የፖለቲካ ልዩነቴ እንደተጠበቀ ሆኖ በተቀበልኩት ኃላፊነት የምችለውን ለሀገሬ አደርጋለሁ – ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


<< የፖለቲካ ልዩነቴ እንደተጠበቀ ሆኖ በተቀበልኩት ኃላፊነት የምችለውን ለሀገሬ አደርጋለሁ >> – ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ
የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት በመደባቸው የሥራ ኃላፊነት ላይ ለሀገር የሚበጀውን ለማበርከት ጥረት እንደሚያደርጉ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ገለጹ።
በጥናትና ምርምር ላይ ያተኮረ ተቋም ውስጥ በኃላፊነት መመደባቸው ኃላፊነቱን ለመቀበል ዋነኛው ምክንያት እንደሆናቸውም ፐሮፌሰር በየነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት ሥራቸው እና የፖለቲካ ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የፌዴራል መንግሥት በመደባቸው ኃላፊነት ላይ ሀገራቸውን ለማገልገል እና ውጤት ለማምጣት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። ሀገርና ህዝብን ማገልገል የሚለውን አብይ አላማ አንግበው ኃላፊነቱን በመቀበላቸው ለሀገር የሚበጅ ሥራ ለማከናወን ተዘጋጅተዋል።
እንደ ፕሮፌሰር በየነ ገለጻ፤ ኢንስቲትዩቱ የፓርቲ ሥራ የሚከናወንበት ሳይሆን መንግሥታት ቢቀያየሩም የማይለዋወጥ እና ከአንድ ምርጫ ዘመንም ዘልቆ የሚሄድ ሥራ የሚከናወንበት ሙያዊ ተቋም ነው። መሰረታዊ ጥናቶች እየተካሄዱ የፖሊሲ አቅጣጫዎች የሚቀየሱበት ሥራ በመሆኑ በዚህ አይነት ተቋም ውስጥ ለመሳተፍ እድል ማግኘት በእራሱ ጠቃሚ መሆኑን ፕሮፌሰሩ አስረድተዋል። ‹‹ይህንን መስራት አልችልም ››ማለት ነበር መሸነፍ የሚሆነው የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ ኃላፊነቱን ከተቀበሉ በኋላ በርካታ ባለሙያዎችን በማሳተፍ ውጤት ለማምጣት እንደሚጥሩም አመልክተዋል።
‹‹በፖለቲካ አቋሜ ግትር ቀኖና ውስጥ ቁጭ ብሎ ስልጣን ላይ እስክወጣ ድረስ ሥራዎች ሁሉ ይጠብቁኝ የምል እና ሁሉንም ነገር የምቃወም ሰው አይደለሁም ››ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ የፖለቲካ ልዩነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለሀገር ማበርከት የሚችሉትን ሁሉ ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የለውጡ መንግሥት ስልጣን ከያዘ ወዲህ በሚመለከቱኝ ሀገራዊ ሥራዎች ላይ ስሳተፍ ቆይቻለሁ ያሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን እና የመንግሥት ድርጅቶች ወደግል በማዛወር ሂደት የሚያማክረው ቦርድ ውስጥ እየሰራሁ ነው ሲሉ ተናግረዋል። ይህ ሁሉ ግን ለሀገር እና ለህዝብ እንጂ የተለየ አጀንዳ ይዞ በግል ተጠቃሚ ያደርገኛል ብለው የሚገፉት ሥራ እንደሌለ ገልጸዋል።
‹‹የተሰጠኝንም ኃላፊነት ለመቀበል ያስገደደኝ እና እኔንም የሳበኝ የተመደብኩት ሙያዊ የሆነ የጥናት ማዕከል መሆኑ ነው። ከተመደብኩበት ሥራ ጎን ለጎንም የፖለቲካ ሥራዬን በጎንዮሽ ለማከናወን የሚያግደኝ ነገር አለመኖሩን አረጋግጬ ነው።የኢትዮጵያን ፖሊሲ በሚመለከቱ ሰፊ ጉዳዮች ላይ ሙያህን እንፈልጋለን የሚል ጥያቄ ሲቀርብልኝ ጥናትና ምርምር የሙያ ሥራ ነውና ለመካፈል ፍላጎት አድሮብኛል ›› ሲሉ በተመደቡበት ሥራ ዙሪያ ያላቸውን ምልከታ አጋርተውናል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የምርምር ሥራዎች ላይ ተመራማሪዎች የሚከውኑት ሥራ ሳይንሳዊ መንገዱን ስለመከተሉ ማረጋገጥ እና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ላይ ማሳለፋቸውን የገለጹት ፕሮፌሰር በየነ፤ አሁንም በኢንስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ስርዓቱን ማስተባበር እና ለተመራማሪዎቹ ሃሳብ የማመንጨት እንዲሁም በአካሄዱ ላይ ሙያዊ እገዛ የመስጠት ሥራ ማከናወን እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ፕሮፌሰር በየነ እንደገለጹት፤ መንግሥት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንም በተለያዩ መስኮች የማሰማራቱ ልምድ ቢዘገይም አሁን ግን ጅማሮው መልካም ነው። በኢትዮጵያ የሚገኙ ፓርቲዎች በመሰረታዊ የልማት አጀንዳዎች ላይ ልዩነት አላቸው ብለው እንደማያምኑና ልዩነታቸው በአተገባበራቸው እና ኢኮኖሚ መር አቅጣጫቸው ላይ መሆኑን የሚናገሩት ፕሮፌሰር በየነ ሁሉንም ባቀፈ መልኩ ክህሎት ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትም በሙያቸው ሀገራቸውን ማገልገል የሚችሉበት መንገድ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ጠቁመዋል።
‹‹ሀገርን ለመጥቀም መነሻ ካደረገ ሃሳብ በመነሳት የፓርቲ አመራሮች እና አባላትም ደረቅ ፖለቲካውን ብቻ ሳይሆን ሙያዊ ሥራዎች ላይ የሚሳተፉበት መንገድ ሊስፋፋ ይገባል ሲሉም›› አክለው ገልጸዋል።
እንደ ፕሮፌሰር በየነ ከሆነ፤ አሜሪካን ሀገር ላይ አንድ ሪፐብሊካን ወይም ዴሞክራት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ነው ተብሎ መስራት በሚችልበት ሙያው ተሾሙ እንዳይሰራ አይከለክልም፤ ኢትዮጵያ ውስጥም የምንሰራውም ለአንድ ሀገር ስለሆነ ሙያ እና ብቃት ያለው ሰው በመንግሥት ኃላፊነቶችም ተመድቦ ቢሰራ ለሀገር ይጠቅማል እንጂ ጉዳቱ አይታየኝም ሲሉ ተናግረዋል ።
የእልህ ፖለቲካ በመከተል‹‹ እውቀቴን እና ልምዴን ስልጣን ሳገኝ ብቻ ነው ለሀገር ጥቅም የማውለው›› የሚል ሃሳብ ማንገብ ችግር እንጂ መፍትሄ አያመጣም። በመሆኑም የፖለቲካ ልዩነት ቢኖርም በሀገር ጉዳይ ላይ በሙያው ሁሉም በጋራ ቢሰራ ኢትዮጵያ ታድጋለች ሲሉ ሃሳባቸውን ቋጭተዋል።
አዲስ ዘመን