" /> ከዳያስፖራው ተግባራዊ መደመር ያስፈለጋል – የዶ/ር አብይን ጉብኘት በተመለከተ #ግርማ_ካሳ | Mereja.com - Ethiopian Amharic News

ከዳያስፖራው ተግባራዊ መደመር ያስፈለጋል – የዶ/ር አብይን ጉብኘት በተመለከተ #ግርማ_ካሳ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በአሜሪካ በዋሺንገትን ዲሲና በሎስ አንጀለስ ከኢትዮጵያዉያን  እና ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ በይፋ ተገልጿል። በዚህ ዉይይት ብዙ ኢትዮጵያዉያን ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዳያስፖራ ብዙ ስብሰባዎች፣ ዉይይቶች ተደርገዋል። ዉይይቱ ፣ ስሜታችንን ብቻ ገልጸንበት፤ ዶር አብይን እንደምደገፍ ብቻ አሳወቀን፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አዉለብልበን የምንለያየበት መሆን የለበትም። ስብሰባዎቹ የተጨበጡ ተግባራዊ ድሎችን ማስመዝገብ መቻል አለበት።

ምን ያህል እንደሆነ በግልጽ ባይታወቅም ከአገሩ ወጥቶ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ  በሚሊዮኖች የሚቆጠር ነው። ከ27 አመታት በፊት ቢያንስ ወደ 35 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ዋሺንግትን ዲሲ እንደሚኖሩ ሰምቼ ነበር። አሁን በዲሲና አካባቢዋ ያለ ምንም ጥርጥር ከመቶ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ። በዳላስ፣ በሎስ አንጀለስ፣ በኦክላንድ፣ በሲያትል፣ በቺካጎ ፣ በቶሮንቶ፣ በካልገሪ …ስትደምሯቸው በሰሜን አሜሪካ ብቻ ከሚሊዮን ይበልጣሉ ባይ ነኝ። አዉሮፓን፣ አውስትራሊያን፣ ደቡብ አፍሪካን ..ስትጨመሩ ቁጥሩን አስቡት:፡

ለዉይይታችን እንዲረዳ ቁጥሩን አሳንሼ እንበል አንድ ሚሊዮን ብቻ ነው በዉጭ ሰርቶ የሚኖረው ዳያስፖራ ብዬ ልዉሰድ።፡ይህ ዳያስፖራ ከዚህ በፊት ከነበሩ ገዢዎች ጋር ቢጋጭም አገሩን የሚወድ፣ ሕዝቡን የሚወድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አካል የሆነ  ነው። ከመቼውም ጊዜ በበለጠም ለዶ/ር አብይ አሀመድ ድጋፉን እየገለጸ ያለ ነው።

ፖላንድ በሁለተኛ አለም ጦርነት ጊዜ ፈራርሳ፣ የተገነባችው በዋናነት ከፖላንድ ውጭ በኖሩ ፖላንዳዊያን ገንዘብ ድጋፍ ነው። የት አገር እንደሆነ አሁን አላስታወስም ኢኩዋዶር ወይም እል ሳልቫዶር መሰለኝ። በአሜሪካ የሚኖሩ ዜጎቻቸው አንድ የፈረሰ ትልቅ ድልድይ እንደገና በአዲስ መልክ እንዲገነባ አድርገዋል።

በግላቸው በተለያዩ መልኩ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ሲደገፉና ሲረዱ የነበሩ፣ አሁን የየረዱ ያሉ ብዙ ወገኖች አሉ። እግዚአብሄር ያክበራቸው። ለምሳሌ አንዲት ካሊፎርኒያ የምትኖር  ከካንሰር የዳነች ነርስ የሆነች ኢትዮጵያዊት ፣  በሸኖ  የካንሰር ክሊኒክ አቋቁማለች። አንድ የማክበረው የትግራይ ልጅ፣  ጋደኛዬ ገንዘብ አሰባስቦ በትግራይ አይናለም በምትባል ከተማ በሶላር ኤነርጂ መብራት እንድታገኝ አድርጓል።

