ከወደብ ቀጥሎ ስምምነት ቢደረግባቸው የሚጠቅሙ አምስት ነጥቦች – ግርማ_ካሳ


ኢትዮጵያን ካጋጠሟት እጅግ ውስብስብ ችግሮች ለማዳን የተለያዩ ጠቃሚ ሃሳቦችን እና ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርቡ ነፃ ሚዲያዎች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይታወቃል። ስለዚህም ኢትዮ360፣ መረጃ ቲቪ፣ አዲስ ድምጽ፣ ምንሊክ ቲቪ እና ሌሎችም የኢትዮጵያዊነት አጀንዳ የሚያራምዱ ሚዲያዎች በመተባበር ፕሮግራሞቻቸውን በሳተላይት ቲቪ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሚዲያዎች የፈጠሩት ማህበር የሳተላይት ወጪውን መሸፈን እንዲያስችለው ይህን የጎፈንድሚ ፔጅ ከፍተናል → እዚህ ሊንክ ላይ ይጫኑ። ለትብብርዎ እናመሰግናለን።
 
በዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ኦስማን ሳሌህ የሚመራ የ’ኤርትራ ልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ገብቷል። ዶ/ር አብይ አህመድ ለኤርትራ መንግስት ጥሪ ካቀረቡ ወር አልሞላዉም። የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የአሜሪካን መንግስት፣ ካታር፣ የአልጂሪያ መንግስትና ሌሎች “አስታራቂዎች” ሊሆኑ የሚችሉ ሶስተኛ አካላት አላስፈለጉም። እየሆነ ባለውም ነገር ሳይደነቁና ሳይገረሙ እንደማይቀር ነው።
የዛሬው ቀን ለኤርትራም ለኢትዮጵያም ሕዝብ ትልቅ ቀን ነው ።ለሃያ አመታት የሰፈነዉን የጦርነት ድባብ ገፎ ሰላምን ለማውረድ የሚረዳ የመጀመሪያ እንቅስቃሴ በመሆኑ።
የ’ኤርትራን ልኡካን ቡድን ቦሌ አይሮፕላን ማረፊያ ሄደው የተቀበሉት ጠ/ሚኒስትር ዶር አብይ አህመድ ናቸው። በፕሮቶኮል መሰረት ዶር አብይ ቦሌ መሄድ አልነበረባቸው። የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበር መቀበል የነበረበት። ግን ዶር አብይ ያደረጉት አንደኛ ለኤርትራ ሕዝብ ክብር ሲሉ፣ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ኤርትራን ጉዳይ መፍታት አንገብጋቢ የአገር ጉዳይ በመሆኑና ሶስተኛ እነ አቶ ኦስማን ሳሌን የዉጭ አገር ሉካን ሳይሆን ወንድሞች፣ የአንድ ሕዝብ ልጆች አድርገው ስለቆጠሩ ነው።
የልኡካን ቡድኑ በምን ጉዳዮች ላይ ሊነጋገር እንደሚችል በገሃድ የታወቀ ነገር የለም። ሆኖም ግን ኤርትራ የአሰባንና የምጻዋን ወደብ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያ መጠቀም እንደምትችል ለዶ/ር አብይ ያሳወቃሉ የሚል መረጃዎች እየወጡ ነው። ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያ በአልጀርሱ ስምምነት መሰረት የተቋቋመዉን የድንበር ኮሚሽን ዉሳኔ እንደሚቀበሉም ገልጸዋል። ያንን በሚሉበት ጊዜ የኤርትራ ጥያቄ የባድመ ወይንም የድንበር ጥያቄ እንዳልሆነ ሳያውቁት ቀርቶ አይመስለኝም። በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የነበረው ችግር የመሬት ወይንም የኢኮኖሚ ችግር አልነበረም፣ አይደለምም። የነበረው ችግር በሻ’እቢያና በሕወሃት መካከል ያለው መናናቅና እልህ ነበር። የዶ/ር አብይ ወደ ሃላፊነት መምጣት ይሄን በሻ’እቢያና በሕወሃት መካከል ያለውን ሕዝብንና አገርን አንቆ የያዘው ማነቆ በመስበሩ ነው ለዚህ የበቃነው። ዶ/ር አብይ በፍቅር የማንፈታው ነገር የለም እያሉ ነው።
በዚህ ስብሰባ ከወደብ አጠቃቀም በተጨማሪ አጀንዳ ቢሆኑና ስምምነት ቢደረስባቸው ጠቃሚ ይሆናሉ የምላቸው ነጥቦች አሉኝ። እነርሱ፡
1.ኤርትራ ውስጥ የታሰሩ ፣ ያልታሰሩም ግን ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የሚፈልጉ፣ እንደ ግንቦት ሰባት ፣ ኦነግ .የመሳሰሉትን ለመቀላቀል ወደዚያ የሄዱ፣ ሁሉም ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መወሰኑ በጣም አስፈላጊና ቁልፍ ነው።
2.ኢትዮጵያና ኤርትራ ድርብ ዜግነትን በመፍቀድ፣ ፍላግት ያላቸው ሁሉም ኤርትራዉያን የኢትዮጵያ ዜግነት፣ ኢትዮጵያዉያን ደግሞ የኤርትራ ዜግነት ማግኘት እንደሚችሉ ለማረጋገጥ እንደሚሰራበት ቢገለጽ፣ እንደ ባድመ ያሉ ቦታዎች ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ ቢሄዱ ሕዝቡ ኢትዮጵያዊነቱን እንደያዘ እንዲቀጥል ይረዳዋል። ይህ ዉሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን በፓርላማ መወሰን ስላለበት፣ ሕግ መንግስት ማሻሻል ስለሚጠይቅ፣ እስከዚያው ማንኛው ኤርትራዊ በኢትዮጵያዊ፣ ማንኛውም ኢትዮጵጵያዊ በኤርትራ መኖር፣ መስራት፣ መነገድ ፣ መማር እንደሚችል ማረጋጋጥ በጣም ይረዳል።
3.በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ድንበሩ በሁለቱም መስመር እስከ መቶ ኪሎሜትሮች ከወታደራዊ እንቅስቃሴ የጸዳ (demilitarized) ቢሆን ጥሩ ነው።
4.ማንኛውም ዜጎች ምንም ነገር ሳይጠየቁ ፣ ከአስመራ ወደ ከረን፣ ከአክሱም ወደ ሽሬ እንደሚኬደው ፣ ከሽራሮ ባሬንቱ፣ ከሰናፈ አዲግራት፣ ከአሰብ ደሴ መመላለስ፣ መዉጣት መግባት እንዲችሉ ቢደረግ ጠቃሚ ነው።ድንበሩ ክፍት መሆን አለበት። በአጭሩ ድንበሩ “ድንበር የለሽ” መሆኑ አስፈላጊ ነው።
5.የኤርትራ ነገር ሲነሳ ብዙ ጊዜ ወደ ልቤና ወደ አይምሮዬ የሚመጣው ዶር ክፍሉ ገብረ እግዚአብሄር ነው። የአስመራ ዩኒቨርሲቲ የናቹራል ሳይንስ ዲን የነበረና በ Computational Mathematics ከኢሊኖይ ኢንስቲቲዉት ኦፍ ቴክኖሎጂ ፒ.ኤች.ዲውን የተቀበለ ፣ መምህሬና ጓደኛዬ ነው። ዶር ክፍሉ በአሁኑ ጊዜ የወንጌላዊ ቤተክርስቲያን አማኝ በመሆኑ፣ በእምነቱ ምክንያት፣ በወህኒ ይገኛል። የኤርትር መንግስት ዶር ክፍሉንና በሺሆች የሚቆጠሩ ኤርትራዊ ወንድሞቻችንን መፍታት መቻል አለበት። የኤርትራ መንግስት የሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብር፣ ያሰራቸው ዜጎች ሁሉ እንዲፈታ፣ አንደ አሸን የፈሉትን ወታደራዊ ካምፖቹን እንዲዘጋ፣ አስገዳጅ የዉትድርና ስልጠናዉን እንዲያቆም የማግባባት ስራ መሰራት አለበት።
አንዳንድ ወገኖች ይሄ የውስጥ ጉዳይ ነው የሚሉ አሉ። የሰብአዊ መብት መከበር ድንበር አይወስነውም። የ ዶር ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ “በአንድ ቦታ ያለ ኢፍትሃዊነት፣ በሁሉም ቦታ ፍትህ ላይ አደጋ የሚፈጠር ነው“( Injustice anywhere is a threat to justice everywhere) እንዳለው፣ በኤርትራ ኢፍትሃዊነቱና ግፉ ከቀጠለ በኢትዮጵያዉን ሊኖር የሚገባው ፍትህ ላይም አደጋ የሚፈጥር ነው። የኤርትራ መንግስት የኤርትራ ሕዝብን መብት ማክበር ካልተቻለ፣ ለኤርትራዉያን መሆን ካልተቻለ፣ በመርህ ደረጃ እንዴት ለኢትዮጵያዉያን መሆን ይቻላል ? የሰብዓዊ መብቱን ጉዳይ የዶ/ር አብይ አስተዳደር ትልቅ ትኩረት ሰጥተዉበት የተጨበጠ ነበር እንደምናይ ተስፋ አደርጋለሁ።