በፍትህ ዙርያ ምን እየተሰራ እንደሆነ የማውቀው ነገር የለም- ለቤተሰቡ ዝምታው ከግድያው በላይ ነው የሆነብን – የጀኔራል ገዛኢ አበራ ባለቤት

‘የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን’ የጀነራል ሰዓረ እና ሜ/ጀነራል ገዛኢ ቤተሰቦች – BBC AMHARIC

ሰኔ 15/2011 ዓ.ም አመሻሽ፣ የአማራ ክልል ፕሬዚደንት አምባቸው መኮንን ( ዶ/ር) ጨምሮ ስብሰባ ላይ በነበሩ የአማራ ክልል አመራሮች ጥቃት ተፈጽሞ ተገድለዋል። በወቅቱ የደረሰውን ጥቃት በሚመለከት በመገናኛ ብዙሃን የተገለፀው “መፈንቀለ መንግሥት” ለማካሄድ ያለመ የሚል ነበር።

ከሰዓታት በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከባህዳሩ ክስተት በተጨማሪ ጥቃቱን ለማስቆም አዲስ አበባ በሚገኘው ቤታቸው ሆነው ወታደራዊ አመራር ይሰጡ የነበሩ የአገሪቱ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ገለጹ።

የጥቃቱ ሰለባ ግን ኤታማዦር ሹሙ ብቻ አልነበሩም። ለሥራ ጉዳይ በጀነራሉ ቤት የተገኙት ጡረተኛው ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራም ጭምር እንጂ።

አገሪቱ ውስጥ ትልቅ ድንጋጤ ፈጥሮ የነበረው ግድያ አንድ ዓመት ቢሞላውም ፍትህ እንዳላገኙና “የአገር ባለውለታ” የነበሩት ጀነራሎች ችላ መባላቸውን የጀነራል ሰዓረ መኮነን እና የሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ ቤተሰቦች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምን ነበር የተፈጠረው ?

ጥቃቱ በተፈጸመበት ዕለት ከሰዓት በኋላ ጀነራል ሰዓረ መኮንን የአዲስ አበባ አስተዳደር ባዘጋጀው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ ተካፍለው እንደተመለሱ ባለቤታቸው ኮሎኔል ጽጌ አለማየሁ ያስታውሳሉ።

ድንገት ግን መሪነታቸው የሚፈልግ ወታደራዊ ግዳጅ መኖሩን በስልክ ተደውሎ ተነገራቸው።

ስለ ባህርዳሩ ክስተት ስልክ ደውለው የነገሯቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እንደሆኑ የሚገልጹት ኮ/ል ጽጌ አለማየሁ፤ በመሃል ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ መምጣታቸውን ነገር ግን ጀነራል ሰዓረ በስልክ በሚመሩት ግዳጅ ተጠምደው ስለነበር ግቢ ውስጥ ይጠብቋቸው እንደነበር ይገልጻሉ።

“ከምሽቱ 3፡12 ሲል በጉዳዩ ዙርያ የአማራ ቴሌቪዥን ምን እያስተላለፈ እንደነበረ እንዳይ ተነጋግረን ወደ ሳሎን ገባሁ። ገና ቴሌቪዥኑን ከፍቼ ቻናል በመምረጥ ላይ እያለሁ አንድ ጥይት ተተኮሰ፣ ከዚያም ተደጋገመ። ሮጬ ስወጣ ሁለቱም በያሉበት ተመትተው፣ ልጁ [ግድያውን የፈጸመው] ደግሞ ሰዓረ እግር ስር ወድቆ አገኘሁት። ጀነራል ገዛኢ ወድያው ነበር የተሰዋው፣ ጀነራል ሰዓረ ግን ጥበቃዎቹ አቅራቢያችን ወደሚገኝ ዋሽንግተን ሆስፒታል ወሰዱት” ይላሉ ኮሎኔል ጽጌ አለማየሁ።

ከሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ አስከሬን እና በጀኔራሎቹ ግድያ ከሚጠረጠረውና መሬት ላይ ወድቆ ከነበረው የጀነራል ሰዓረ ጠባቂ አጠገብ በድንጋጤ ቆመው የነበሩት ኮሎኔል ጽጌ ጠባቂው ድንገት መሬት ላይ ተኝቶ የነበረው ተነስቶ ወደ ሰርቪስ ክፍል እንደሸሸና ሊይዘው ከሞከረ ሌላ ጠባቂ ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ያስታውሳሉ።