ይህ አይነት ስራ በተደራጀ፣ተጠያቂነትና ግልጽነት ባለው መልኩ በስፋት መቀጠል አለበት፡፡ ዳያስፖራ በአገር ላይ ያለውን ቀንበር በተወሰነ መልኩ ለማራገፍ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ መሰማራት አለበት። በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር መደመር አለብን ባይ ነኝ።

ለዚህ ይረዳ ዘንድ እንደሚከተለው መደረግ የሚችሉ ተግባራትን በማስቀመጥ፣ ዶ/ር አባይ ወደ አሜሪካ በሚመጡበት ጊዜ  በነዚህ ወይንም ተመሳሳይ በሆነ አጀንዳዎች ዙሪያ ንግግር ተደርጎ ወደ ስራ ቢገባ ጥሩ ይሆናል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ ችግር አለባት። ከዚህ የተነሳ ዶ/ር አብይ  ከዩናይትድ አረብ ኤሜረት የአንድ ቢሊዮን ዶላር እርዳታ አግኝተዋል። ለምነው ማለት ነው። ይህ አንድ ቢሊዮን ዶላር አንደኛ ማለቁ አይቀርም፣ ሁለተኛም በቂ አይደለም። በመሆኑም ዶ/ር አብይ እንደገና ወደ ልመና መሄዳቸው የማይቀር ነው።

አንዱ የዉጭ ምንዛሬ እንዲያጥረን ያደረገው ነገር የዉጭ እዳ ነው።  ዳያስፖራው ቢያንስ አገራችን ያለባትን እዳ እንድትከፍል በማድረግ ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል። ለምሳሌ በአዲስ አበባ የመልስተኛ ባቡር ግንባታ ወደ  400 ሚሊዮን ዶላር ነው ያወጣው። ከዚህ ውስጥ 360 ሚሊዮን ዶላሩ እዳ ነው። ከአዋሽ፣ በሸዋ ሮቢት፣ ኮምቦልቻ አልፎ ወደ ወልዲያ የሚወስደው የባቡር መስመር ወደ 1.7 ቢሊዮን ዶላር ነው።  ከዚያ ውስጥ 1.53  ቢሊዮን ዶላሩ እዳ ነው። ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ያለው መስመር 2.3 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ነው። ከዚያ ውስጥ  2.07 ቢሊዮኑ እዳ ነው። እነዚህ ሶስት የባቡር ፕሮጀክቶችን ብንወስድ እንኳን 3.96 ቢሊዮን ዶላር እዳ ኢትዮጵያ አለባት። ዳያስፖራ እነዚህን እዳዎች በአራት አመት ተኩልስ ውስጥ መድፈን ይችላል።

ይሄን አይነት ትልቅና አንገብጋቢ ጉዳይ በግለሰቦች ወይንም ቡድኖች የሚሰራ አይደለም። በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ፣ በቅንጅት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ መሰራት ነው ያለበት። በመሆኑም ዶ/ር አብይ በዳያስፖራው ተቀባነይነት ያላቸው ወገኖችን በሃላፊነት ቦታ ላይ ቢያስቀምጡ በጣም ይረዳል። ከዉጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ፣ ዶ/ር ወቅርነህ ገበየሁ  ጀምሮ፣  በየኤምባሲ እክሰተመደቡት (አቶ ካሳ ተክለማሪያምን ጨምሮ)  አምባሳደሮችና የቆንጽል ጽ/ቤቶች ያሉ፣ ቢቻል በጡረታ፣ አሊያም ወደ ሌላ ህጋላፊነት እንዲመደቡ በማድረግ፣   እንግሊዘኛ በደንብ መናገር የሚችሉ፣ ቢቻል ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ የመሳሰሉትንም፣ በዉጭ አገር ባሉ የኢትዮጵያዉያን ማህበረሰባት ዘንድ የሚከበሩ፣ ኢትዮጵያዊያንን ከያሉበት አምጥተው በአገር ጉዳይ እንዲሳተፉ ማድረግ የሚችሉ፣ ብቃትና ችሎታ ያላቸውን ወገኖች መሾም በጣም አስፈላጊ ነው።

እነዚህ ብቃት ያላቸው ዲፕሎማቶች በዉጭ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረስበ ኮሚቲዎቾ፣ የእምነት ተቋማት  ጋር በቅርበት በመስራት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ ዳያስፖራው የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግ ነገሮችን ማመቻቸት ይቻልል።

