ተፈናቃይ አርሶ አደሮች የተሰጠን የጋራ መኖሪያ ቤት የለም አሉ

“እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ገበሬ ባዶ እጁን ነው ያለው። ይህ ፈጣሪ የሚያውቀው እውነት ነው” በማለት ለቢቢሲ የተናገሩት ከመሬታቸው ተፈናቅለው የጋራ መኖሪያ ቤት ይሰጣቸዋል ከተባሉት ግለሰብ መካከል አንዱ ናቸው።

BBC Amharic : በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ አርሰው ያድሩ የነበሩ ገበሬዎች፣ በከተማዋ መስፋፋት እና ለልማት በሚል ምክንያት ከእርሻ መሬታቸው የተፈናቀሉ በርካቶች መሆናቸው ይነገራል።

ከእርሻ መሬታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው የአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ኮሚሽን በተጠናቀቀው 2012 ዓ.ም ብቻ መሬት ከተወሰደባቸው እና ለችግር ከተጋለጡ ከ67 ሺህ አርሶ አደሮች ላይ መረጃ ተሰብስቧል ብሏል።

ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ በ2012 ዓ.ም መሬታቸው ከተወሰደባቸው ገበሬዎች መካከል 1655 የሚሆኑት መጠለያ እና ገቢ ምንጭ በማጣታቸው በእምነት ተቋማት እና መንገድ ላይ በልመና ህይወታቸውን እየገፉ ነው።

ከንፋስ ስልክ፣ ቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች ለልማት በሚል ምክንያት ከይዞታቸው የተፈናቀሉ ገበሬዎች ጉዳያቸው መፍትሄ እንዳላገኘ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ዶሮ እንኳ የለንም”

አቶ ተሾመ ፈይሳ በየካ ክፍለ ከተማ 15 ሄክታር መሬታቸው የካ ኮንዶሚኒም ሲሰራ በ2004 ዓ.ም እንተወሰደባቸው ይናገራሉ።

አቶ ተሾመ እንደሚሉት ከሆነ የእርሻ መሬታቸውን ከተነጠቁ ወዲህ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ገልፀዋል።

“የእኔ እና የአባቴን 15 ሄክታር መሬት ሲወስዱብን 1 ካሬ መሬትን በ15 ብር ነው ያሰሉት። እኛ ወደ 14 የቤተሰብ አባላት እንሆናለን። በዛን ወቅት ለአጨዳ የደረሰ እህል እስክናነሳ እንኳን አልጠበቁንም። እህላችንን በዶዘር ነው የጠረጉት”

ከእርሻ ውጪ ሌላ ክህሎት እንደሌላቸው የሚናገሩት አቶ ተሾመ፤ የእርሻ መሬታቸው ከተወሰደ ወዲህ ላለፉት 8 ዓመታት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ይገልጻሉ።

“መሬታችን ከተወሰደ በኋላ እርሻ የለንም፣ ከብት ለንም። ዶሮ እንኳን የለንም። እኔ ብቻ ሳልሆን ሁሉም ገበሬ ባዶ እጁን ነው ያለው። ይህ ፈጣሪ እና ይህች ምድር የሚያውቁት ሃቅ ነው።” ይላሉ።

አዲስ አበባ እና የገበሬ ቤት

አቶ ተሾመ ጨምረው እንደተናገሩት እርሳቸው እና ጎረቤቶቻቸው የገቢ ምንጭ ስለሌላቸው ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት መላክ እንዳልቻሉ ያስረዳሉ።

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የነበሩት አቶ ታዬ ከበደም በተመሳሳይ የእርሻ መሬታቸው ለልማት በሚል ምክንያት ከተነጠቁ በኋላ ለችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ከ1995 ጀምሮ ለልማት በሚል ምክንያት የእርሳቸው እና የጎረቤቶቻቸው መሬት ስለተወሰደባቸው፤ ከአዲስ አበባ ተሰድደው መውጣታቸውን አቶ ታዬ ይናገራሉ።

“እኛ አከባቢ መፈናቀል የቆየ ነገር ነው። አያቶቻችንም ከመሃል ከተማ ተገፍተው ነው ወደ ከተማ ዙሪያ የወጡት። አገር ለቀው የተሰደዱም አሉ” በማለት ይናገራሉ።

