" /> ከጠ/ሚ አብይ ጋር በአሜሪካ የሚደረጉ ውይይቶች ይዘታቸው ሁለገብ ሊሆን ይገባል | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ከጠ/ሚ አብይ ጋር በአሜሪካ የሚደረጉ ውይይቶች ይዘታቸው ሁለገብ ሊሆን ይገባል

የሚቀጥለው ሳምንት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ለመወያየት ዋሽንግተን ዲሲ ይገባሉ። በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሎስ አንጀለስና በሚኒያፖሊስ ከተማዎች የተለያዩ ስብሰባዎች ተዘጋጅተዋል። አንዳንዶቹ ስብሰባዎች ብዙ ሺህ ህዝብ የሚሳተፍባቸው ሲሆኑ፣ የተቀሩት ደግሞ የተለያዩ ድርጅቶችንና ማህበሮችን የሚወክሉ ጥቂት የተጋበዙ ግለሰቦች የሚካፈሉበት የውይይት ፕሮግራሞች ናቸው።

አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በእነዚህ ሶስት ከተሞች የሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ የሚገኘው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍና በርቱ ለማለት ነው። የውይይት መድረኮቹ ግን ትንሽ ለየት ያለ ይዘት ይኖራቸዋል። ማለትም የተለያዩ የህብረተሰቡን ክፍል የሚወክሉ፣ በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት በተቃውሞ ጎራ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የቆዩ አክቲቪስቶች ተገኝተው ጥያቄዎች የሚጠይቁበትና አስተያየቶች የሚያቀርቡበት ፕሮግራሞች ይኖራሉ።

ከፕሮግራሞቹ ውስጥ አንዳንዶቹ ግን ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ወደአሜሪካ ከሚመጡበት ዓላማ ጋር የሚጋጩ ናቸው። በተለይ ቪዥን ኢትዮጵያ የሚባለው ቡድን ባልታወቀ ሁኔታ የጠለፈውና ወደ 100 የሚጠጉ ግለሰቦች የሚሳተፉበት በዋሽንግተን ዲሲ የሚደረገው የውይይት መድረክ የተለያዩ ድርጅቶችን አመለካከቶች የሚያንጸባርቅ ሳይሆን የአንድን ድርጅት፣ ማለትም የግንቦት ሰባትን አጀንዳ ለማራመድ የተሰናዳ ሆኖ ተገኝቷል። ግንቦት ሰባት በዳያስፖራ ካሉ ኢትዮጵያውያን መካከል 1 ፐርሰንቱን እንኳን አይወክልም። ከዛም በተጨማሪ ከውጭ መንግስት (ኤርትራ) ጋር ባለው ጥብቅ ትስስር ምክንያት ኢትዮጵያውያን በጥርጣሬ የሚያዩት ድርጅት ነው። ለዚህ ድርጅት ከሚገባው በላይ እውቅና ሰጥቶ ሌሎችን ማግለል ተገቢ አይደለምና ሊስተካከል ይገባል። የውይይት መድረኮቹ ሁሉገብ ይዘት ይኖራቸው።


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV