የጸጥታ አካላትን በተለይም የፖሊስ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።

የፖሊስ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተቋሙ አሳሰበ
(ኢፕድ) – የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት በተገቢው መንገድ ለማስጠበቅ የጸጥታ አካላ ትን በተለይም የፖሊስ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ እንደሚያስፈልግ የኢፌዴሪ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አሳሰበ።
የኢፌዴሪ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ለአዲስ ዘመን በላከው መግለጫ እንደተገለጸው ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በኦሮሚያ የሰዎች ግድያ እና የንብረት ውድመት ማጋጠሙ በርካቶችን ለችግር ዳርጓል። ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ የጸጥታ እና የፖሊስ ተቋማት ላይ የሪፎርም ሥራዎችን ማድረግ ላይ ትኩረት ያስፈልጋል ።
እንደ መግለጫው ከሆነ፤ የጸጥታ መዋቅሩ በተለይ ፖሊስ በኢትዮጵያ ያለውን ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ለውጥ ተከትሎ የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ማስጠበቅ በሚያስችለው ቁመና እና አመለካከት እንደገና የማደራ ጀት ወይም የሪፎርም ሥራ ሊከናወንበት ይገባል።
አሁን በክልሎች ያለው የልዩ ኃይል የፌዴራል ፖሊስ አካል ሊሆን በሚችልበት ጉዳይ መንግሥት ምክክር ቢያደርግ መልካም እንደሆነ ተቋሙ ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን፣ ልዩ ኃይሉ ዴሞክራት አመራሮች በሚገኙበት ወቅት የየክልሎቹን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ይችላል፤ በአንጻሩ አምባገነን የክልል መሪዎች እና አመራሮች ሲገኙ ደግሞ የሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ይደፈጥጣል ። ከዚህ በተጨማሪ በተለያዩ ክልሎች ልዩ ኃይሉ የግለሰቦች በሚመስል መልኩ ተከፋፍሎ ስለሚገኙ የልዩ ኃይሉ ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሄ እንደሚሻው አመልክቷል።
የክልል መንግሥታት የህዝቡን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ የራሳቸው ፖሊስ እንደሚያደራጁ ቢቀመጥም ምን አይነት ፖሊስ ማደራጀት እንደሚችሉ ግን በግልጽ የተቀመጠ ነገር እንደሌለ በመግለጫው አስታውቀዋል ። የህግ አውጪው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክልሎች ሊኖራቸው ስለሚገባው የፖሊስ ኃይል አደረጃጀት በህግ ወሰን እንዲያበጅለት የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ምክረሃሳብ አቅርቧል።