መሬታቸው የተነጠቁ ገበሬዎች እና የተወሰነ የእርሻ መሬት ያላቸው ገበሬዎች በከተማ ግብርና እንዲሰማሩ ከ2012 ጀምሮ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን አርሶ አደሮቹ ጨምረው ተናግረዋል።

ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ- ኢዜማ አካሄድኩት ባለው ጥናት በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራዎች መፈጸማቸውን እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ለሰዎች መተላለፋቸውን አረጋግጫለሁ ማለቱ ይታወሳል።

የቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ወደ 20ሺህ የሚጠጉ ጋራ መኖሪያ ቤቶች በልማት ምክንያት ከእርሻ መሬታቸው ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች መሰጠቱን ተናግረው ነበር።

አርሶ አደሮቹ ግን በቀረችን መሬት ላይ አትክልትና ፍራፍሬ ትከሉበት ብለውን ትንሽ እንቅስቃሴ ተጀምሯል እንጂ ያገኘነው ነገር የለም ይላሉ።

የከተማ አስተዳደሩ የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፈትያ መሐመድ በአንድ ዓመት ውስጥ ከይዞታቸው የተፈናቀሉ 67 ሺህ አርሶ አደሮች መረጃ መሰብሰቡን ይናገራሉ።

“እነዚህ አርሶ አደሮች መሬታቸው ከተወሰደ በኋላ ወዴት እንዳሉ የሚያውቅ አካል የለም፤ መረጃው ያለው ማንም የለም። የተከናወነው ነገር ገበሬዎቹን የማፈናቀል ስራ ነው የሚመስለው” ይላሉ ኮሚሽነሯ።

የጋራ መኖሪያ ቤት አግኝተዋል?

ከይዞታቸው የተፈናቀሉት አርሶ አደሮች ተበታትነው ይኑሩ እንጂ የአንድ አካባቢ ጎረቤታሞች የነበሩት አርሶ አደሮች ማን የት እንዳለ ያውቃሉ።

ኮሚሽነር ፈቲያም ስለ አርሶ አደሮቹ መረጃ መሰብሰብ የተቻለው በእነዚህ አርሶ አደሮች አማካኝነት እያጠያየቁ ያሉበት ቦታ ድረስ በመሄድ እንደሆነ ይናገራሉ።

ኮሚሽኑ መረጃ የተሰበሰበባቸው 67ሺህ አርሶ አደሮች ከቀደመ ኑሯቸው ዝቅ ያለ ደረጃ ላይ ቢገኙም 1ሺህ 655 የሚሆኑት ግን በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እንደሚገኙ እና በልመና የሚተዳደሩም እንዳሉ ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ለእነዚህ ለከፍተኛ ችግር ለተጋለጡት አርሶ አደሮች በየወሩ ገንዘብ እንዲያገኙ በማድረግ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልፀዋል።

አዲስ አበባ አከባቢ ያሉ ነዋሪዎች

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ 2011 ግንቦት ወር የእርሻ መሬታቸውን የተነጠቁ ገበሬዎች ከ23ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲተላለፍላቸው ቢወስንም አርሶ አደሮች ግን የጋራ መኖሪያ ቤቱ ተላልፎ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።

የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ እና የአሁኑ የማዕድን ሚኒስቴር ሚኒስትር ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ይህን ጉዳይ በተመለከተ ከከተማው አስተዳደር ከለቀቁ በኋላ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ በከተማው ካቢኔ ውሳኔ መሠረት ለ20ሺህ አርሶ አደሮች ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲሰጥ መወሰኑን ገልጸዋል።

ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከመሬታቸው ላይ ተፈናቅለው በዝቅተኛ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ 67 ሺህ አባወራዎች እንደነበሩ በመጥቀስ ከእነርሱ መካከል “የከፋ ችግር ላይ ለወደቁት 20 ሺህ ኮንዶሚንየም” መሰጠቱን መግለጻቸው ይታወሳል።

“እንዲሰጥ የተወሰነው ቤት ቁጥር ከተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከግማሽ በታች ነው። እጣ የወጣው ጥቅምት 2012። ገበሬ እጅ የደረሰ ግን አንድም ቤት የለም። የከተማው የቤቶች ልማት ቢሮ ለምን ይዞ እንደሚቀመጥ ግልጽ አይደለም” የሚሉት ደግሞ ወ/ሮ ፈትያ ናቸው።

በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት ቢሮ አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።