በመተከል አሁንም ዘርን መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

(አብመድ) ከአሁን በፊት በመተከል ዞን የደረሰውን ጅምላ ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል አብመድ በተደጋጋሚ ሲዘግብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ ዛሬም ዘርን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ነዋሪዎች ለአብመድ ተናግረዋል፡፡
በተለይም ትላንት ጠዋት በድባጤ ወረዳ በዳሊቲ ቀበሌ በተፈጸመው ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በርካታ ንጹሓን ዜጎች ህይወታቸውን እንዳጡ ነው ነዋሪዎቹ ለአብመድ ያስረዱት፡፡ጭፍጨፋውን የፈጸሙት ደግሞ የታጠቁ ቡድኖች ናቸው ብለዋል ነዋሪዎቹ፡፡ የሟቾችን አስክሬን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት አፈር ለማልበስ መቸገራቸውንም ከጥቃቱ የተረፉ ዜጎች ተናግረዋል፡፡
አሁንም በድባጤ ወረዳ ጋሌሳ ቀበሌ ሌላ ጥፋት ለማድርስ የተዘጋጁ ቡድኖች በዙሪያው እንደሚገኙና እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡ በከባድ ጭንቅ ውስጥ ሆነው የድርሱልን ጥሪም አቅርበዋል፡፡በጉዳዩ ላይ በአካባቢው የተሰማራውን ግብረ ኀይል ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ምላሽ እንዳገኘን ይዘን የምንቀርብ ይሆናል፡፡