ግብፅና ሱዳን በቀጠሮው ቀን የህዳሴ ግድብ ድርድሩን የመጀመር ፍላጎት እንደሌላቸው ተሰማ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


የግብፅና ሱዳን ሚዲያዎች የአገሮቹን ባለሥልጣናት ጠቅሰው ባሠራጯቸው ዘገባዎች፣ በቀጠሮው ቀን ድርድሩን የመጀመር ፍላጎት እንደሌላቸው አመላክተዋል።

ሰኞ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ዳግም ይጀመራል ተብሎ ቀጠሮ የተያዘለት የህዳሴ ግድብ ድርድር፣ የመካሄዱ ጉዳይ አጠራጣሪ እንደሆነ ተሰማ።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት እያካሄዱ የነበረው ድርድር የአሥር ቀናት ፋታ ከወሰደ በኋላ ሰኞ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ዳግም እንዲጀመር ቀጠሮ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፣ ከግብፅና ከሱዳን በኩል በቀጠሮው ቀን ወደ ድርድሩ ለመመለሰ ፍላጎት አለመኖሩ ተሰምቷል።

የሁለቱ አገሮች ሚዲያዎች የአገሮቹን ባለሥልጣናት ጠቅሰው ባሠራጯቸው ዘገባዎች፣ በቀጠሮው ቀን ድርድሩን የመጀመር ፍላጎት እንደሌላቸው አመላክተዋል።

ለመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በተያዘው ቀጠሮ በሦስቱ አገሮች የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ውይይት እንደሚካሄድ ተወስኖ ነበር። ሚኒስትሮቹ በዚህ ቀን ለድርድር ከመቀመጣቸው አንድ ሳምንት በፊት የሦስቱ አገሮች የቴክኒክ ቡድኖች ቀድመው ተገናኝተው የልዩነት ነጥቦቻቸውን ለማጥበብ እንዲወያዩ አጀንዳ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ የሁለቱ አገሮች የቴክኒክ ቡድኖች ባለመገኘታቸው ውይይቱ ሊካሄድ አለመቻሉን  ከምንጮች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የቴክኒክ ባለሙያዎቹ ተወያይተው የሚያቀርቡት የውሳኔ ሐሳብ ሚኒስትሮቹ ለሚያደርጉት ድርድር መሠረት መሆኑን የገለጹት ምንጮች፣ የባለሙያዎቹ ውይይት ባለመካሄዱ፣ እንዲሁም በግብፅና በሱዳን በኩል ድርድሩን ስለመቀጠል የመረጃ ልውውጥ እያደረጉ ባለመሆኑ፣ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው ደርድር አጠራጣሪ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ይህንን ሁኔታ መሠረት በማድረግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአፍሪካ ኅብረትን በመወከል ድርድሩን ለምትመራው ደቡብ አፍሪካ አቻቸው መልዕክት መላካቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።

የአቶ ገዱ መልዕክት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሁለቱ አገሮች ወደ ድርድሩ እንዲመለሱ እንዲያሳስቡ የሚጠይቅ መሆኑንም ምንጮች አክለዋል፡፡

ሦስቱ አገሮች የህዳሴ ግድቡን የውኃ ሙሌትና አስተዳደር በተመለከተ በተናጠል ያቀረቧቸውን ሰነዶች አጣምረው በአንድ ሰነድ ድርድሩን ለሚመሩት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት እንዲያቀርቡ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ፣ እስከ መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቷቸው ነበር።

ይሁን እንጂ አገሮቹ ተገናኝተው አለመወያየታቸውንና የተባለውንም አንድ ሰነድ ማጠናቀር እንዳልቻሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ድርድሩን ለመቀጠል ዝግጁ እንደሆነች የጠቆሙት ምንጮች፣ ሁለቱ አገሮችም ከዚህ ወጪ አማራጭ እንደሌላቸው በመግለጽ ኢትዮጵያ በማናቸውም ጊዜ ድርድሩን ለመቀጠል አቋም መያዟን ገልጸዋል።

በዚህ ድርድር ውስጥ የግብፅ መንግሥት ጥቅም እንዲከበር ጫና እያደረገች መቆየቷ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የምትወቀሰው አሜሪካ፣ ከሳምንት በፊት በድርድሩ ሒደት ላይ ጫና ለማሳደር ለኢትዮጵያ ትሰጥ ከነበረው ዓመታዊ የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ 130 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነውን ለማቋረጥ መወሰኗን ባለፈው ሳምንት መዘገባችን ይታወሳል።