የወላይታው ግርግር ብልጽግና ፓርቲ እና አመራሮቹ የፈጠሩት ችግር ነው ! ሰርጎ ገቦችም አደመቁት ! – ምንሊክ ሳልሳዊ

የወላይታው ግርግር ብልጽግና ፓርቲ እና አመራሮቹ የፈጠሩት ችግር ነው፡  ሰርጎ ገቦችም አደመቁት – ምንሊክ ሳልሳዊ

የወላይታው ግርግር በሌሎች ክልል እንሁን ዞኖችም ለመቀጠሉ ዋስትና የለም። ክልል ሆኖ የስልጣን ጥማትን ማስተንፈስ የፈለጉት የወላይታ ባለስልጣናት መታሰራቸውን ሰማን። የወላይታ ባለስልጣናት የክልል ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝ ራሳቸውን ከደቡብ ክልል ምክር ቤት አግልለው እንደነበር ይታወሳል። ባለስልጣናቱ የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ቅርንጫፍ አመራሮች ናቸው። ባለስልጣናቱ ሕዝቡን ወደ ግርግር ለመውሰድ የልብ ልብ የተሰማቸው መንግስት በደቡብ ክልል ላይ የሚከተለው አዲስ የ አደረጃጀት ፖሊስ መሆኑ የማይካድ ሐቅ ነው።

ብልጽግና መራሹና ገዢው ፓርቲ ኦዴፓ የደቡብ ክልልን ወደ ትናንሽ ክልሎች ለመከፋፈል የሚሔድበት አካሔድ የግርግሩ መነሻና ለወላይታ ባለስልጣናትም የትእቢት መሰረት መሆኑ እሙን ነው። የደቡብ ክልልን ለማፍረስ የሚኬድበት መንገድ የልብ ልብ የሰጣቸው የወላይታ ብልጽግና አመራሮች የሲዳማ ክልል መሆን የፖለቲካ ቅናት ስላስከተለባቸው የራሳቸውን ክልል መመኘታቸውና ከፌዴራል መንግስቱና ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ማፈንገጣቸው አይፈረድባቸውም።

የሐገራችንን ሰላምና ደሕንነት የማይፈልጉ ኃይሎች የገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል ላይ የሚከተለውን አዲስ ፖሊስ ተገን አድርገው ሰርገው በመግባት ግርግር እንደሚፈጥሩም ቀድሞ ማወቅና መጠንቀቅ ያስፈልግ ነበር። የወላይታው ግርግር በሌሎች ክልል እንሁን ዞኖችም መቀጠሉ የማይቀር ሐቅ ነው። የዞን አስተዳዳሪዎች የስልጣን ጥማቸውን ለማርካት ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ክልል የመሆን ሳይሆን በመላው ሐገሪቱ በሰላም ተዘዋውሮ የመስራት ንብረት አፍርቶ የመኖር የሕልውና ጥያቄ ነው።

ጉዳዩን የለኮሰውም ሆነ የደቡብ ክልል ለማፈራረስ እቅድ ይዞ የሚንቀሳቀሰው ገዢው ፓርቲ የወላይታን ባለስልጣናት አፍሶ ማሰሩና በዞኑ ግርግር እንዲነሳ ምንጭ መሆኑን ፓርቲው ሊያውቅ ይገባል። ገዢው ፓርቲ ለራሱ አገዛዝ በሚያመቸው መልኩ የሚሔድበት መንገድና የወደፊት እቅዱን በደቡብ ክልል ላይ ለማሳካት የሚያራምደው የእቅድ አፈጻጸም የሕዝብ ጥያቄ አድርጎ ማቅረብም ጥፋት ነው። የወላይታ ዞን ባለስልጣናት የገዢውን ፓርቲ እቅድ ይዘው ወደ ፍጥነት መግባታቸው እንደ ወንጀል ሊያስቆጥርባቸውም ይሁን ሊያሳስራቸው አይገባም። ምንሊክ ሳልሳዊ