እንደው በትንሹ አስልቼው፣ ከላይ እንደገለጽኩት፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አዉስትራሊያ፣ አዉሮፓ.. የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን አንድ ሚሊዮን ናቸው እንበል። እርግጠኛ ነኝ ትንሽ ደሞዝ አገኙ ቢባል በአመት 12 ሺህ ዶላር አካባቢ ነው።  ሁለት ስራ ከሰሩ ወደ 25 ሺህ፣ ፕሮፌሽናል ከሆኑ ከአምሳ ሺህ በላይ ነው የሚያገኙት። ለዉይይት እንዲመቸን ሁሉም ኢትዮጵያዊን ትንሹን ደሞዝ በአመት 12 ሺህ ዶላር ነው የሚያገኙት እንበል። በወር $1000  ፣ በቀን ደግሞ $34 ዶላር። በመሆኑ አንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ አባል

  • የአመት ደሞዛቸውን 0.03%፣ በቀን አንድ ዶላር ቢሰጡ፣ በአመት 365 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል። ከ34 ዶላር አንድ ዶላር ማለት ነው። ያ በአንድ ጊዜ የአዲስ አበባ የመስለተኛ ባቡር ፕሮጀክትን እዳ ይዘጋል።
  • ከ34 ዶላር በቀን ከአንድ ወደ $2.09 ቢያደረጉት፣ 762 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል። በሁለት አመት ውስጥ 1.5 ቢሊዮን ዳር ይሰበሰባል። ከወልዲያ አዋሽ ያለው የባቡር መስመር እዳ ይዘጋል።
  • በቀን $2.09 ለሁለት አመት ተኩል ቢሰበሰብ ወደ $2.28 ቢሊዮን ዶላር ይጠጋል። ይሄን ከአዲስ አበባ ፣ ጅቡቲ ያለውን የባቡር ፕሮጀክት እዳ ይዘጋል።

እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው፣ በትንሹም አስልተነው፣ ዳያስፖራው በፕሮጀክት መልክ፣ በአራት አመት ተኩል ጊዜ ውስጥ  የሶስቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በቀላሉ መሸፈን እንደሚችል ነው። ያስቀመጥኳቸው ቁጥሮች በጣም ያነሱ ናቸው። ከትንሹ እንጀምር ከሚል። እንጂ እመኑኝ ከዚህም በላይ ዳያስፖራው የማድረግ አቅም አለው። ምንነው በየአመቱ በሚደረገው የኢትዮጵያዊያን እግር ኳስ ስዉድድር ለመዝናናት ምን ያህል ነው የምናወጥው ? ቢያንስ በቀን በመቶ ዶላር አናወጣም ? የመኪና ፍሬን ቢበላሽ በመቶዎች አይደለም የምናወጣው ? አቅሙ አለን። ሌሎች አገሮች አድርገዉታል። እኛ የማናደርገበት ምክንያት የለም።

ወገኖች ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ በተግባር እንደመር። በአፍ በስሜት ለአገራችን ያለንን ፍቅር መግለጽ ጥሩ ነው። አስፈላጊ ነው። ግን ተግባር ደግሞ ይጨመረበት። ትልቁ የአገራችን ጠላት ድህነት ነውና ሁላችን እዚያ ላይ እንረባረብ።

ዶ/ር አብይ በአሜሪካ ጉብኘት ሲያደርጉ የግድ እኔ እዚህ ያስቀመጥኩት ይሁን ማለቴ አይደለም። ግን ተመሳሳይ እቅዶች ተነድፈው  ለተግባራዊነቱ ስራ የምንጀመርበት መሆን አለበት። እንደው ስብሰባ ተደረጎ ተሟሙቀን፣ ፎቶ ተነስተን ፣ ተሞጋግሰን ብቻ የምንሄድ ከሆነ በጣም፣ እጅግ በጣም ያሳዝናል።


የመረጃ ቲቪ አባል በመሆን የስራችን ጥራት እንዲሻሻል ያግዙን። አባል ለመሆን እዚህ ላይ ይጫኑ።
JOIN Mereja TV