አናቱን ካይሮ ጭራውን ካርቱም ያደረገው የሱዳኑ ወታደራዊ ‘ቡድን’


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

አናቱን ካይሮ ጭራውን ካርቱም ያደረገው የሱዳኑ ወታደራዊ ‘ቡድን’

በሰላም ሙሉጌታ


ህዝብን በመጨቆን እና ጥያቄውን ባለመመለስ ሊመጣ የሚችለውን የመጨረሻውን አስከፊ ውጤት ያየች ሃገር ናት፤ ሱዳን። የደቡብ ሱዳን መገንጠል የዚህ ማሳያ ነው። የህዝቧን 1/5ኛ እንዲሁም የመሬቷን ፣ የከርሰ-ምድር እና የገፀ ምድር ግማሽ ሃብቷን በደቡብ ሱዳን መገንጠል አጥታለች።

አሳዛኙ ነገር ሱዳን ዛሬም በተመሳሳይ ሃዲድ ፣ ተመሳሳይ ጉዞ ላይ የመሆኗ ጉዳይ ነው።
ህዝቧ ዴሞክራሲን ፣ ልማትን፣ እኩልነትን “አምጡ” ፤ እያለ መጠየቁን አላቋረጠም።
ሆኖም አዛኝ አንጀት፣ አስተዋይ አእምሮ፣ ሃገር ወዳድ ልብ ፣ አዳማጭ ጆሮ ፣ መላሽ አመራር እና ስርአትን ግን ገና አላገኙም። የሃገሪቱን ሽግግር መንግስት ቁልፍ ስልጣን የጨበጡት ወታደራዊ መኮንኖች ባረጀ የፖለቲካ ቁማር ሱዳንን ወደ ሃገራዊ ሞት እያንደረደሯት ይገኛሉ። ቤታቸውን ማመሳቀላቸው ሳያንስ፥ በኢትዮጵያ ላይ ወረራን በመፈፀም ፥ ድንበር የለሽ ከሃዲ እና አጥፊነታቸውን በተግባር እያሳዩ ነው።

📍 የካይሮው ውል እና የአብዮት ቅልበሳው
ከሶስት ወራት ህዝባዊ ተቃውሞ በኋላ በሚያዚያ 2019 ኘሬዝደንት ኦማር አልበሽር ከስልጣን ተወገዱ።
ለውጡ ለሱዳናውያን የጨለማው ዘመን ፍፃሜ ፥የብርሃን ጉዞ ጅማሬ መስሎ ነበር።
ሆኖም በሰላሳ አመቱ የአልበሽር አስተዳደር ሱዳንን “ምድራዊ ሲኦል” እንድትሆን ያደረጎት የጦር አጋፋሪዎች መለዮአቸውን ሳያወልቁ የለውጥ መሪ እና ጠባቂ ሆነው ቀጠሉ።

አሁን ወታደራዊ መኮንኖቹ ከሲቪል ማህበረሰብ ወኪሎች ጋር በጥምረት የመሰረቱትን የሽግግር መንግስት ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል ።
ለሁሉም የምትሆን ዴሞክራሲያዊት ሱዳንን ለመፍጠር የሚደረገውን ትግል በመጥለፍ አቅጣጫውን አስተውታል ።
ሱዳን ህመም ላይ ናት፤ ህዝቦቿ ፈውስን ሲጠብቁ ህመሟ ግን እየፀና ሄዷል። አሳሳቢው ነገር የወቅቱ የሱዳን ደዌ ከራሷ አልፎ መልካም ጎረቤቶቿንም የሚያጠቃ መሆኑ ነው።
የሃይል የበላይነት የጨበጠው ወታደራዊው ቡድን ህዝቡ የሚናፍቃትን ሱዳን ያዋልዳል ብሎ ማሰብ ከእባብ እንቁላል እርግብን እንደመጠበቅ ነው። “ለምን?” ካላችሁ ሁለት መሰረታዊ ምክኒያቶችን መጥቀስ ይቻላል።የወታደራዊ ቡድኑ ስርአታዊ ባህሪ እና ወደ ስልጣንን የመጣበትን መንገድ ነው።

