የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና ለምን በረራ አያቆምም? ጥያቄው ልክ ነው፣ ግን በረራ ማቆም መፍትሔ አይደለም።

Image result for ethiopian airlines and coronavirus

ኢትዮ ኤፍ ኤም – የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ቻይና እያደረገው ባለው በረራ ዙሪያ የተደረገ ቃለ መጠይቅ;-

የኮሮና ቫይረስ በቻይና መከሰቱን ተከትሎ ብዙዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ስጋት ውስጥ ናቸው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደግሞ ወደ ቻይና ከተሞች በረራውን መቀጠሉ ለብዙዎች ስጋት ዋነኛው ምክንያት ነው።

ኢትዮ ኤፍ ኤም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አቭዬሽን አካዳሚ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ደበበ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

ኢትዮ ኤፍ ኤም፡- በአሁኑ ሰዓት አየር መንገዱ በሳምንት ምን ያህል በረራዎችን ወደ ቻይና ያደርጋል? መዳረሻዎቹስ የትኞቹ የቻይና ከተሞች ናቸው?

አቶ ሰለሞን ደበበ፡-የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻይና ወደ 5 ከተሞች ይበራል፡፡ ቤጂንግ ፤ ሻንጋይ ፤ ቸንግዱ ፤ ሆንግ ኮንግና ጓንዡ መዳረሻዎቹ ናቸው፡፡ በሳምንት ወደ ቻይና ከተሞች 35 በረራዎችን ያደርጋል፡፡ ወደ እያንዳንዱ የበረራ መዳረሻዎች በቀን በቀን ይበራል፡፡ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሳይሆን ከቻይና አዲስ ዓመት ጋር በተያያዘ የበረራ ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ የኖቨል ኮረና ቫይረስ ስርጭት በቻይና ሁቤ በሚባለው አካባቢ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቫይረሱ በተስፋፋባት በሁቤ ግዛት ከዚህ ቀደምም አይበርም አሁንም አይበርም፡፡ የቻይና መንግስትም ይህንን ወረርሽኝ ለመከላከል እርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል የቫይረሱ መነሻ የሆኑትን አካባቢዎች መዝጋት ነው፡፡ ከዛ አካባቢ የሚወጣም ሆነ የሚገባ በረራም የለም፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም፡- እሳካሁን ባለው መረጃ ከ35 ሺህ በላይ ዜጎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ 800 በላይ ቻይናውያንን ቀጥፏል፡፡ ስጋቱ አለም አቀፍ ነው፡፡ ኢትጵያውያን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ናቸው ከዚህ አኳያ አየር መንገዱ ወደ ሌሎቹ የቻይና ከተሞች የሚደርገውን በረራ ለምን አያቆምም?

አቶ ሰለሞን ደበበ፡- የኮረና ቫይረስን አስመልክቶ የተለያዩ ግለሰቦች ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለምን በረራ አያቆምም ጥያቄው ልክ ነው ግን በረራ ማቆም ለዚህ ችግር መፍትሔ ነው አይደለም የሚለውን በትክክለኛ አተያየ መመልከት ያሻል፡፡ ለዚህ የቫይረስ ስጋት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመብረሩ ነው ወይ ለሚለው አይደለም ነው መልሱ እንደውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጥታ እየበረረ ከሌሎቹ የቻይና ግዛቶች የሚነሱት መንገደኞች አስፈላጊው ምርመራ መደረጉን የማረጋገጥ እድል አለው፡፡ ባለመብረሩ ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ለምን ቢባል ሌሎች አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚበሩ በመሆናቸው ነው፡፡ በአዲስ አበባ አድርጎ ወደ ሌሎቹ የአፍሪካ መዳረሻዎች መብረር የሚፈልግ መንገደኛ ካለ አየር መንገዱ በረረም አልበረረም ወደ አዲስ አበባ የሚመጡበት ሁኔታ አለ፡፡ አየር መንገዱ እራሱ ስለማያመጣቸው የመቆጣጠር እድል የለውም፡፡ ለዚህ ነው የአየር መንገዱ ወደ ቻይና መብረርና አለመብረር የቫይረሱን ስጋት አይጨምርም አይቀንስም የምንለው፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ላለማቋረጥ ከቻይና ጋር የገባው ውል ሳይኖር አይቀርም የሚሉ አሉ፡፡ አየር መንገዱ ከበረራ ጋር በተያያዘ የተለየ ስምምነት ከቻይና ጋር አለው?

አቶ ሰለሞን ደበበ፡- በረራን ላለማቋረጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገባው ግዴታ የለም፡፡ አየር መንገዱ ከሚበርባቸው ሀገሮች ጋር ጠንካራ ግንኙነት አለው በመጥፎም በመልካም ጊዜያቶች ፤ ከዚህ አንፃር አየር መንገዱ እንደዚህ አይነት መልካም ያልሆኑ ችግሮች ሲፈጠር እርምጃ ለመውሰድ አይቸኩልም፡፡ ታሪካዊ ልምዳችንም የሚሳየው ይህንን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ኢቦላ ቫይረስ በተከሰተ ጊዜ ፤ አዲስ ኤርፖርት በሚሰሩበትና ከተማቸውን በሚቀይሩበት ጊዜ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጋራ ዘልቋል፡፡ ይህ ደግሞ የተለየ ስምምነት ኖሮ ሳይሆን ያ ባህል ስላለን ነው፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም፡- ኮረና ቫይረስን ለመቆጣጠር አየር መንገዱ በኤርፖርቶች እያከናወነ የሚገኘው ጥንቃቄ ምን ይመስላል?

አቶ ሰለሞን ደበበ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቻይና መንግስት በሁሉም ኤርፖርቶች ከፍተኛ የቁጥጥርና የምርመራ ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡ ቤጂንግ ላይ መንገደኞች ከበረራ ሰዓታቸው 11 ሰዓት ቀድመው እንዲመጡ መመሪያ ወጥቶ በዛ መልኩ እየተስተናገዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም መንገደኞቹን ከመቀበል ጀምሮ ወደ አውሮፕልን ከመግባታቸው በፊትና ከገቡ በኋላ ምርመራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ ከጤና ሚንስቴር ፤ ከማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በመተባበር በአለም አቀፉ የጤና ድርጅት መስፈርት ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም፡- አንዳንድ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ወደ ቻይና አንበርም በማለታቸው ተቋሙ ከስራቸው እንዳባረራቸው እየተወራ ይገኛል፡፡ አየር መንገዱ ያባረራቸው ሰራተኞች በተጨባጭ አሉ?

አቶ ሰለሞን ደበበ፡- ወደ ቻይና አልሄድም ብሎ ጥያቄ ያቀረበ ሰራተኛ የለም፡፡ በዛ ምክንያት እርምጃ የተወሰደበት የለም፡፡ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አየር መንገዱ የሰራተኞቹ የጤና ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው እርሱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8