ለ4011 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ

የኮሮና ወረርሽኝን ለመግታት ለ4011 የህግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ
የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ለ4011 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ እንደሚፈቱ አስታወቀ።
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫ እየሰጠ ነው፡፡
በመግለጫው መሠረትም
• ቀላል ወንጀል ፈጽመው እስከ ሦስት ዓመት የተፈርባቸውና በእስር ላይ የሚገኙ ታራሚዎች በይቅርታ እንዲለቀቁ ተወስኗል፤
• የአመክሮ ጊዜያቸው እስከ አንድ ዓመት ድረስ የሆኑ ታራሚዎችም ይቅርታ ተደርጎላቸዋል፤
• የሚያጠቡ እናቶች፣ ነፍሰጡር ታራሚዎችም ወንጀላቸው ግድያ ያልሆነ ከሆኑ በይቅርታ ይቅርታ ተደርጎላቸዋል፤
• የሌሎች አገራት ዜጎች ሆነው ከግድያ ውጭ ወንጀል ፈጽመው ያሉ ታራሚዎችም በይቅርታ እንዲለቀቁና ከኢሜግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ጋር በመሆን ወደአገራቸው የሚሸኙ ይሆናል፤
• በክስ ሂደት ላይ ያሉና የሚያጠቡ ወይም ነፍሰጡር ሴቶችም ለልጆችና ጽንሳቸው ደኅንነት ሲባል ክሳቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል፤ ብዛታቸው ሰባት መሆኑም ተገልጿል፡፡
• በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ተከሳሾ የክስ ሂደትም ከዚህ በፊት ከተቋረጠላቸው ጋር ተመሳሳይ ተሳትፎ የነበራቸው 20 ሰዎች ክስ ተቋርጧል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመግለጫው እንዳመለከተውም የማረሚያ ቤቶችን አጠቃላይ ሁኔታ ከተመለከተ በኋላ ነው ይቅርታውን ያደረገው፡፤
በይቅርታው 4 ሺህ 11 ታራሚዎች መለቀቃቸው ነው የተገለጸው፡፡ ውሳኔ በይቅርታ ቦርዱ ቀርቦ በሀገሪቱ ርእሰ ብሔር የጸደቀ እንደሆንም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡
ታራሚዎቹ ከማረሚያ ቤት ሲወጡ የጤና ምርመራ እንደሚደረግላቸውና ከቫይረሱ ጋር አጠራጣሪ ጉዳዮች የሚታዩ ከሆነ ወደ ማቆያ እንደሚወሰዱም ታውቋል፡፡
ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ስም ዝርዝር ወደየአካባቢያቸው ፖሊስ እንደሚላክና ክትትል እንደሚደረግባው፤ በተመሳሳይ ወንጀል የሚጠረጠሩ ከሆነም ይቅርታው ሊነሳ እንደሚችልና በአዲሱ ጉዳይም እንደሚጠየቁ ለዚህም ተገቢው ማብራሪያ ተሰጥቷቸው እንደሚለቀቁ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