በህዳሴው ግድብ ድርድር ሰበብ የዓባይ ወንዝ ተጠቃሚነቷን የሚገድብ ስምምነት ኢትዮጵያ አትቀበልም – ገዱ አንዳርጋቸው


መረጃ ቲቪ አባል በመሆን የሳተላይት ቲቪውን ቀጥታ ስርጭት፣ ወቅታዊ ዜናዎችን እና ትንተናዎችን፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞችን፣ ስፖርት እና ሌሎችንም ዝግጅቶቻችንን በፍጥነት እና ጥራት ስልክዎ፣ ኮምፒዩተርዎ ወይም ቲቪዎ ላይ ማየት ይችላሉ። እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን አባል ይሁኑ


(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ሰበብ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚኖራትን ቀጣይ የመልማት መብት የሚገድብ ስምምነት እንደማትቀበል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው አረጋገጡ።
ሚኒስትሩ በግድቡና ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በግድቡ የውሃ አሞላል ያደረጉት ድርድር በቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ ወደ ስምምነት ቢቃረቡም፤ ሕግ ነክ በሆኑ ጉዳዮች የሚያቀራርቡ ሐሳቦች ተቋርጧል።
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምታደርገው ድርድር ግድቡን በሚመለከቱ ጉዳዮች እንጂ በቀጣይ የዓባይን ወንዝ ተጠቅማ የመልማት መብቷን እንደማያካትት አቶ ገዱ ተናግረዋል።
ግብፅ በግድቡ ላይ የሚደረገውን ድርድር በማስታከክ ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የሚኖራትን መብት ለመገደብ እየሞከረች መሆኗንም አስረድተዋል።
የግድቡ ጉዳይ የዓባይ ወንዝ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አንድ ነጠላ አካል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የዓባይ ወይም የናይል ወንዝ ተጠቃሚነት መታየት ያለበት ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች በተደራደሩበት የትብብር ስምምነት መሠረት ነው ብለዋል።
ስምምነቱ የወንዙን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንም ማዕከል ማድረጉን አስታውሰው፤ ግብፅ ከአሁኑ የሦስትዮሽ ድርድር አፈንግጣ መውጣቷን ገልጸዋል።
ስምምነቱን ከተደራደሩት 10 አገሮች ስድስቱ የፈረሙ ሲሆን፤ ከነዚህም ኢትየጵያን ጨምሮ አራት አገሮች ስምምነቱን በፓርላማቸው አፅድቀው የሕጋቸው አካል አድርገውታል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ተጠቃሚነት በተመለከተው ስምምነት መሠረት ወንዙን በፍትሃዊነት መጠቀም ትችላለች ብለዋል ሚኒስትሩ።
ሦስቱ አገሮች የሚያደርጉት ድርድር ግድቡን ብቻ እንደሚመለከትና ይህም ኢትዮጵያ በቀጣይ ሌላ ግድብ የመገንባትም ይሁን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ወንዙን የመጠቀም መብቷን የሚያስጠብቅ መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
ከግድቡ ጋር በተያያዘ ከአሜሪካ መንግሥት ተቋማት በተናጠል የሚወጡ መግለጫዎች ከኢትዮጵያ ሉአላዊነት አኳያ እንዴት ይታያል? ጥያቄ ለአቶ ገዱ ቀርቦላቸዋል።
“እንዲዚህ ዓይነት መግለጫ ባያወጡ ተመራጭ ነበር” ብለዋል።
ኢትዮጵያን ምንም ዓይነት ውጫዊም ይሁን ውስጣዊ ችግር ግድቡን ውሃ ከመሙላት እንደማያግዳት ተናግረዋል።
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 74 ከመቶ መድረሱና የውሃ ሙሌቱም በቀጣዩ ወር እንደሚጀመር መረጃዎች ያመለክታሉ።