"ልባችንም ቤታችንም ጨልሟል" የጀነራል ሰዓረ እና ሜ/ጀነራል ገዛኢ ቤተሰቦችበ 2005 ዓ.ም በጡረታ ተሰናብተው የነበሩት ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ፣ ለአጭር ጊዜ በግል ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ቢሆንም፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን ተመልሰው በሙያቸው እንዲያገለሉ ተጠርተው እስከተገደሉበት ቀን ድረስ የመንግሥት ሥራ እየሰሩ እንደነበር ባለቤታቸው ወ/ሮ አበባ ዘሚካኤል ይናገራሉ።

“በፐብሊክ ሰርቪስ አውቶቡሶች ቦርድ ሆኖ አቋቁሟል፣ በባሕርና ሎጂስቲክስ እንዲሁም ትራንስፖርት ሚኒስቴር ብዙ ሥራ ይሠራላቸው ነበር። ውጭ አገር እየተላከ ብዙ ስራ ይሰራ ነበር። ለመከላከያም የተለያዩ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል። ለስሙ ጡረታ ወጣ ተባለ እንጂ የመንግሥት ሥራ ነበር የሚሰራው” ይላሉ።

እሁድ ጠዋት ወደ መቀለ ለመጓዝ ፕሮግራም የነበራቸው ሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ፤ ቅዳሜ ሰኔ 15 አመሻሽ ላይ ለሥራ ጉዳይ ወደ ጀነራል ሰዓረ ቤት ጎራ አሉ።

“ለሥራ ጉዳይ ነበር የሄደው። በመሃል ደውዬ ‘አልመሸም?” አልኩት። ‘እሺ ሰዓረ ስልክ ስለያዘ አልጨረስንም፤ መጣሁ’ አለኝ። የመጨረሻ ንግግራችን ነበር። ቆይቼም ደውዬለት ነበር፤ ስልኩን አያነሳም። በኋላ ተደውሎ ተነገረኝ” በማለት ባለቤታቸው ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

“ጡረታ ቢወጣም አርፎ አያውቅም። ሁሌም ተው ለራስህ ጊዜ ስጥ እለው ነበር። እሱ ግን ‘እኛ ከሞቱት ትርፍ ነን፤ ለመንግሥት እና ለአገር ነው እያገለገልኩ ያለሁት’ ነበር የሚለኝ” ይላሉ።

ግድያው ከተፈጸመ አንድ ዓመት የሞላው ቢሆንም ጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠው የሚናገሩት የጀነራል ሰዓረ ባለቤት ኮሎኔል ጽጌ አለማየሁ፣ በማኅበራዊ ሚድያ ከሚሰሙት ውጪ ስለጉዳዩ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ይህ ጉዳይ ለእኔ ትልቅ ስቃይ ነው። ሰዓረ እና ገዛኢ ሕዝብ እያገለገሉ ነው በእሳት የተቃጠሉት፡፡ . . .[ገዳዩ] ተይዟል ይባላል። . . . በፍትህ ዙርያ ምን እየተሰራ እንደሆነ የማውቀው ነገር የለም። ብዙ ሰው ይጠይቀኛል የማውቀው ነገር ግን የለም። ልባችን ጨልሟል፤ ቤታችን ጨልሟል” ይላሉ።

አክለውም “ሰዓረ፤ ጠበቃ እና ጠያቂ ያጣ ሰው ነው። የሚቆምለት ሰው የለውም፤ እኛ አቅም የለንም። ከእኔ አቅም በላይ ነው። ማን ጋር ተሂዶ አቤት እንደሚባልም አላውቅም፤ ጨንቆኛል” ይላሉ።

የሜ/ጀነራል ገዛኢ አበራ ባለቤትም፣ “. . .ሰዓረ እና ገዛኢ ትልልቅ መሪዎች ናቸው። የአገሪቱ ጀነራሎች ናቸው። በሥራ ላይ እያሉ ነው የተገደሉት። የፌደራል መንግሥት፣ የመከላከያ እና ደኅንነት ባለበት አገር ትልልቅ መሪዎች ማን ገደላቸው? ለምን? መልስ ማግኘት ይገባን ነበር። ለቤተሰቡ ዝምታው ከግድያው በላይ ነው የሆነብን . . .” ይላሉ።

አክለውም “የማውቀውና ያነጋገረኝ ባለስልጣን የለም፤ እንደተጎዳን፣ ጥቃት እንደደረሰብን፣ ያን የመሰለ ሰው አጥተን በጭንቀትና በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ እንዳለን ተረድቶ አይዟችሁ ያለን የለም፡፡ . . . የሚጠይቀኝ ባገኝ የሚሰማኝን እናገር ነበር. . . የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደን” በማለት ታጋይ አበባ ዘሚካኤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።