▪ስርአታዊ ባህሪው ፣
በሱዳን የሽግግር መንግስት ውስጥ ከፍተኛውን ስልጣን የጨበጠው ወታደራዊው
ሃይል ባለፋት 30 አመታት በተግባር ባህሪውን ለአለም ገልፅልፅ አድርጎ አሳይቷል። የዘር ጭፍጨፋ፣ ፆታዊ ጥቃት፣ ሰብአዊ መብት ጥሰት ፣ዘረፋ ወዘተ ዋንኛ የሰራዊቱ ባህሪያት ናቸው። በደቡብ ሱዳናውያን ፍጅት፣ በዳርፋራውያን ጭፍጨፋ፣ በደቡብ ኮርዶፋን እና በብሉ ናይል የእርስ በእርስ ጦርነት ሰራዊቱ የነበረው ሚና የስርአታዊ ባህሪው ጥቂት ማሳያዎች ናቸው።
የነበረችበት ፣በሰብአዊነት፣ በሃገር ፍቅር እና ጥቅም ታነፆ የተገነባ ሰራዊት አይደለም። ሱዳን ያለችበት እና የነበረችበት ፥እንዲሁም ህዝቧ ላይ እየደረሰ ያለው መከራ የሰራዊቱ ባህሪ ውጤት ነው።
የሰራዊቱ ተልዕኮ የጥቂት ቡድኖችን ፓለቲካዊ እና ኢኮኖሚ ጥቅሞችን ማስጠበቅ ነው። ለዚህም ሲባል ከሃገራዊ እና ህዝባዊ እሴቶች ጋር ፈፅሞ እንዳይተዋወቅ ተደርጓል።

እንግዲህ የሱዳናውያን ወደ ዴሞክራሲ የመሸጋገር ህልም ይህን ሰራዊት በሚመሩ “ጥቂት መኮንኖች” መዳፍ ውስጥ ነው የወደቀው ። ይህን ስርአታዊ ባህሪውን ሳይለቅ ሽግግሩን ከፊት እየመራ ይገኛል።

▪ወደ ስልጣን አመጣጡ ፣
በተግባር ሱዳንን እየመሩ ያሉት ጄነራል አብዱልፈታ አል ቡርሃን እና ሃምዳን ደጋሎ ናቸው። ሁለቱ የጦር መኮንኖች በአል በሽር ስንብት ዋዜማ ካይሮ በማምራት ከግብፅ ኘሬዝደንት እና የደህንነት ሚኒስትር ጋር ለሚስጥራዊ ውይይት ተቀመጡ። የሱዳንን ሽግግር መንግስት ሁለቱ እንዲመሩ ግብፅ እና ሳኡዲ አረቢያ ፍላጎት እንዳላቸው አል ሲሲገለፁላቸው። በአንፃሩ ይህ የሚሆነው ግን እነርሱ (አል ቡርሃን እና ደጋሎ) የግብፅን ሁሉንም አይነት ጥቅም የሚያስጠብቁ እንዲሁም የሽግግር አስተዳደሩ በግብፅ መንግስት ‘የበላይ ተቆጣጣሪነት’ በስውር እንዲመራ ከተስማሙ ብቻ እንደሆነ ተነገራቸው። ሰዎቹ አላመነቱም፤ ሲፈፅሙ በኖሩት የጦር ወንጀል ዘብጥያ እንወረወራለን ብለው ስጋት ውስጥ የነበሩት አል ቡርሃን እና ደጋሎ ግብዣውን በደስታ ተቀበሉ። ሱዳናውያንን ለመምራት ለግብፅ መንግስት ማህላ ፈፀሙ ፤ሉዐላዊነቷን ሸጠው ወደ ካርቱም ተመለሱ!!

በቀናት ውስጥ ለባንዳዊ ኪዳናቸው ማሰሪያ በሳኡዲ መንግስት በኩል በስመ-እርዳታ 3 ቢሊየን ዶላር ተለቀቀላቸው።

እነርሱም ሱዳንን በመጉዳት ላይ የተመሰረተውን የግብፅን ጥቅም ለማስጠበቅ በውስጥም-በውጭም የሚታዘዙትን ሁሉ ወደ መፈፀም ተሸጋገሩ።

የግብፅ መንግስታት ከጥንት ጀምሮ ሱዳን ላይ የሚከተሉት ፖሊሲ፥ ከሱዳናውያን ጥቅም እና ፍላጎት ጋር የሚፃረር እንጂ ፈፅሞ የሚስማማ አይደለም።
ግብፆች ከሱዳን ሰላም እና እድገት፣ ከሱዳን መጠንከር እናተርፋለን ብለው አያምኑም ። አሁንም በገሃድ የሚታየው ነባሩ ይህ ስርአታዊ ( systemic) አመለካከት ነው።
የሱዳን ህዝብ እና የግብፅ መንግስት ፍላጎት ፈፅሞ ሊገጥም የማይችል፥ በተቃርኖ የተወጠረ ነው።
ሱዳናውያን ልማትን፥ግብፅ ድህነትን፣ ሱዳናውያን ሰላምን ፥ ግብፅ ግጭትን፣ ሱዳናውያን አንድነትን፥ ግብፅ ክፍፍልን ፣ ሱዳናውያን ነፃነትን ፥ግብፅ የእጅ አዙር አስተዳደርን ፣ ሱዳናውያን ዴሞክራሲን፥ ግብፅ አምባገነን ስርአትን ለመትከል በሚያደርጉት ትግል ሃገሪቱን ወጥረዋታል።
የሱዳን ህዝብ ጥያቄዎች ከተመለሱ ፥ግብፅ ስግብግብ ጥቅሞቿን ታጣለች። ስለዚህ ሱዳን ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት የሌላት ሃገር ሆና የግድ መቀጠል አለባት። ይህ ሲሆን ግብፅ በትንሹ ሁለት መሰረታዊ ፍላጎቶቿን ታሳካለች፤

👉 አንድ፥ ሱዳን ጠንካራ ማዕከላዊ አስተዳደር ከሌላት ልማትን ፈፅሞ አታስብም። ግጭት የሚነግስባት ሃገር ስለምትሆን የአባይን ውሃ ማልማት አትችልም ። ስለዚህ እስካሁን ከተጠቀመችው ውጭ ያለው ውሃ የግብፅ ይሆናል፤ ግብፅ በነፃነት ትጠቀመዋለች። በሱዳን የደካማ መንግስት መኖር ከዚህ በተጨማሪ የታጣቁ ሃይሎች እንዲፈጠሩ እና እንዲፈረጥሙ ያስችላል። ይህም ግብፅ በቀጥታ እና በወኪል ሃይሎቿ በኩል ሱዳንን እስከወዲያኛው የምታመሳቅልበትን አስቻይ ሁኔታ ይፈጥርላታል። ሱዳንን ከአንድ ትልቅ ሃገርነት ወደ ብዙ ትንንሽ እና ደካማ ሃገርነት የመቀየሪያውን መንገድም ይጠርግላታል።

👉 ሁለት፥ የሱዳን ደካማነት እና መንግስት አልባ መሆን ግብፅ “ቁጥር አንድ ጠላቴ የምትላትን” ኢትዮጵያን ለማተራመስ ትልቅ አቅም እና ዕድል ያስገኝላታል። የታጠቁ የውስጥ እና የውጭ ሃይሎችን በማሰማራት ኢትዮጵያን ፋታ የለሽ ግጭት ውሰጥ የመክተት የዘመናት ፍላጎቷን ማሳኪያ ዕድል አድርጋም ትቆጥረዋለች።
እንደ ግብፅ ስሌት ፥ ኢትዮጵያ በቀውስ ከተዘፈቀች የጀመረችውን የህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ ይሳናታል፤ አልፎም ተርፎ አጠቃላይ ስለ አባይ ማሰብ እድታቆም ያስገድዳታል።
የሱዳን ወታደራዊ ቡድን ወደ ስልጣን የመጣበት እና የሃይል የበላይነትን እንዲቆናጠጥ እየተደረገ ያለውም በዋናነት ለዚሁ አላማ ነው።
ቡድኑ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገዋ ግብፅ የሚሆን ስርአተ መንግስትን በሉአላዊት ሱዳን ላይ የመትከል ተልዕኮን ነው ያነገበው።

📍የአል ሲሲን ታሪክ በካርቱም ለመድገም?

የወታደራዊው ቡድን የስልጣን ምንጭ የሱዳን ህዝብ ሳይሆ

ን የግብፅ መንግስት ነው ፤ እናም በፈርኦኖቹ ጋላቢነት የሱዳናውያንን ህልም እያጨናገፈ ይገኛል።
የግብፁ አል ሲሲ በካይሮ የሰሩትን እኩይ ታሪክ አል ቡርሃን በካርቱም ለመድገም ሩጫ ላይ ናቸው።
እንዲህ ነበር የሆነው፤
ከፀደይ አብዮት በኋላ እአአ በ2013 በግብፅ የተካሄደውን ምርጫ የሙስሊም ወንድማማች ፓርቲ አሸነፈ። የፓርቲው መሪ የነበሩት መሀመድ ሙርሲም የግብፅ ኘሬዝደንት ሆኑ። ከአንድ አመት በላይ ሳይጓዙ ግን በወቅቱ የሃገሪቱ ጦር አዛዥ በነበሩት አብዱልፈታ አል ሲሲ ስልታዊ መፈንቅለ መንግስት ተፈፅሞባቸው ከስልጣን ተባረሩ። የግብፅም አብዮት ተቀለበሰ ፤ ሙርሲም ዘብጥያ ተወረወሩ፤ ህይወታቸውም በዚያው አለፈ።
ካርቱም ላይ የካይሮውን ታሪክ ለመድገም ሽር-ጉዱ ቀጥሏል። አላማው በተመሳሳይ ስልት ‘በካይሮ አምሳያ’ የተቀረፀ መንግስትን ሱዳን ላይ ማዋለድ ነው። የግብፅን ህልም የወረሰ ፣ መንፈሷን የተላበሰ ተልዕኮዋን ፈፃሚ -መንግስትን መፍጠር !!
እንዲህ ያለው መንግስት ለሱዳናውያን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እና ለቀጠናው ጭምር አደጋ ነው።
የሱዳን ወታደራዊ ቡድን የስልጣን ዋስትናው የሚመነጨው ከቀጣሪው ግብፅ በመሆኑ ሉዐላዊውን የሱዳንን ህዝብ ባይተዋር አድርጎታል።
የተግባሩ መለኪያ የግብፅ መንግስት ፍላጎት ብቻ ነው !! የሱዳንን ህዝብ ጊዜያዊ እና ዘላቂ ጥቅም ስሌት ውስጥ አይከትም። የገዛ ህዝቡን የከዳው ወታደራዊ ቡድን፥ ወዳጅ ኢትዮጵያንም በገሃድ ክዶ እያየነው እንገኛለን። የመሬት ወረራ የፈፀመበት አግባብም ይኸው ነው።

📍የክህደቱ ጉዞ……
የሱዳን ወታደራዊ ቡድን በኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል ዘመናትን ለተሻገሩ የአብሮነት እሴቶች ደንታ የማይሰጥ ስብስብ ነው።
ቡድኑ በሃገራችን ላይ የመሬት ወረራን የፈፀመው የኢትዮጵያ መንግስት በውስጥ ወታደራዊ ዘመቻ በተወጠረበት ወቅት መሆኑ ክህደቱን ከፍ ያደርገዋል። የኢትዮጵያን ውስጣዊ አለመረጋጋት እንደ እድል የመቁጠራቸው እሳቤ ምን ያህል ትላንትን የረሱ፣ ነገን የማያስቡ ቅርብ አላሚ መሆናቸውን የሚያረግጥ ነው!!
ኢትዮጵያ ፥ ሱዳን ፈተና እና ችግር በገጠማት ጊዜ ከማንም ቀድማ የምትደርስላት ፣መልካም ጎረቤት እደሆነች በተደጋጋሚ ያሳየች ሃገር ናት።

ምስቅልቅል እና ግጭት ባልተለየው ያለፋት ሃምሳ አመታት የሱዳን ታሪክ ውስጥ ሸምጋይ እና ገላጋይ የሆንን ባለውለታ ህዝቦች ነን።
እኤአ በ1972 በሱዳን መንግስት እና በያኔው የደቡብ ሱዳን አማፂ ሃይል መካከል በኢትዮጵያ አሸማጋይነት ለውጤት የበቃው የአዲስ አበባ ስምምነት( addis ababa acord ) ይጠቀሳል።
ከአመት በፊትም የሱዳንን ሽግግር በሚመሩት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ልዩነት በውይይት እንዲፈታ ያደረገችው ኢትዮጵያ ናት።

ሱዳን ወደ እርስ በርስ ግጭት ባመራችባቸው ክፋ ጊዜያትም ቢሆን ለሰላሟ ቀድሞ የደረሰ ከኢትዮጵያ ሌላ አንድም ሃገር የለም።
ዳርፋርን ከእልቂት ለመታደግ ከ4000 በላይ የሰራዊት አባሎቻችንን ለ13 አመታት ያህል ያሰማራን፣ በአባዪ ግዛት ሰላምን ለማስጠበቅ ከ3500 በላይ ሰራዊታችን ዛሬም ከእነርሱ ጋር እንዲሆን የፈቀድን ህዝቦች ነን።
በክፉም ሆነ በመልካም ጊዜ ኢትዮጵያ ለሱዳን ታማኝ ወዳጅ መሆኗን አስረጂ ከዚህ በላይ ብዙ ታሪኮችን መጥቀስ ይቻላል ።

ኢትዮጵያ ሱዳንን የምታይበት መነፅር ፈፅሞ ግብፅ ሱዳንን ከምትመለከትበት የተለየ ነው። ኢትዮጵያ አተርፋለው ብላ የምታምነው ሰላማዊ፣ የለማች፣ በጋራ ተጠቃሚነት የምታምን እና ጠንካራ የሆነች ሱዳን ስትኖር ነው። እንዲህ ያለችው ሱዳን ናት ለህዝቧም፣ ለቀጠናችንም ሆነ ለአለም ጠቃሚ የምትሆነው ።
የሱዳን ሰላማዊ መሆን ከ1600 ኪ.ሜ በላይ ድንበር ለምትጋራት ሃገራችን ውጣዊ ደህንነት ወሳኝ ነው። የሱዳን መልማት የኢትዮጵያን ልማት ይደግፋል፤ የጥቅም ትስስርም ይፈጥራል። በልማት የተሳሰሩ ህዝቦች ለትብብር ይተጋሉ እንጂ ለግጭት አይሽቀዳደሙም ።
የሱዳን ህዝብ መበልፀግ ለኢትዮጵያ ንግድ እና ምጣኔ ሃብት እድገት እድልን ያመጣል። ፍላጎትን በማጣጣም እና በመከባበር ሃገራት በዘመነ ሉላዊነት (globalization ) አያሌ ጋሬጣዎችን ሲሻገሩ እያየን ነው።

አለመታደል ሆኖ የሱዳን ወታደራዊ ቡድን ይህን እውነታ መረዳት ቀርቶ የሃገሬውን ህዝብ ፍላጎቱንም በቅጡ የተገነዘበ አይደለም፤ ፈቃደኝነቱም የለውም።ይህም በመሆኑ የሁለቱን ህዝቦች የአብሮነት ሃዉልት እየናደ ይገኛል።

🎈በጦር ላይፈታ ምን ሊፈይድ ውጊያ ??

በካይሮ የሚሾፈረው ይህ ቡድን ዘመን ተሻጋሪውን የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝብ ግንኙነት ለመበጠስ ፤ ብሎም የደም ታሪክ ለመፃፍ ጦር አውርድ ብሏል።
ከሃዲው የሱዳን ወታደራዊ ቡድን መሬታችንን ሲወር፣ ዜጎቻችንን ሲያፈናቅል፣ ንብረት ሲዘርፍ እና ሲያወድም የኢትዮጵያ መንግስት አፀፋውን በልኩ የመመለስ አቅም ቢኖረው በትዕግስት አልፎታል።
የኢትዮጵያን መሬት በመዉረር የሚመለስ አንዳችም የሱዳን ህዝብ ጥያቄ የለም። ይልቅ ዛሬን የሚሻገር ሌላ ችግር ይወልዳል እንጂ።
ከምንም በፊት የሱዳን ሰራዊት በእብሪት ከወረረው የኢትዮጵያ መሬት ለቆ ሊወጣ ይገባል !!

የሁለቱ ሃገራት የድንበር ጉዳይ በውይይት እና በህግ እንጂ በጦርነት መፍትሄ መቼም ሊያገኝ እንደማይችል መታመን አለበት።
የሰላም ጀምበር ፈፅሞ ባይጠልቅም ፤ ከቀን ወደ ቀን ግን እየደበዘዘ መሆኑ እየታየ ነው።
የሆነው ሁሉ ሆኖ ጦርነት ሳይሆን፤
እውነት፣ጊዜ እና ትዕግስት ፍትህን አሸናፊ ያደርጋታል፤ ድልን ያጎናፅፈናል!!