በኮንሶ ዞንና በአሌ ልዩ ወረዳ ግጭት አራት ሰዎች ሲሞቱ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል በርካታ ቤቶች እየተቃጠሉ ነው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


DW በኮንሶ ዞንና በአሌ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌያት የተቀሰቀሰዉ ግጭት እንደቀጠለ ነዉ
በኮንሶ ዞንና በአሌ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌያት ላይ ዳግም በተቀሰቀሰ ግጭት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፡፡
ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግጭቱ ከባለፈው ዓርብ አንስቶ ዳግም የተቀሰቀሰው ሁለቱ ማህበረሰቦች በሚጎራበቱባቸው ቀርቀርቴ ፣ደልቤና ፣ ገዋዳ ፣ ኢያና ፣ ጎሮዜና ገርጋማ በተባሉ ቀበሌያት ውስጥ ነው፡፡
ግጭቱ ዳግም ሊቀሰቀስ የቻለው በአሌ ልዩ ወረዳ ቀርቀርቴ በተባለ ቀበሌ ውስጥ በቡድን የተሰባሰቡ ስዎች የአንድን ሰው ሕይወት አጥፍተዋል የሚል መረጃ ከተሠራጨ በኋላ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
ዶቼ ቬለ ( DW ) ያነጋገራቸው በአሌ ልዩ ወረዳ የቀርቀርቴ ነዋሪ ነኝ ያሉ አንድ የአይን እማኝ ከመስከረም አንድ ጀምሮ በሁለቱም ወገን በርካታ ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
የአይን እማኙ አያይዘውም << በግጭቱ እስከአሁን አራት ሰዎች ሲሞቱ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል፡፡ ከሟቾቹ ሁለቱ በቅርብ የማውቃቸው ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ በርካታ መንደሮች አሁን ድረስ በእሳት እየጋዩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በአሌ ልዩ ወረዳና በደልቤና ቀበሌ የምትገኝ ሐሙስ የተባለች መንደር ሙሉ በሙሉ ወድማለች >> ብለዋል፡፡
በኮንሶ ዞን የካራት ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን ገረመው በወረዳው አርካይዴ እና ገላቡ በተባሉ ሁለት በቀሌዎች ውስጥ በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ በተፈፀሙ ጥቃቶች ሁለት ሰዎች መሞታቸውን ለዶቼ ቬለ ( DW ) አረጋግጠዋል፡፡
<< በአሁኑ ወቅትም በቀበሌያቱ የሚገኙ ከ5 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ጥቃቱን በመሸሽ አካባቢውን ለቀው እየወጡ ይገኛሉ፡፡ የፀጥታ ሀይሉም ግጭቱን ለመቆጣጠር የቻለ አይመስልም፡፡ አለመረጋጋቱ ወደ ሌሎች ቀበሌያትም እየተዛመተ ይገኛል” ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡
ዶቼ ቬለ ( DW ) በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የደቡብ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዴ ግጭቱ ዳግም መቀስቀሱን አረጋግጠዋል፡፡
የመከላከያና የክልል ልዩ ሐይል አባላት ግጭቱ ወደ ተነሳባቸው ቀበሌያት እንዲገቡ ከመደረጉም በላይ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እየተለየ ይገኛል ብለዋል፡፡
አቶ አለማየሁ አያይዘውም<< ከሁለት ሳምንታት በፊት ከሁለቱም ወገን የተውጣጡ የአገር ሽማግሌዎች ባደረጉት ምክክር ሕዝቡ ወደ ሰላማዊ ኑሮው እንዲመለስ ፣ ግጭቱን የቀሰቀሱ አካላት ደግሞ ለሕግ እንዲቀርቡ ሲሉ ወስነው ነበር፡፡ የፀጥታ ሠራዊቱ በውሳኔው መሠረት በሁለቱም መስተዳድሮች በኩል የቀበሌ አስተዳዳሪዎችና የፖለቲካ አመራሮችን ጨምሮ ግጭቱን አነሳስተዋል የተባሉትን በሕግ ጥላ ሥር ለማዋል እንቅስቃሴ ሲጀመር አነኚህ አካላት ሂደቱን ማደናቀፍ ጀመሩ፡፡ ለእናንተ መብት በመታገላችን መንግሥት ሊያስረን ስለሆነ ለመብታችሁ ተነሱ በማለት ሕዝቡን ዳግም ግጭት ውስጥ እንዲገባ አድርገውታል >> ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፀጥታ ሠራዊቱ በእያንዳንዱ መንደር በመግባት የማረጋጋትና ግጭቱን በማነሳሳት የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ሥር የማዋል ሥራ አያከናወነ እንደሚገኝ አቶ አለማየሁ አስረድተዋል፡፡
በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞንና በአሌ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ከባለፈው የሀምሌ ወር ጀምሮ በመሬት ይገባኛል ጥያቄ በተቀሰቀሰ ግጭት እስከአሁን ከጠፋው የሰው ህይወትና ንብረት በተጨማሪ ከሃያ ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸው ይታወቃል።
ፎቶ ፣ ከአሌ ልዩ ወረዳ መንግስት ኮሚኒዩኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት