ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሄድ እስከ 13 ወራት ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችልና ተጨማሪ ከ2 ቢሊዮን 512 ሚሊዮን በላይ ብር እንደሚስፈልገው አስታውቋል፡፡

በቀጣይ ምርጫውን ለማካሄድ ከ2 ነጥብ 51 ቢሊዮን በላይ ብር እንደሚያስፈልገው ቦርዱ አስታወቀ፡፡
ሕገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በሸራተን አዲስ ሆቴል ባካሄደው የባለሙያዎች ሀሳብ መስሚያ መድረክ፤ ምርጫ ቦርድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ከተወገደ፤ ምርጫ ሊያካሂድባቸው የሚችላቸውን 2 የቢሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳዎችን አቅርቧል።የመጀመሪያው የምርጫ ቦርድ የቢሆን የጊዜ ሰሌዳ (ሴናሪዮ) የምርጫ ሂደቱ 10 ወራት እንደሚወስድ አስቀምጧል። ሁለተኛው የቢሆን የጊዜ ሰሌዳ ደግሞ የምርጫው ሂደት ሶስት ተጨማሪ ወራት ወስዶ በ13 ወራት እንደሚጠናቀቅ ይገልጻል።

Image
Image
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስለተራዘመው ሀገራዊ ምርጫ አሁናዊና ቀጣይ ዝግጅቶች ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ማብራሪያ እየሰጠ ነው፡፡ ቦርዱ ነሐሴ 23/2012 ዓ.ም 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀ እንደበር ይታወሳል፡፡
በአንድ የምርጫ ጣቢያ 1 ሺህ 500 ሰዎችን፣ በአጠቃላይ በመላው ኢትዮጵያ ደግሞ ከ50 ሚሊዮን በላይ መራጮችን ለማሳተፍ በዝግጅት ላይ እንደነበር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ በምክትል ሰብሳቢው አቶ ውብሸት አየለ አማካኝነት አብራርቷል፡፡ ለ50 ሺህ የምርጫ ጣብያዎች የሚሆኑ ቁሳቁስ ማዘጋጀት፣ የምርጫ ሰነዶችን በተለያዩ ቋንቋዎች ማዘጋጀት፣ የምርጫ ክልሎችን ካርታ አዘጋጅቶ ማሳወቅና ሌሎችም ከቦርዱ ከሚጠበቁ ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ውብሸት ማብራሪያ የምርጫ ትምህርት በአምስት የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ማዘጋጀትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዲስ እንዲመዘገቡ ማድረግም የቦርዱ ወቅታዊ ሥራዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ከመጋቢት 7/2012 ዓ.ም ጀምሮ የኮሮና ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ክልከላዎች መጀመራቸው ሥራውን በአግባቡ ለመከወን እንዳላስቻለ ነው ቦርዱ ያስታወቀው፡፡
ይህንን ተከትሎም ቦርዱ ሁኔታውን ማጥናቱንና በጥናቱ ውጤት መሠረትም ክልከላው ከ14 ቀናት በላይ ከቀጠለ ምርጫውን በወቅቱ ለማካሄድ እንደማይችል ማሳወቁን አስታውሷል፡፡ በውሳኔ ሐሳቡም ወረርሽኙ መወገዱ በጤና ባለሙያዎች ተረጋግጦ ሲገለጽ እንደገና ሥራዎቹን በማስኬድ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል አሳውቋል፡፡ ለዚህ እንዲረዳውም የመራጮችን፣ ተመራጮችን፣ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞችንና ታዛቢዎችን የተመለከቱ የመረጃ ቋቶች እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በአምስት የአገር ውስጥ ቋንቋዎች የሚዲያ ክትትል ቁሳቁስ ግዥ እየተፈጸመ መሆኑና መሠል ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውም ተብራርቷል፡፡ የመራጮችና የዕጩ ምዝገባ በአነስተኛ ቴክኖሎጂ የሚካሄዱ በመሆናቸው ምርጫውን ማስኬድ አለማስቻሉንም ቦርዱ አስታውቋል፡፡ በኦንላይን ወይም በፖስታ ቤት በኩል ድምጽ ለማሰጠት መሞከር የሚያስኬዱ አለመሆኑንም ቦርዱ ማጤኑን አስታውቋል፡፡ የወደፊት የምርጫ ሁኔታን በተመለከተ ግምቶችን መነሻ አድርጎ የሁኔታ ትንተና ማድረጉንና ለዚህም እየተዘጋጀ መሆኑን ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው አብራርቷል፡፡
እንደ ቦርዱ ማብራሪያ በሁኔታ ትንተናዎችም የምርጫ ሂደቱ ሊዘገይ፣ የቁሳቁስ ዋጋ ሊጨምር፣ የገንዘብ እጥረት ሊያጋጥም፣ ከዓለማቀፍ አጋር አካላት ዕርዳታ ላይገኝ ይችላል፤ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ስጋቶችም ሊኖሩ ይችላሉ የሚሉት ተመላክተዋል፡፡ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ሊቀጥልና የአካል ደኅንነት መጠበቂያ ቁሳቁስም ሊያስፈልግም እንደሚችል፣ የምርጫ ሕግ ማሻሻል ሊያስከትል እንደሚችልም በትንተናው ተመላክቷል፡፡
ከዚህ በመነሳት ቦርዱ ሁለት የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀቱን ምክትል ሰብሳቢው አብራርተዋል፡፡ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ትኩረታቸውን ሙሉ በሙሉ ለኮሮና ምላሽ መስጠት ላይ ሊያደርጉ እንደሚችሉም አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሄድ እስከ 13 ወራት ጊዜ ሊወስድበት እንደሚችልና ተጨማሪ ከ2 ቢሊዮን 512 ሚሊዮን በላይ ብር እንደሚስፈልገው አስታቋል፡፡ ይህም አጠቃላይ የቦርዱን ወጪ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያደርሰው ተመላክቷል፡፡
(አብመድ)

 



መረጃ ቲቪን በተሻለ ጥራት እና ፍጥነት እንድናቀርብ እገዛችሁን እንሻለን።
መረጃ ቲቪን ለማገዝ ይህን ሊንክ በመጫን አባል ይህኑ - JOIN Mereja TV