ከንፁሃኑ ግድያ በስተጀርባም የህወሀት እጅ እንዳለበት ደርሰንበታል – የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በመተከል ዞን ንፁሃን እንዲገደሉ በማስተባበርና በመምራት የተጠረጠሩ 504 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል

 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመተከል ዞን ንፁሃን እንዲገደሉ በማስተባበርና በመምራት የተጠረጠሩ 504 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ፡፡

የአማራና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም በተደጋጋሚ በክልሉ መተከል ዞን በንፁሃን ላይ የሚፈፀመው ጥቃት መንስኤው ብዙ መሆኑን ጠቅሰው፥ የመሬት ይዞታ እና ለውጡን ተከትለው ያኮረፉ አካላት የሚፈጥሩት የፀረ ሰላም ኃይሎች እንቅስቃሴ ዋናዎቹ ናቸው ብለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ከንፁሃኑ ግድያ በስተጀርባም የህወሀት እጅ እንዳለበት ደርሰንበታል ብለዋል፡፡

ይህን ድርጊት ለማስፈፀም ወጣቶችን በመመልመልና አንዳንድ በኢንቨስትመንት የገቡ ባለሀብቶችን በመጠቀም ችግሮቹ እንዲባባስ ህወሃት ስራ ስትሰራ ከርማለችም ነው ያሉት፡፡

የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና ጥፋተኞችን ተጠያቂ ለማድረግ በክልሉ ተዋቅሮ ያለውን የኮማንድ ፖስት አፈፃፀም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር በመሆን መገምገማቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የመከላከያ ኃይሉ በአካባቢው የመሸጉ ታጣቂ ቡድኖችንና ሽፍታዎችን የመደምሰስ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡

የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ ከአማራ ክልል የፀጥታ መዋቅር ጋር የጣምራ ስራዎችን እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ነዋሪነታቸው በቤኒሻንጉል ክልል በመሆኑ የክልሉ መንግስት ደህንነታቸውን ማስጠበቅ እንዳለበት አንስተዋል፡፡

ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ የፖለቲካም፣ የሕግም እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በሚሊሻ በማደራጀት ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እንደሚደረግ በመጥቀስም በክልሉ ለሚፈጸም ጥቃት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ተጠያቂ መደረጋቸውን አውስተዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከአማራ ክልል ጋር በመሆን ጠንካራ ሥራ እንዲሠራ እና ያጋጠሙትን ችግሮች ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ አቅጣጫ መሰጠቱም በመግለጫው ላይ ተነስቷል።