ህገ ወጡ የህወሓት ቡድን እየፈጸመው ያለውን ግፍ ለመላው ዓለም ለማሳወቅ ሰላማዊ ሰልፍ ነገ ይደረጋል


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ

  • በኦሮሚያ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልሎች በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መታቀዱን የክልሎቹና የከተማ አስተዳደሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
  • በርካቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ ይህ ሰልፍ ወቅቱን ያልጠበቀ እንደሆነ እየገለጹ ይገኛሉ። ድርጊቱ በርካቶችን ለአደጋ ያጋለጠ ነውም ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

በነገው ዕለት ሊካሄድ የታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ

በኦሮሚያ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልሎች በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ መታቀዱን የክልሎቹና የከተማ አስተዳደሩ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በርካቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ላይ ይህ ሰልፍ ወቅቱን ያልጠበቀ እንደሆነ እየገለጹ ይገኛሉ። ድርጊቱ በርካቶችን ለአደጋ ያጋለጠ ነውም ሲሉ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው።

በአማራ ክልል ሰልፉ በባህር ዳር፣ ፍኖተ ሰላም፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ደብረ ታቦር ከተሞች ብቻ የሚካሄድ መሆኑን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ወ/ሮ አንቺነሽ ተስፋዬም በሰጡት መግለጫም ሰልፉ በከተማዋ በነገው እለት እንደሚደረግና የድጋፍ ማሰባሰብና የደም ልገሳ መርኃግብሮች እንደሚኖሩት ገልጸዋል።

በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልልም ከነገ ከሀሙስ ህዳር 3/2013 ጀምሮ ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች እንዲደረጉ መፈቀዱንና የጸጥታ አካላትም የህዝቡን የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡ በጅማ ከተማ ሰልፉ ቀደም ብሎ ዛሬ ተካሂዷል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በትላንትናው ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ሕዝቡ በንቃትና በተደራጀ መንገድ አካባቢውን እንዲጠብቅ አደራ ማለታቸው ይታወሳል።

EBC : የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ሰልፉን አስመልክቶ መግለጫ “መላው የክልላችን ህዝብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ህገ ወጡ የትህነግ ቡድን ያደረሰውን ግፍ እና የሀገር ክህደት ወንጀል ለመላው ዓለም በምንችለው ሁሉ ለማሳወቅ የሰልፉ ተሳታፊ አንድንሆን ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል፡፡
የሰልፉ ዓለማ ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን እየፈጸመው ያለውን ግፍና በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረሰውን ክህደት ለመላው ዓለም ለማሳወቅ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሰልፉ ባህር ዳር፣ ፍኖተ ሰላም፣ እንጅባራ፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደብረ ብርሃን፣ ኮምቦልቻ፣ ደሴ፣ ደብረ ታቦር ከተሞች ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከእነዚህ ከተሞች ውጭ ባሉ የክልሉ ከተሞች ሰልፉ የማይካሄደው ህገ ወጡን ቡድን በህግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል በሚደረገው ውጊያ ልዩ የጸጥታ ጥበቃ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡
ሠላማዊ ሰልፉ ነገ ህዳር 3፣2013 ጠዋት 2፡30 ተጀምሮ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ሲሆን በተዋቀረው የሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ እና የጸጥታ ኃይል ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግለት እንደሆነ ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
———————–
ጽንፈኛው የሕወሃት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በኦሮሚያ ከነገ ህዳር 3 ቀን 2013 ጀምሮ ሊደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሕወሃት ጁንታ በሰሜን ዕዝ ጀግኖች የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ለመስማት እንኳን የሚከብድ ዘግናኝ የሆነ ሰይጣናዊ ጭፍጨፋ መፈጸሙ የኦሮሚያ ክልል ህዝብን እንዳስቆጣ ተገልጿል፡፡
ይህ አሳፋሪ ተግባር በዓለም ታሪክ ከተፈጸሙ እጅግ አሳፋሪ የጦር ወንጀል ታሪኮች ውስጥ ተመዝግቦ ይኖራልም ተብሏል፡፡
በመላው የኦሮሚያ ዞኖች፣ ከተሞች እና ወረዳዎችም ሰላማዊ ሰልፎች ለማድረግ በርካታ ጥያቄዎች በመቅረብ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡ ሰላማዊ ሰልፎቹ ከነገ ህዳር 3 ቀን 2013 ጀምሮ እንዲደረጉ መፈቀዱም ተገልጿል፡፡
የሰላማዊ ሰልፎቹ ዓላማ ህገ ወጡ የሕወሃት ጁንታ ከግብረ አበሩ ኦነግ ሸኔ ጋር በመቀናጀት በጀግናው የሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላት ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ እና የጦር ወንጀል በማውገዝ ጥፋተኞች ለህግ እንዲቀርቡ መጠየቅ፣ መንግስት ሕግን ለማስከበር እየወሰደ ያለውን ዕርምጃ በመደገፍ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ያላቸውን ዝግጁነት ለመግለጽ እንዲሁም የአጥፊው ጁንታ ጥፋት የጥቂት ስግብጎቦች ሴራ እንጂ የሰላም ወዳዱን የየትኛውንም ህዝብ ፍላጎት የማይወክል መሆኑንና በጁንታው በተፈጸመው ዘግናኝ ጥፋት ምክንያት የኢትዮጵያ አንድነት የማይፈርስ የህዝቦች ወንድማማችነት እንደማይናጋና የጁንታውን ሀገር የማፍረስ ሴራ በቁርጠኝነት ለመታገል ያላቸውን አቋም ለመግለጽ ነው ተብሏል፡፡
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የጸጥታ አካላትም የህዝቡን የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡
ሰላማዊ ሰልፈኞቹም ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ሰልፎቹ በሰላም እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ ራሳቸውንም ከኮቪድ-19 ስርጭት ለመከላከል አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ቀርቧል፡፡ EBC