በየዓመቱ እየተጫነ ጓዳና ጎተራቸውን ሲያጨናንቅ የነበረው ግዙፉ ማሳቸው ራቁቱን ቀርቷል !


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


ባለቤቴ የወደመውን ሰብል ስትመለከት ራሷን ሳተችብኝ፣ ልጆቼን ምን ላበላቸው ነው ብላ ተጨነቀችብኝ፣ ቤታችን በሰፊው የተለመደበት ስለነበር አሁን ባዶ ማሳ ስታይ ነገ ምን ልንሆን ነው ብላ ራሷን ሳተችብኝ፣ ስለዚህ አንበጣ መከላከሉን ትቼ እርሷን ሳጽናና ዋልኩ። እርሷን በሕይወት ማትረፌ ራሱ ትልቅ ደሰታ ተሰምቶኛል

BBC Amharic : አቶ ሐሰን አህመድ ማሳቸውን የወረረውን የአንበጣ መንጋ ማባረሩን ትተው ባለቤታቸውን ሲያጽናኑ ዋሉ። “ከሁሉም በላይ ባለቤቴን ማትረፌ ትልቅ ነገር ነው” ይላሉ።

ከማሳ ላይ አንበጣ የሚያባርሩ ወጣቶችአቶ ሐሰን አህመድ፣ በራያ ቆቦ ወረዳ ዲቢ ቀበሌ አንቱ የተባሉ አርሶ አደር ናቸው። ማሽላ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና ሽምብራ የመሳሰሉትን አዝዕርት በማምረት ኑሯቸውን ይመራሉ። ዘንድሮ ከወትሮው በተለየ መልኩ የክረምቱ ዝናብ የሰጠ ስለነበር የአቶ ሐሰንን አዝመራ ሙሉና ለአይን ግቡ አድርጎላቸዋል።

15 ጥማድ [4 ሄክታር የሚጠጋ] መሬታቸውን ማሽላ ዘርተው ውጤቱን ከአንድ ወር በኋላ ለማግኘት እየተጠባበቁ ነበር። ከዚህ ማሳ፣ ልክ እንደ ዘንድሮው ሁሉ የክረምቱ ዝናብ በማይጓደልበት ወቅት ከ80 እስከ 100 ኩንታል ማሽላ ያመርቱ እንደነበርም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዘንድሮ ደግሞ ሰብሉ በጥሩ ሁኔታ እያደገ ስለነበር ከወትሮው ከፍ ያለ ካልሆነ ደግሞ ተመሳሳይ ምርት እንደሚያገኙ እርግጠኛ ነበሩ።

ከአሁን በፊት አንዱ ልጃቸው ለቤቱ ተጨማሪ ገቢ አስገኛለሁ ብሎ ወደ አረብ አገር ሥራ ፍለጋ ሂዶ ነበር። ቤቱንም በገቢ አልደጎመም እርሱም አልተመለሰም። እዚያው ሞቶባቸው “ወይኔ ልጄን ባልላከኩት ኖሮ” እያሉ ለዓመታት የልጃቸው ጸጸት አልወጣላቸውም።

ጸጸቱን ለመወጣት ያቀዱት በቂ ምርት አምርተው ቀሪ ልጆቻቸው የወንድማቸው እጣ እንዳይገጥማቸው ፍላጎታቸውን ለማሟላት እና ለማስተማር ነው። ይህንን ለማሳካት ደግሞ የዘንድሮ የሰብል አያያዝ ትልቅ ተስፋ ሰጥቷቸው ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ አቶ ሐሰን ከሚያገኙት ምርት ግማሹን ሽጠው ደካማ የሳር ጎጇቸውን በተንጣለለ የቆርቆሮ ክዳን ቤት ለመቀየር እቅድ አስቀምጠዋል። ሁሉም እውን ሊሆን ቢበዛ የሁለት፣ ካነሰ ደግሞ የአንድ ወር ጊዜ ብቻ ቀርቷቸው ነበር።

ይህ ሁሉ እቅድ ግን ተስፋ ሆኖ የቆየው እስከ መስከረም 6 2013 ዓ.ም ነው።

በዚህ ዕለት ያልተጠበቀ ክስተት መጣ። የአንበጣ መንጋ።

የጣልኩብሽ ተስፋ እኔን ይዞ ጠፋ. . .

ብዙ ተስፋ የጣሉበት የአቶ ሐሰን 15 ጥማድ የማሽላ ማሳ በአንበጣ ተወረረ። የሚችሉትን ያክል ቀን ከሌሊት አንበጣን ታገሉት፣ ነገር ግን ድካሙ ፍሬ አልባ ሆነ፤ አንበጣው አሸነፋቸው። ያ ለስንት ያቀዱለት ሰብላቸው አሁን ያለበትን ሁኔታ “የታሰበው 100 ኩንታል ይቅርና ለዘር የሚሆን አንድ ጣሳም [አንድ ኪሎ] አይገኝበት” በማለት ይገልጹታል። አሁን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ መሆኑን ይናገራሉ።

አቶ ሐሰን ሌላ የስምንት ጥማድ [4 ሄክታር] እርሻቸው ደግሞ በበቆሎ ሰብል የተሸፈነ ነው። 15 ጥማድ ማሳቸውን ያወደመው የአንበጣ መንጋ፣ በዚህ ይበቃዎት አላላቸውም።

ሁለተኛ ምዕራፍ የጥቃት ዘመቻውን የበቆሎ ማሳቸው ላይ አሳረፈ ነው።

ሰሞኑን በአውሮፕላን በሚደረግ የኬሚካል ርጭትም በመታገዝ መከላከል ሲደረግ ቆይቷል፣ ጉዳቱ ግን አልቀነሰም። አቶ ሐሰንም ከመስከረም ስድስት ጀምረው ሌላ ሥራ በማቆም፣ መደበኛ ሥራቸው ከልጆቻቸው ጋር የአንበጣ መንጋ ማባረር ቢሆንም የማሽላ ሰብላቸው ሙሉ በሙሉ በመውደሞ በቆሎአቸውን ለመታደግ እየተውተረተሩ ነው።

ከሰሞኑ ግን ከልጆቻቸው በተጨማሪ ባለቤታቸውም ማሳቸውን ከአንበጣ ለመካለከል ወደ ማገዝ ጀምረዋል።

የአቶ ሐሰን ባለቤት ያዩትን ማመን አልቻሉም። ያ በየዓመቱ እየተጫነ ጓዳና ጎተራቸውን ሲያጨናንቅ የነበረው ግዙፉ ማሳቸው ራቁቱን ቀርቷል።

“ባለቤቴ የወደመውን ሰብል ስትመለከት ራሷን ሳተችብኝ፣ ልጆቼን ምን ላበላቸው ነው ብላ ተጨነቀችብኝ፣ ቤታችን በሰፊው የተለመደበት ስለነበር አሁን ባዶ ማሳ ስታይ ነገ ምን ልንሆን ነው ብላ ራሷን ሳተችብኝ፣ ስለዚህ አንበጣ መከላከሉን ትቼ እርሷን ሳጽናና ዋልኩ። እርሷን በሕይወት ማትረፌ ራሱ ትልቅ ደሰታ ተሰምቶኛል” በማለት ባለቤታቸው የወደመውን ሰብል ሲመለከቱ የተሰማቸውን ስሜት ያብራራሉ።

አሁን ከሁለተኛው ማሳቸው የተወሰነ ነገር ለማትረፍ የሞት ሽረት ትግል እያደረጉ ቢሆንም እንዲሁ ዝም ብሎ ላለማስበላት እንጂ ተስፋቸው ተሟጥጧል። ቀጣይ ዝናብ ጥሎ በበልግ ለማምረት፣ ካልሆነ ደግሞ መንግሥት የሚሰጠው ነገር ካለ እርሱን የሕይወት ማቆያ ለማድረግ ተስፋ ሰንቀዋል።

ሌላኛው አርሶ አደር ይማም መሃመድ በዚሁ የራያ ቆቦ ወረዳ ያያ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። አንበጣው ቀድሞ ሲገባ የመጀመሪያ ጥፋቱን የጀመረው ከእርሳቸው ማሳ ነው። “ሁሉንም እርሻዎቼን አንበጣው ሙሉ በሙሉ አውድሟቸዋል። አሁን አንበጣ የምከላከለው የሌሎች አርሶ አደሮችን ማሳ ለማትረፍ ነው” ይላሉ። እርሳቸው የሚኖሩበትን ያያ ቀበሌ ጨምሮ በወረዳው የሚገኙ ሁለት ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ የዘንድሮ ሰብላቸው በአንበጣ መንጋ ወድሟል።

በአጠቃላይ በራያ ቆቦ ወረዳ 16 ቀበሌዎች በአንበጣ መንጋው ተወርረዋል። በሰውና በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እንዲሁም የመከላከል ሥራ ቢሰራም ለአንድ ወር ያክል አንበጣውን ከአካባቢው ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አልተቻለም።

በአማራ ክልል ከሰሜን ሸዋ እስከ ሰሜን ወሎ ድረስ የአንበጣ መንጋው ከፍተኛ ጉዳት ካስተናገደባቸው ወረዳዎች አንዱ የሃብሩ ወረዳ ነው። በወረዳው ሰባት ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ በአንበጣ መንጋው ወድመዋል።

አርሶ አደር አሊ ሰዒድ ከእነዚህ ቀበሌዎች አንዷ በሆነችው ጥልፌ ቀበሌ ይኖራሉ። ከአራት እርሻዎቻቸው መካከል የ13 ጥማድ [3 ሄክታር በላይ] መሬት ወድሞባቸዋል። አንድ እርሻ ማትረፋቸውን የሚናገሩት አቶ አሊ፣ “የተረፈው እርሻ የአንድ ወር ቀለብ እንኳን የሚሆን አይደለም፣ ዓመት ሙሉ የደከምንበት እንኳን ለእኛ ለከብቶቻችንም የሚሆን እንዳይተርፍ አድርጎ አውድሞብናል” በማለት አንበጣው ያደረሰባቸውን ጉዳት ይገልጻሉ።

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግሥቴ የአንበጣ መንጋው በክልሉ 4 ዞኖች፣ 18 ወረዳዎች በ136 ቀበሌዎች መከሰቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል። በእነዚህ አካባቢዎች በአጠቃላይ 328 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ መውረሩን የተናገሩት አቶ ተስፋሁን ግማሽ የሚሆነውን መሬት የአውሮፕላን ርጭትን ጨምሮ በተለያዩ የመከላከያ ዘዴዎች የመከላከል ሥራ ተሠርቶበታል ሲሉ ይናገራሉ።

የአንበጣ መንጋው 87 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ በሰብልና በእንስሳት መኖ ላይ ጉዳት አድርሷል የሚሉት አቶ ተስፋሁን፣ ከእነዚህም መካከል 30 ሺህ 500 ሄክታር የሚሆነው የሰብል ምርት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋው ባደረሰው ከፍተኛ ውድመት የተጎዱ አርሶ አደሮችን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ድጋፍ ለማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑንም ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተናግረዋል።