የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ታወቀ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በምትካቸው የቀድሞው ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ይሾማሉ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሲሠሩ የቆዩት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ፣ ከቅዳሜ መስከረም 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን የሪፖርተር ምንጮች አረጋገጡ፡፡

ከባንኩ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ አቶ ኃይለየሱስ ኃላፊነት ያለባቸው ውሳኔዎችን ከማስተላለፍ የታገዱ ሲሆን፣ ምንም ዓይነት አዲስ ብድር እንዳይፈቅዱ፣ የተፈቀደ ብድር ካለም እንዳይለቀቅ መታገዱን የባንኩ ምንጮች አስታውቀዋል፡፡ፕሬዚዳንቱ ለምን እንደተነሱ ለማወቅ ከባንድ ቦርድ አመራር እንዲሁም ከአቶ ኃይለየሱስ ለመረዳት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡ የሪፖርተር ምንጮችም የፕሬዚዳንቱ መነሳት ምክንያቱን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ የመነሳታቸው ጉዳይ ግን ውስጥ ውስጡን ሲነገር መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ኃየለየሱስ የቀድሞው የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ሠርተዋል፡፡ ባንኩ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲጠቀለልና ህልውናው ሲያበቃ በንግድ ባንክ ውስጥ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ጥቂት ጊዜያት አገልግለዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ ጌታሁን ናና ልማት ባንክን በፕሬዚዳንትነት ሲመሩ ቆይተው፣ አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ሥልጣን ከተረከበ በኋላ እሳቸውም ፕሬዚዳንተንቱን ለአቶ ኃይለየሱስ አስረክበው ነበር፡፡

እስካሁን የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ኃይለየሱስ በአሁኑ ወቅት መነሳታቸው ሲታወቅ፣ በእሳቸው ምትክ የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ዋና የኢኮኖሚ ባለሙያና ምክትል ገዥ ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) እንደሚሾሙ ከልማት ባንክ የቦርድ አባላት ምንጮች ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዮሐንስ (ዶ/ር) የባንኩ የቦርድ አባል በመሆናቸው አባልነታቸው እንዲነሳ ተደርጎ ሺመታቸው በብሔራዊ ባንክ እስኪጸድቅ ድረስ ያለው የአካሄድ ጉዳይ ካሀልሆነ በቀር፣ የልማት ባንክ ቦርድ አባላት እሳቸው እንዲሾሙ ተነጋግረው መወሰናቸው ታውቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ልማት ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ነበር፡፡

ዮሐንስ (ዶ/ር) አነጋጋሪ በሆነው የ15 በመቶ የምንዛሪ ተመን ለውጥ ይታወቃሉ፡፡ ይህ ዕርምጃ ስህተት እንደነበርና የታሰበውን ውጤት እንዳላመጣ በቅርቡ በሚዲያ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