅና በደቡብ ኢትዮጵያ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎች ከሶማሌ ክልል፣ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ ሶማሌዎች ከኦሮሞ ክልል፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ጌደዎዎች ከኦሮሞ ክልል በግፍና በጭካኔ ተፈናቅለዋል።

8. በአዋሳ በወልያታዎች ላይ ዘር ተኮር ጥቃት በአክራሪ ሲዳማዎች ተፈጽሞ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆ ዜጎች የተፈናቅለዋል። እዚያ አዋሳ ሲዳማዎች የራሳችንን ክልል ካልተሰጠን እያሉ ነው። የደቡብ ክልልን እነርሱ ካልገዙት አይመቻቸውም።

9. በአሶሳ በአማራዎችና ኦሮሞዎች ላይ ዘር ተኮር ጥቃት ተፈጸሞ ትልቅ ረብሻ ተፈጥሮ ነበር። ከአሶሳ ውጭ በመተከልና ሌሎች የቤነሻንጉል ቦታዎች አማራዎች ላይ ከፍተኛ የዘር ማጽዳት ወንጀል ተፈጽሟል።

10. በባሌ/ጎባ በአክራሪ ኦሮሞዎች አማራዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። አማራዎች ከኢሊባቡር፣ ከምእራብ ሸዋ፣ አወለጋ በአካራሪዎች ተፈናቅለዋል። በገጀራ የተገደሉም አሉ።

11. በወለጋ በጭካኔ ትግሪዎች ተገድለዋል። በአማራ ክልል በሰሜን ወሎና በሰሜን ጎንደር የትግራይ ተወላጆች ንብረት ላይ ዉድመት ደርሷል። ብዙ ትግሬዎችም ለደህንነታቸው በመፍራት ከጎንደር፣ መተማና ወልዲያ አካባቢ የተሰደዱበትና የተፈናቀሉበት ሁኔታም ነበር።

ወደ ኋላ መለስ ስንል በጉሩፈርዳ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ….በተለያዩ ቦታዎች ከዘራቸውና ከሚናገሩት ቋንቋ የተነሳ በብዙ ወገኖቻችን ግድያዎች፣ መፈናቅሎች ተፈጽመዋል። በበደኖ ነፍሰ ጡር ሴቶች ሳይቀሩ በሕይወት ገደል ውስጥ ተከተዋል። አሁን እንኳን በሻሸመኔ ኢትዮጵያዊያንን በሙሉ አንገት ያስደፋ ድርጊት ተፈጽሟል። ምንም ያላጠፋን ሰላማዊ ዜጋ ሰቃለው ሆ ይሉ ነበር።

ዘረኛ ስንሆን ወደ እንስሳነት ነው የምንቆጠረው። ማመዛዘን ይሳነናል። ጭካኔ እንሞላለን።የሰው ልጅ በስብእናው፣ በዜግነቱ መከበር እንዳለበት እንረሳለን። የኛ ዘር፣ የኛ ወገን፣ የኛ ጎሳ ካለሆነ በቀር ለሌላው ግድ አይሰጠንም። ዘረኘነት በሽታ ነው።
በአጠቃላይ የሕወሃት/ኦህዴድ በዘር ማንነት ላይ ያተኮረ ፖለቲካ “ ይሄ ብሄረሰብ፣ ያ ብሄረሰም፣ ይሄ ዘር፣ ያ ዘር፣ ይሄ የኛ መሬት ነው፣ ያ የነርሱ መሬት ነው …..” እያልን፣ በጋራ እንድንያያዝ ሳይሆን የራሳችንን ጎጥ ይዘን ቀስት እንድንወራወር የሚያደርግ፣ ወደ እንስሳነት እየለወጠን፣ እያሳነስ ያለ፣ አደገኛና በቶሎ መስተካከል የሚያስፈልገው ፖለቲካ ነው።

ቋንቋ የመግባቢያ መሳሪያ ነው። አራት ነጥብ።፡አፋን ኦሮሞ፣ ትግሪኛ፣ ጉራጌኛ፣ ሃምባሻ፣ ቆጮ፣ ቆጭቆጫ ….በተለያዩ የአገራችን ግዛቶች ያሉ የተለያዩ ባህሎች፣ ቋንቋዎች ፣ ምግቦች …ሁሉም «ኢትዮጵያዊነት» ናቸው። ሁሉም የኢትዮጵያ መገለጫዎች ናቸው። ኢትዮጵያ አንድ ወጥ አይደለችም። የተለያዩ ባህሎችን ፣ ቋንቋዎች፣ በአጭሩ የተለያዩ ብሄረሰቦች ያሉባት አገር ናት። ቢራቢሮዎችና አበባዎች የተለያዩ ቀለማቶቻቸው ዉበታቸው እንደሆኑ፣ የኢትዮጵያም ዉበቷ ብሄረሰቦቿ ናቸው። ለሚነሱ መሰረታዊ ጥያቄዎች ሁሉ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር መመለስ ይችላሉ።
ግርማ ካሳ ዘብሄረ ኢትዮጵያ ( የዶር ፍቅሬ ቶሎሳን አባባል ልዋስና)