የግብጽ ወገን የተለያዪ አጀንዳዎችን እያቀረበ ዉይይቱን ዉጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ ነበር – አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከአልጀዚራ አረብኛ ስርጭት ጋር


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


በህዳሴ ግድብ ድርድር ወቅት የግብጽ ወገን የተለያዪ አጀንዳዎችን እያቀረበ ዉይይቱን ዉጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ እንደነበር ተነገረ
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ከግድቡ ጋር በተያያዘ ባደረጓቸው ድርድሮች የግብጽ ወገን የተለያዪ አጀንዳዎችን እያቀረበ ዉይይቱን ዉጤት አልባ ለማድረግ ተዘጋጅቶ ይመጣ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ። ግብጽ የራሷን ፍላጎት ብቻ ለመጫን ትሰራ እንደነበርም አስረድተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰሞኑን ከአልጄዚራ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በተለይ በህዳሴዉ ግድብ ዙሪያ ከአልጀዚራ አረብኛ ስርጭት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ትናንት ሰኔ 16 ቀን 2012 ዓም ማምሻዉን በጣቢያዉ ተላልፏል።
በዚሁ መሰረት በጣቢያዉ የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ መሀመድ ጣሃ ተወኩል በኩል ለቀረበላቸው ጥያቄዎች አቶ ገዱ ምላሽ ሰጥተዋል።
ግብጽ በጎረቤት አገሮች ላይ የጦር ካምፕ ለመመስረትና የኢትዮጵያን ደህንነት ለመፈታተን የምታደርገዉን ጥረት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ግብጽ የተለያዪ ሙከራዎችን በመጠቀም ላይ መሆኗን፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤት አገረቿ ጋር ማለትም ከሱዳን፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ኤርትራ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ያላት በመሆኑ ሙከራው የማይሳካ ህልም ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈ የጎረቤት አገሮች ግንኙነታቸውን በማጠናከር ወደ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ውህደት እያመሩ በመሆኑ በዚህ ሁኔታ ሲመዘን አገራቱ ግብጽን በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማጥቃት ይንቀሳቀሳሉ ብለዉ እንደማያምኑም አቶ ገዱ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለዉ ግንኙነት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ በከፍተኛ ደረጃ እየተጠናከረ እንደመጣ የገለጹት አቶ ገዱ፤ ከእርሻ መሬት ጋር በተያያዘ በድንበር አካባቢ የሚነሳው ችግር ለዘመናት የቆየ በመሆኑ ችግሩን በዘለቄታው ለመፍታት ሁለቱ አገራት በጋራ እና በትብብር እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ የተከሰተውን ሰሞነኛ ክስተት የግብጽ ሚዲያዎች እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዲያመራ በስፋት ሲሰሩ መቆየታቸውንም አቶ ገዱ አብራርተዋል።
የግብጽ ሚዲያዎች ሃላይብ ትሪያንግል በመባል የሚታወቀውን የሱዳን መሬት ግብጽ በወረራ መያዟን በተመለከተ አንድም ቀን ሳይተነፍሱ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ጉዳይ እንደ ትልቅ አጀንዳ አንስተው ሰፊ ሽፋን መስጠታቸው ያላቸውን ተዓማኒነት ትዝብት ውስጥ እንደሚከትም የተናገሩት።
ግብጾች ግድቡን ከእስራኤል ጋር ለማገናኘት መሞከራቸው ስህተት ብቻ ሳይሆን ወንጀል መሆኑንም አቶ ገዱ በነበራቸው ቃለ ምልልስ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።
Source –Ethiopian News Agency